ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያዊው ሞገስ ጥዑማይ የ10 ሺህ ሜትር ባለድል ሆነ
ኢትዮጵያዊው አዲስ መጭ አትሌት ሞገስ ጥዑማይ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮንሺፕ መክፈቻ የ10 ሺህ ሜትር ባለድል ሆኗል።
ሞሪሺዬስ እየተካሄደ በሚገኘው ሻምፒዮና የ25 ዓመቱ ሞገስ 29 ደቂቃ ከ12 ሰከንድ በመግባት ወርቅ አጥልቋል።
ጭምዴሳ ደበሌ ሁለተኛ ሲወጣ ኬንያዊው አብራሃም ሎንጎሲዋ ነሐስ አግኝቷል።
የሞሪሺዬሱ ኮትዱዋር ስታድዬም በሚያስተናግደው ሻምፒዮና የመክፈቻ ቀን ሌሎችም ውድድሮች ተካሂደዋል።
ደቡብ አፍሪካ በወንዶችና ሴቶች አሎሎ ውርወራ ሁለት ሜዳሊያ አግኝታለች።
በሻምፒዮና የ100 ሜትር ማጣሪያ ተደርጎ ስመ ጥር አፍሪካዊያን አትሌቶች ወደ ቀጣይ ዙር አልፈዋል።
ፈጣኑ አፍሪካዊ የሚባለው ፈርዲናንድ ኦማንያላና ደቡብ አፍሪካዊው አካኒ ሲምቢኔ ግማሽ ፍፃሜውን ተሻግረዋል።
ኦማንያላ በያዝነው ዓመት መቶ ሜትር ርቀትን በ9.85 ሰከንድ መጨረሱ ይታወሳል።
በ800 ሜትር ማጣሪያ ደግሞ ኢትዮጵያዊያኑ ቶሎሳ ቦደና፣ ኤፍሬም መኮንን እና ባጫ ሞርክ ከምድባቸው አልፈዋል።
በመቶ ሜትር መሰናክል የማጣሪያ ውድድራቸውን ያደረጉት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ወደ ቀጣዩ ዙር ሊያልፉ አልቻሉም።
ዛሬ በሚካሄዱ የፍፃሜ ውድድሮች ካስተር ሰሜኒያ በ5 ሺህ ሜትር ፍፃሜ ትሳተፋለች።
በ400 ሜትርት ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያን የወከሉ ሴት አትሌቶች በማጣሪያው ድል ሲቀናቸው በወንዶች አንድ አትሌት ወደ ቀጣዩ ዙር ተሻግሯል።