በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ባጋጠመ አደጋ በዋናው ጊቢ የመጀመሪያው ቀን ፈተና ሳይሰጥ ቀረ

በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ. ም. ባጋጠመው የመተላለፊያ ድልድይ መደርመስ አደጋ ምክንያት በዋናው ጊቢ የመጀመሪያው ቀን ፈተና እንዳልተሰጠ የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የውጭ ግንኙነት እና ኮምዩኒኬሸን ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እመቤት በቀለ ለቢቢሲ ገለጹ።

ከሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ዋናው ጊቢ ወደ ቴክኖሎጂ ጊቢ የሚወስደው የመተላላፊያ ድልድይ ተደርምሶ የአንድ ተማሪ ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ሦስት ተማሪዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ዶ/ር እመቤት ተናግረዋል።

“ተማሪዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብም ደንግጠው ግርግር ስለተፈጠ በተለይም በዋናው ጊቢ ፈተና ማስቀጠል አልቻልንም ነበር። የዋናው ጊቢ ተፈታኞች በድንጋጤ ወደ ውጭ ስለወጡ ፈተናው አልተሰጠም። በቴክኖሎጂ ጊቢ ግን ከሰዓት በኋላ ፈተናው ተሰጥቷል” ሲሉ አስረድተዋል።

ተደናግጠው ከዩኒቨርስቲው ቅጥር ጊቢ የወጡት ተማሪዎች እየተመለሱ እንደሆነ ጠቅሰው “አሁን ነገሮች ተረጋግተው ይገኛሉ። ለነገው ፈተና እንዲዘጋጁም መረጃ እየሰጠን ነው” ብለዋል።

ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ሦስት ተማሪዎች በሆስፒታል እንደጎበኙና 90 በመቶው ተማሪዎች የደረሰባቸው ጉዳት ቀላል እንደሆነ ዶ/ር እመቤት ተናግረዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ሪፈራል ሆስፒታልና በሌላም ሆስፒታል እንደየጉዳታቸው መጠን የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አክለዋል።

“በጣም መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ ካምፓስ ተመልሰዋል። ከሰባቱ ካምፓሶች በአምስቱ ውስጥ በሰላም ፈተናው ሲሰጥ ነው የዋለው” ብለዋል።

አደጋው በደረሰበት ጊዜ ከዋናው ጊቢ ወደ ቴክኖሎጂ ጊቢ የሚወስደውንና ለአሥር ዓመታት ያገለገለው ድልድይ እየተሻገሩበት የነበሩት ወደ 400 የሚጠጉ ተማሪዎች እንደነበሩ ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

“ሲሻገሩ የነበሩት ከ400 በላይ ተማሪዎች ነበሩ። ድልድዩ መሸከም ከሚችለው በላይ ተማሪዎች ስለወጡ ተደርምሶ ነው አደጋው ያጋጠመው” ብለዋል።

ድልድዩ ሲደረመስ በብረት ተመተው የእጅና እግር መሰበር የደረሰባቸው እንዳሉና የከፋ አደጋ የደረሰው ጭንቅላት ላይ መመታት እንደሆነ ገልጸዋል።

በተፈጠረው ግርግር ሳቢያ በዋናው ጊቢ ፈተናውን ያልወሰዱ ተማሪዎች ከነገ ጀምሮ ያለውን ፈተና ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚታመንና ያመለጣቸውን ፈተና በተመለከተ የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከፈተናዎች ድርጅት ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ አክለዋል።

“ፈተናውን መውሰድ ላልቻሉ ተማሪዎች ቀድሞውኑ በትምህርት ሚኒስቴር እና የፈተናዎች ድርጅት የተዘጋጀ አሠራር ነበር። ተማሩዎቹ በሐዋሳና በዙሪያው ያሉ ስለሆኑም ከድንጋጤያቸው ተመልሰው የቀረውን ፈተና ይወስዳሉ ብለን እናስባለን” ሲሉ ተናግረዋል።

አምስት ሜትር ስፋት ያለው ድልድይ ተማሪዎችን ከዋናው ዩኒቨርስቲ ወደ ቴክኖሎጂ ካምፓስ በመውሰድ ሲያገለግል እንደቆየ፣ እንዲህ ያለ አደጋ ደርሶ እንደማያውቅ ዶ/ር እመቤት ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ከመስከረም 30/2015 ዓ. ም. ጀምሮ በሚካሄደው እና በ131 የፈተና ማዕከላት በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና 984 ሺህ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀመጡ አገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ለቢቢሲ ገልጿል።

ትምህርትሚኒስቴር ዛሬ ከሰዓት የሰጠው መግለጫ፤ ባጠቃላይ ፈተና ከሚሰጥባቸው 130 ጣቢያዎች በ128ቱ ፈተና ሲሰጥ እንደዋለ ይጠቁማል።

ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ የፈተና ስርቆቶችን ለመከላከል በሚል ከዚህ በፊት ባልነበረ ሁኔታ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በመላው አገሪቱ በሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እየወሰዱ ይገኛሉ።

ተማሪዎቹ ትራንስፖርታቸው እና ፈተናውን ወስደው እስኪጨርሱ ድረስ በዩኒቨርስቲዎቹ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ መኝታቸውና ምግባቸው በመንግሥት ይሸፍንላቸዋል ተብሏል።