ማንቸስተር ዩናይትድ ከሊጉ ሊወርድ ይችላል - ሩበን አሞሪም

ማንቸስተር ዩናይትድ ከሊጉ ከወረደ 50 ዓመታት አልፈዋል።

ነገር ግን በፍፁም ታሪክ ራሱን ሊደግም ይችላል ብሎ የሚያስብ የለም ይላል የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ሳይመን ስቶን።

ምንም እንኳ ዩናይትድ የቀድሞው ክብሩን ቢያጣም ሰኞ ምሽት የነበረው ጨዋታ ግን የዘንድሮው ዩናይትድ ችግር ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው።

ሰኞ ምሽት ከኒውካስል በነበረው ጨዋታ 2 ለባዶ ተሸንፏል። አልፎም በጨዋታው መበለጡ ሩበን አሞሪምን አሳስቧቸዋል።

ከጨዋታው በኋላ ዩናይትድ ምናልባት ከሊጉ ሊወርድ ይችል ይሆን ተብለው በቢቢሲ የተጠየቁት አዲሱ አሰልጣኝ ሩብን አሞሪም "አይሆንም አልልም። ከደጋፊዎቻችን ጋር ግልፅ መሆን አለብን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ተንታኙ ሳይመን ዩናይትድ የመውረድ ስጋት አለበት ይሆን? የሚያስብሉ ነጥቦችን ይዞ መጥቷል፡

  • ማንቸስተር ዩናይትድ በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ ወር ብቻ ስድስት ጨዋታዎች ተሸንፏል።
  • በወርሀ ታኅሣሥ 18 ጎሎች ተቆጥሮባቸዋል። ይህ ከ1964 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
  • አሞሪም ባለፈው ኅዳር አሰልጣኝ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ሳውዝአምፕተን ብቻ ነው ከዩናይትድ በላይ ሽንፈት የቀመሰው። በዚህ ጊዜ በፕሪሚዬር ሊጉ ሳውዝአምፕተን 7 ጊዜ ሲሸነፍ ዩናይትድ 6 ጊዜ ተሸንፏል።
  • ዩናይትድ የአውሮፓውያኑን 2024 የሚያገባድደው 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነው። ይህ ከ1989 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በወቅቱ የውድድሩን ዘመኑን ያጠናቀቁት 13ኛ ሆነው ነበር።
  • ዩናይትዶች በሜዳቸው ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሲሸነፉ ከ1979 በኋላ ይህ የመጀመሪያው ነው። ሶስት የሊግ ጨዋታዎችን ሲሸነፉ ደግሞ ከ2015 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሩበን አሞሪም ለዩናይትድ ውጤት ቀውስ እኔም ተጠያቂ ነኝ ብለዋል።

"ቡድኑ ራሱን እያሻሻለ አይደለም። ለጊዜው ግራ መጋባት ላይ ነን። በአሁኑ ወቅት የዩናይትድ አሰልጣኝ ሆኖ በርካታ ጨዋታዎች መሸነፍ ያሳፍራል።"

ዩናይትድ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የማይጫወት ከሆነ ከአዲዳስ የሚያገኘውን 10 ሚሊዮን ፓውንድ ያጣል። ይህ ብዙም የሚያስደነግጥ አይደለም።

ነገር ግን ወደታችኛው ሊግ የሚወርድ ከሆነ ይህ ሌላ ጉዳይ ነው ይላል ሳይመን።

በወርሀ ጥር 14ኛ ደረጃ ይዘው የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ ከሊጉ የወረዱ አራት ክለቦች አሉ። ከሁለት ዓመታት በፊት ሊድስ ዩናይትድ የሆነው እንዲህ ነው።

እርግጥ ነው ዩናይትድ ይወርዳል ብሎ በእርግጠኝነት ማውራት ቀላል አይደለም። ነገር ግን ክለቡ በጥር ወር የዝውውር መስኮት ለውጥ ይፈልጋል።

ነገር ግን ባለፈው ሰኔ በወጣው የፋይናንስ ሪፖርት 113 ሚሊዮን ፓውንድ ያጣው ክለብ በዝውውር መስኮቱ ገንዘብ ያፈሳል ብሎ መጠበቅ ከባድ ነው።

"የተወሰኑ ተጫዋቾችን ካልሸጥን አዳዲስ ተጫዋቾችን ማምጣት አንችልም" ይላሉ አሞሪም።

ተጫዋቾችን መሸጥ ለዩናይት ገቢ ሊያስገኝለት ይችላል። ግን ማንን ይሸጣሉ?

ካዜሚሮ? ዚርክዚ? ራሽፈርድ?

ራሽፈርድ በኒውካስሉ ጨዋታ ወደ ቡድኑ ቢመለስም ተሰልፎ አልተጫወተም። ለምን? አሞሪም ተጠየቁ።

"እኔ ስለቡድኑ ነው የማስበው። እናንተ ደግሞ ሁሌ ማውራት የምትፈልጉት ስለራሽፈርድ ነው" የሚል ምላሽ ሰጡ።

"እኔ ጨዋታ ማሸነፍ ነው የምፈልገው።"