የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ የልጅ ልጅ አረፈች

ጨቋኙን የነጭ አገዛዝ በመታገል የሚታወቁት የደቡብ አፍሪካ የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ የልጅ ልጅ ዞሌካ ማንዴላ ህይወቷ አለፈ።

በ43 ዓመቷ ህይወቷ ያለፈው ዞሌካ ጸሃፊ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነበረች።

የአፓርታይድ ስርዓት ከተገረሰሰ በኋላ በደቡብ አፍሪካ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ነበሩ ኔልሰን ማንዴላ።

የልጅ ልጃቸው ዞሌካ ማንዴላ ህይወቷ ያለፈው በካንሰር ህመም መሆኑንም ቤተሰቦቿ አስታውቀዋል።

የቤተሰቡ ቃለ አቀባይ በኢንስታግራም ላይ በሰጡት መግለጫ ዞሌካ ሰኞ ማምሻውን በጓደኞቿ እና በቤተሰቦቿ ተከባ ህይወቷ አልፏል ብለዋል።

ዞሌካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በካንሰር ህክምናዋ ያጋጠማትን ውጣ ውረድ እንዲሁም በአንድ ወቅት የአደንዛዥ ዕጽ ሱሰኛ እንደነበረች በመናገሯ በበርካቶች ዘንድ ዕውቅናን አትርፋለች።

በተጨማሪም በድባቴ ትሰቃይ እንደነበር እንዲሁም በልጅነቷ የወሲብ ጥቃት እንደደረሰባትም ታሪኳን አጋርታለች።

የ13 ዓመት ሴት ልጇ በአውሮፓውያኑ 2010 በመኪና አደጋ መሞቷን ተከትሎ የትራፊክ ደህንነትም ላይ ዘመቻ ስታደርግ ነበር።

የህይወት ታሪኳንም ‘ዌን ሆፕ ዊስፐርስ’ በሚል ርዕስም መጽሃፍ አሳትማለች።

ዞሌካ በካንሰር የተጠቃችው ከአስር አመታት በፊት ነበር። ህክምና ካገኘች በኋላም ተሽሏት ነበር።

ነገር ግን ባለፈው አመት በጉበት እና በሳንባ ካንሰር እንደተጠቃችም አረጋገጠች። ሆኖም በህይወት በመቆየቷ ምስጋናዋን ገልጻ ነበር።