የእስራኤል የስለላ ተቋማት መጠነ ሰፊውን የሐማስ ጥቃት እንዴት ሳይደርሱበት ቀሩ?

እስራኤል ካላት ወታደራዊ እና የመረጃ አቅም አንጻር ቅዳሜ ማለዳ በሐማስ ስለተፈጸመባት የተቀናጀ ጥቃት ምንም አይነት ፍንጭ ሳይኖራት በድንገት መፈጸሙ አስደንጋጭ ሆኖባታል።

የእስራኤል ባለሥልጣናትም ከዚህ በፊት ካጋጠሙት በእጅጉ የተለየ ስለሆነው የሐማስ ጥቃት ሲጠየቁ “እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ ምንም አናውቅም” የሚል ነው ምላሻቸው።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች ከጋዛ ወደ እስራኤል ሲወነጨፉ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ፍልስጤማውያን ታጣቂዎች በከባድ ምሽጎች የታጠረውን በእስራኤል እና በጋዛ ሰርጥ መካከል ያለውን ድንበር ጥሰው ወደ እስራኤል ገብተዋል።

የእስራኤል የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት የሆነው ሺን ቤት እና የውጭ ስለላ ተቋሟ ሞሳድ እንዲሁም የአገሪቱ የመከላከያ ኃይሎች ካላቸው አቅም እና ተጽእኖ አንጻር ማንም ይህ ድንገተኛ ጥቃት ይፈጸማል ብሎ አልጠበቀም።

ወይም ጥቃቱን በሚመለከት መረጃው ቢኖራቸው ምናልባትም በጊዜው እርምጃ መውሰድ ሳይችሉ ቀርተዋል ሊባል ይችላል።

በመካከለኛው መሥራቅ ካሉ አገራት ሁሉ አስራኤል ከፍተኛ ሃብት የሚፈስበት መጠነ ሰፊ ተጽእኖ ያለው የመረጃ እና ደኅንነት አላት።

የደኅንነት ተቋሞቿ በሌባኖስ፣ በሶሪያ እና ሌሎች አገራትን ጨምሮ በፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች ውስጥ ሳይቀር መረጃ አቀባዮች አሏቸው።

በዚህም የታጣቂ ቡድኖችን መሪዎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴን በትክክል ከመከታተል በተጨማሪ አስፈላጊ ሲሆን በማያወላዳ ሁኔታ ግድያን አስከመፈጸም የሚደርስ እርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል።

አንዳንድ ጊዜ የስለላ ድርጅቶቿ ወኪሎች የአቅጣጫ መጠቆሚያ መሳሪያዎችን በተፈላጊዎቹ ሰዎች መኪኖች ላይ በማስቀመጥ በድሮን ጥቃት እንዲገደሉ፣ ወይም የሚጠቀሙባቸውን ሞባይል ስልኮችን በማፈንዳት ተቀናቃኞቿን ታጠፋለች።

በመሬት ላይም በጋዛ እና በእስራኤል መካከል ባለው እና ውጥረት በማይለየው ድንበር ላይም ካሜራዎች፣ እንቅስቃሴን ለይተው የሚጠቁሙ መሳሪያዎች እና መደበኛ የጦር ሠራዊት ቅኝቶች ይካሄዳሉ።

በድንበር ላይ ያለው አጥርም ቅዳሜ ዕለት የተከሰተው አይነት የሰርጎ ገብ ጥቃቶችን ለመከላከል ተብሎ በተጠናከረ ሁኔታ የተገነባ እና የሚጠበቅ ነው።

ነገር ግን አሁን የሐማስ ታጣቂዎች አጥሩን በመጣስ፣ ወይም ቀዳዳ በመፍጠር አልያም በፓራሹት መሳይ መንሳፈፊያ አጥሩን አልፈው ለመግባት ሳይችሉ አልቀሩም።

ሐማስ የፈጸመውን አይነት ውስብስብ እና የተቀናጀ ጥቃት ለመፈጸም ጥንቃቄ የተሞላው ጊዜ የሚፈለግ ዝግጅት ማድረግ የሚፈልግ እንደሆነ ይታመናል።

