የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ሳርኮዚ ለምርጫ ቅስቀሳ ከጋዳፊ ገንዘብ በመቀበላቸው እስር ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፈረንሳይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ለምርጫ ቅስቀሳ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕገወጥ ገንዘብ ከሊቢያው መሪ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ በመቀበል ጥፋተኛ ተብለው የአምስት ዓመት እስር ተፈረደባቸው።
ሳርኮዚ ክሱን ፖለቲካዊ ነው ብለው ቢከራከሩም እአአ በ2007 ከጋዳፊ የተቀበሉትን ገንዘብ ለምርጫ ቅስቀሳ በመጠቀም ተከስሰዋል።
በምትኩ ሳርኮዚ ጋዳፊን በምዕራብ አፍሪካ አገራት ዘንድ ያላቸውን ስም ለመገንባት ቃል መግባታቸውን አቃቤ ሕግ ጠቅሷል።
የሰባ ዓመቱ አዛውንት ሳርኮዚ ፈረንሳይን እአአ ከ2007 እስከ 2012 ድረስ በፕሬዚዳንትነት አስተዳድረዋል።
ናታሊ ጋቫሪኖ የተባሉ ዳኛ ሳርኮዚ የቅርብ ረዳቶቻቸውን የሊቢያ ባለሥልጣናትን በማነጋገር ለምርጫ ዘመቻቸው የገንዘብ ድጋፍ እንዲጠይቁ ፈቅደዋል ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ሳርኮዚ በሕገወጥ መንገድ ከተገኘ የምርጫ ቀስቀሳ ገንዘብ በግል ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አልቀረበም ብሏል።
ሳርኮዚ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የአምስት ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።
ይህም ማለት ይግባኝ ቢጠይቁ እንኳ በእስር ቤት ማሳለፋቸው የማይቀር ይሆናል።
ችሎቱ ከእስር በተጨማሪ 100,000 ዩሮ ቅጣት አንዲከፍሉ በይኗል።
በቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ላይ ምርመራ የተጀመረው እአአ በ2013 የጋዳፊ የመጀመሪያ ልጅ ሳይፍ አል ኢስላም ሳርኮዚ ለምርጫ ቅስቀሳ ከአባቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መውሰዳቸውን በመግለጽ ከወነጀላቸው በኋላ ነው።
በቀጣዩ ዓመት በፈረንሳይ እና በመካከለኛው ምሥራቅ መካከል አገናኝ ሆነው የሚሰሩት ሊባኖሳዊው ባለሃብት ዛይድ ታኬይዲን የሳርኮዚ የምርጫ ቅስቀሳ "በከፍተኛ ሁኔታ" ከትሪፖሊ በተገኘ ገንዘብ መደገፉን ተናግረው የገንዘቡም መጠን ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ የተከፈለውን ጨምሮ 50 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የሳርኮዚ ባለቤት ካርላ ብሩኒ ሳርኮዚ ከጋዳፊ ጋር በተያያዘ ለቀረበው ክስ ማስረጃ የሚሆኑ ሰነዶችን በመደበቅ እንዲሁም ከወንጀለኞች ጋር በመተባበር ባለፈው ዓመት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ሁለቱንም ክሶች ክደው ተከራክረዋል።
እአአ በ2012 በምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ሳርኮዚ በተለያዩ ወንጀሎች ላይ እጃቸው አለበት በሚል ምርመራዎች ተደርጎባቸዋል።
እአአ በ2024 ለዳግም ምርጫ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በማውጣት እና ወንጀላቸወን ለመሸፈን የሕዝብ ግንኙነት ኩባንያ በመቅጠር ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ ይግባኝ ብለዋል።
በዚህ ክስ የአንድ ዓመት እስር ተፈርዶባቸው የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ስድስት ወር ተቀንሶላቸዋል።
እአአ በ2021 ለዳኛ ጉቦ ለመስጠት በመሞከር ጥፋተኛ ሆነው እስር የተፈረደባቸው የመጀመርያው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ሆነዋል።
በታሕሳስ ወር የፓሪስ ይግባኝ ፍርድ ቤት እስር ቤት ከሚገቡ ይልቅ ቤታቸው ሆነው መከታተያ ተገጥሞላቸው ቅጣታቸውን መፈጸም ይችላሉ ሲል ወስኗል።















