ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማንቸስተር ዩናይትድ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሲለያዩ ክለቡ ደግሞ ለሽያጭ ቀረበ
ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከማንቸስተር ዩናይትድ ለቀቀ።
ሁለቱ ወገኖች ለመለያየት የወሰኑት የ37 ዓመቱ ተጫዋች አወዛጋቢ በሆነው ቃለ መጠይቁ ክለቡን ከተቸና ለአሰልጣን ኤሪክ ቴን ሃግ “ክብር የለኝም” ማለቱን ተከትሎ ነው።
የሮናልዶ መልቀቅ በስምምነት ተቋጨ መሆኑን ሁለቱም ወገኖች ገልጸዋል።
ቀያዮቹ ባወጡት መግለጫ “ሁለት ጊዜ ከክለቡ ጋር በነበረው ቆይታ ላደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ክለቡ ያመሰግነዋል” ብሏል።
“ለእሱ እና ለቤተሰቦቹ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማቸው እንመኛለን። ሁሉም በማንቸስተር የሚገኙ አካላት በአሰልጣኝ ቴን ሃግ ስር ለውጥ በማምጣት ሜዳ ላይ ስኬታማ ለመሆን ትኩረት ያደርጋሉ” ብሏል ክለቡ።
በቴን ሃግ የሚሰለጥነው ማንቸስተር ዩናይትድ በደረጃ ሰንጠረዡ አምስተኛ ነው።
ከፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር ለዓለም ዋንጫ ኳታር ሚገኘው ሮናልዶ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከጋና ጋር ሐሙስ ያከናውናል።
ሮናልዶ በማንቸስተር ዩናይትድ ባደረጋቸው 346 ጨዋታዎች 145 ጎሎችን ከመረብ አሳርፏል።
“ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ባደረግነው ውይይት በስምምነት ኮንትራቱን ለመቅደድ ወስነናል” ሲል ተጫዋቹ ገልጧል።
“ማንቸስተር ዩናይትድ እና ደጋፊዎቹን እወዳቸዋለሁ። ይህ መቼም አይቀየርም። ሌላ ምዕራፍ ለመጀመር ትክክለኛው ሰዓት ይመስለኛል” ብሏል።
“ቡድኑ በቀሪው የውድድር ዘመን እና ለወደፊቱ መልካም ነገር እንዲገጥመው እመኛለሁ” ሲል አጠናቋል።
የሮናልዶ ሳምንታዊ ደመወዝ 500 ሺህ ፓውንድ ሲሆን፣ ከሰባት ወራት በላይ የሚቆይ ውል ነበረው።
በሌላ በኩል የማንቸስተር ዩናይትድ ባለቤቶች ሆኑት የግሌዘር ቤተሰቦች “ስትራቴጂካዊ አማራጮችን በማሰስ” ክለቡን ለመሸጥ እያሰቡ መሆኑን አስታውቀዋል።
አሜሪካዊያኑ ክለቡን እአአ በ2005 ነበር በ1.34 ቢሊዮን ዶላር የገዙት።
ይው ውሳኔ ይፋ የተደረገው ለዓመታት ደጋፊዎች ባለቤቶቹ ላይ ተቃውሞ ካሰሙ በኋላ ነው።
ክለቡ በመግለጫው ቦርዱ “በክለቡ አዲስ ኢንቨስትመንት፣ ሽያጭ ወይም ሌሎች ኩባንያውን የሚያካትቱ ግብይቶችን ጨምሮ ሁሉንም ስትራቴጂያዊ አማራጮችን ከግምት ውስጥ ያስገባል” ብሏል።
“የክለቡን የወንዶች እና የሴቶች ቡድኖችን ጨምሮ ለአካዳሚ ቡድኖች፣ ለደጋፊዎች እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ጥቅማ ጥቅሞችን በማምጣት የረዥም ጊዜ ስኬትን ለማጎልበት የስታዲየም እና የመሠረተ ልማት ማሻሻያ ግንባታ እና የክለቡ የንግድ ሥራዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስፋትን ጨምሮ በርካታ ውጥኖችን ያካትታል” ብሏል በመግለጫው።
ግሌዘሮች እአአ በ 2012 ካላቸው ድርሻ 10 በመቶውን የሸጡ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ዓመታትም ተጨማሪ አክሲዮኖችን ሸጠዋል።
“የክለቡን የስኬት ታሪክ እየገነቡ ለመቀጠል ቦርዱ የስትራቴጂክ አማራጮች በጥልቀት እንዲገመገሙ ፈቅዷል” ሲሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚዎቹ እና ዳይሬክተሮች አቭራም ግሌዘር እና ጆኤል ግሌዘር ተናግረዋል።
“ማንቸስተር ዩናይትድ እና ደጋፊዎቻችንን በተሻለ መልኩ ለማገልገል እና ለክለቡ የአሁን እና የወደፊት የዕድገት ዕድሎችን ከፍ ለማድረግ ሁሉንም አማራጮች እንመለከታለን” ብለዋል።
“በዚህ ሂደት ውስጥ የደጋፊዎቻችንን፣ የባለድርሻዎቻችንን እና የተለያዩ አካላትን ጥቅም በማስጠበቅ ላይ ሙሉ በሙሉ ትኩረት እናደርጋለን።”
የግሌዘር ቤተሰብ ከ1995 ጀምሮ የናሽናል ፉትቦል ሊጉን ታምፓ ቤይ ቡካነርስ ባለቤት ነው። አቭራም ግሌዘር ደግሞ ከአዲሱ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ትዌንቲ20 ክሪኬት ሊግ በ2021 አንድ ቡድን ገዝተዋል።
በ2006 አባታቸው ማልኮም መታመማቸውን ተከትሎ ጆኤል እና አቭራም የዕለት ተዕለት የዩናይትድን ሥራን ይቆጣጠራሉ። ቢሊየነሩ ማልኮም በ85 ዓመታቸው በ2014 ሕይወታቸው አልፏል።
በግንቦት ወር የቼልሲን 4.25 ቢሊዮን ፓውንድ ሽያጭ ያሳለጠው የአሜሪካ የኢንቨስትመንት ድርጅት ራይን ግሩፕ የዩናይትድ ብቸኛ የፋይናንስ አማካሪ ሆኖ እየሠራ ነው።