ለዚህም ከእስራኤል የስለላ እና የመከላከያ አፍንጫ ስር በመሆን የተተኮሱትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን የማንቀሳቀስ እና የማከማቸት ሥራ በሐማስ በኩል እጅግ ለየት ያለ ጥንቃቄን የሚፈልግ የደኅንነት ተልዕኮን የሚጠይቅ ነው።

ይህ ጥቃት ከ50 ዓመት በፊት በእስራኤል ላይ የተፈጸመው የዮም ኪፑር ጥቃት ጋር በተመሳሳይ ዕለት መፈጸሙ እንዴት ሊሆን እንደቻለ በማለት የእስራኤል የመገናኛ ብዙኃን የአገራቸው ወታደራዊ እና የፖለቲካ መሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ እየጠየቁ ነው።

የዮም ኪፑር ጦርነት በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 06/1973 የተካሄደ ነው። ይህ ጦርነት በግብፅ እና በሶሪያ የሚመሩ የአረብ አገራት ጥምረት ከእስራኤል ጋር ያካሄዱት ጦርነት ሲሆን፣ አራተኛው የአረብ አስራኤል ጦርነት ተብሎም ይታወቃል።

ይህ የተቀናጀ የሐማስ ጥቃት እንዴት ሳይታወቅ በድንገት ሊከሰት እንደቻለ ከፍተኛ የሚባል ምርመራ እንደሚደረግ የእስራኤል ባለሥልጣናት የተናገሩ ሲሆን፣ ምርመራውም በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ሳይሆን “ለዓመታት የሚቀጥል ነው” ብለዋል።

የሐማስ ኃይሎች የተቀናጀ ጥቃት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገደበ ሳይሆን፣ በእስራኤል በኩል ምላሽ ለመስጠት ተከታታይ ዘመቻን የሚጠይቅ ነው።

ታጣቂዎቹ ደቡባዊውን ድንበር ተሻግረው ወደ እስራኤላውያን መንደር ገብተዋል። በዚህም በርካታ ማኅበረሰቦችን ተቆጣጥረዋል ተብሏል።

ስለዚህም የእስራኤል ኃይሎች እና ባለሥልጣናት ጥቃቱ እንዴት ለፈጸም ቻለ የሚለውን ከመመርመር በፊት ሰርገው የገቡትን ታጣቂዎች መቆጣጠር እና በእነሱ ጥቃት ስጋት ስር ያሉ እስራኤላውያንን ነጻ ማውጣት እና መጠበቅ ቀዳሚ ሥራቸው ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ እስራኤል ሐማስ አግቶ የያዘቸውን ዜጎቿን ለማስለቀቅ ወታደራዊ ተልዕኮን ወይም ድርድርን እንደ አማራጭ ልትጠቀም ትችላለች።

በተጨማሪም መላዋ እስራኤልን እና ዜጎቿን ሽብር ውስጥ የከተቱት ሮኬቶች የተተኮሱባቸውን ስፍራዎች በማደን ማስወንጨፊያዎቹን ከያሉበት ለመደምሰስ ልትሞክር ትችላለች።

ነገር ግን እነዚህ ማስወንጨፊያዎች በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ በቀላሉ እየተንቀሳቀሱ የት እንዳሉ ሳይታወቅ ሮኬቶችን መተኮስ ስለሚችሉ አዳጋች ሊሆን ይችላል።

ሌላው የእስራኤል አሳሳቢው ጉዳይ ሐማስ ሌሎችም ፍልስጤማውያን ቡድኖች ትጥቅ አንስተው እስራኤልን እንዲፋለሙ ያቀረበውን ጥሪ እንዳይቀበሉት ማድረግ እና በተለይ ሌባኖስ ውስጥ የሚገኘው ሄዝቦላህ ወደ ግጭቱ እንዳይገባ እና ግጭቱ ወደ ዌስት ባንክ እንዳይስፋፋ ማድረግ ነው።