የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድ ወር ሳይሞላቸው ሥልጣን ለቀቁ

ሰባስሽን ሌኮርኑ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የፈረንሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰባስሽን ሌኮርኑ አንድ ወር ሳይሞላቸው ሥልጣን ለቀቁ።

ካቢኔያቸው ይፋ በተደረገ በአንድ ቀን ውስጥ ሥልጣን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።

"ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ ለመቀጠል የሚያስችል ሁኔታ አልተሟላም" ሲሉ ለሥልጣናቸው መልቀቅ ምክንያት የሆናቸውን ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ ለመድረስ ፈቃደኛ አለመሆናቸውንም ተችተዋል።

ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ለአንድ ሰዓት የዘለቀ ውይይት ካደረጉ በኋላ ከሥልጣን መልቀቃቸው በይፋ ተገልጿል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንኮስ ባይሩ አስተዳደር መንኮታኮቱን ተከትሎ ከ26 ቀናት በፊት ነበር ሥልጣን የተረከቡት።

ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ካቢኔ እምብዛም ያልተለወጠውን የሰባስሽን ሌኮርኑ አዲስ ካቢኔ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተችተዋል።

ምርጫ ቀድሞ እንዲካሄድና ማክሮን ሥልጣን እንዲለቁም ጫና እያደረጉ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ማክሮን የሥልጣን ዘመናቸው እአአ በ2027 ከመገባደዱ በፊት ከሥልጣን እንደማይወርዱ ተናግረዋል።

የቀኝ ዘመሙ ናሽናል ራሊ ፓርቲ ምክትል መሪ ማሪ ለ ፔን "አሁን ማድረግ የምንችለው ምርጫ ማካሄድ ብቻ ነው" ብለዋል።

"እስካሁን ቀልዱ ቀጥሏል። የፈረንሳይ ሕዝብም መሮታል። ማክሮን አገሪቷን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል" ሲሉም አክለዋል።

በቀጣይ የሚሆነውን የሚወስኑት ማክሮን ናቸው። አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሾሙ ወይም ሥልጣናቸውን ሊለቁ ይችላሉ። ሌላው አማራጭ ካቢኔያቸውን መበተን ይሆናል።

ከሦስቱ አማራጮች ለእውነታቸው የቀረበ የሚሆነው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም ነው።

ሰባስሽን ሌኮርኑ ለፕሬዝዳንት ማክሮን ታማኝ ቢሆኑም በሥልጣን አልቆዩም።

ግራ ዘመም ፖለቲከኛ ሊሾሙ ቢችሉም፤ ሶሻሊስት አመራር እምብዛም ሊቀጥል አይችልም።

ስለዚህም አዲስ ምርጫ የሚካሄድበት ዕድል ሰፊ ነው።

ማክሮንን ከሚደግፉ ይልቅ ለማሪ ላ ፔን የቀረቡ ፖለቲከኛ ወደ ሥልጣን ሊመጡ ይችላሉ።

ሰባስሽን ሌኮርኑ በሁለት ዓመታት ውስጥ አምስተኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።

"የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎቶችን አቻችሎ መሥራት ዝግጁ ነበርኩ። ሁሉም አካል የሚፈልገው ሌሎች እንዲከተሉት ነው። ይሄ አይሆንም። ሁሉም አካል ለራሱ ያለውን የተጋነነ ምልከታ ገሸሽ ማድረግ አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።

ከ2024 አንስቶ የፈረንሳይ ፖለቲካ ነውጥና ውጥረት በዝቶበታል።

የማክሮን ፓርቲ በአውሮፓ ምክር ቤት ውጤት ካጣ በኋላ በምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ለማግኘት ድንገተኛ ምርጫ አከናውነዋል።

ሆኖም ግን ምርጫው ምክር ቤቱ በተለያየ ጽንፍ ያሉ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች የሚፎካከሩበት እንዲሆን አድርጓል።

ማይክል ባርነር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ሦስት ወራት ብቻ ነው ያገለገሉት።

ተከታያቸው ፍራንኮስ ባይሩ ለዘጠኝ ወራት ብቻ አገልግለው የበጀት ዕቅዳቸው በምክር ቤት ተቀባይነት ሳያገኝ ከሥልጣን ወርደዋል።

በ2024 የፈረንሳይ የበጀት ጉድለት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢ አንጻር 5.8% ሲደርስ፤ አገር አቀፍ ዕዳ 114% ደርሷል።

ከግሪክ እና ጣልያን ቀጥሎ በአውሮፓ ከፍተኛ ዕዳ ነው። እያንዳንዱ ፈረንሳዊ 50,000 ዩሮ ዕዳ አለበት ማለት ነው።

ሰባስሽን ሌኮርኑ ሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ የፈረንሳይ የድርሻ ገበያ አሽቆልቁሏል።