በፔሩ የወርቅ ማዕድን ማውጫ በተነሳ እሳት 27 ሰዎች ሞቱ

ደቡብ አሜሪካ ውስጥ በምትገኘው ፔሩ በወርቅ ማውጫ አካባቢ በተነሳ እሳት ምክንያት ቢያንስ 27 ሰዎች ሞቱ።

ይህ በአገሪቱ ከማዕድን ማውጫ ጋር በተያያዘ ከገጠሙ አደጋዎች የከፋው ነው ተብሏል።

ያናኩይሻ የተባለው የማዕድን ድርጅት እንዳለው 175 ሠራተኞችን ከአደጋው ማዳን ተችሏል።

አደጋው የደረሰበት በፔሩ ደቡባዊ ግዛት አርኩዊፓ የሚገኝ አነስተኛ ማዕድን ማውጫ ነው።

እሳቱ የተነሳው በኤሌክትሪክ ገመድ ምክንያት እንደሆነ እና የእሳት አደጋው ሲነሳ ሠራተኞቹ በ100 ሜትር ጥልቀት እየሠሩ እንደነበር ተገልጿል።

በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የታዩ ምሥሎች በአካባቢው እሳት ሲቀጣጠል አሳይተዋል።

አርፒፒ.ፒኢ የተባለው ድረ ገጽ እንደዘገበው፣ በዘይት የጨቀዩ ከእንጨት የተሠሩ መተላለፊያዎች በአካባቢው መኖራቸው አደጋውን አባብሰውታል።

ተቋሙ ስለደረሰው አደጋ አፋጣኝ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ አሳውቋል።

“በዚህ አሳዛኝ ወቅት ቅድሚያ የምንሰጠው ከአደጋው ለተረፉ እና ሕይወታቸውን ላጡ ማዕድን አውጪዎች ጭምር ነው” ሲል ድርጅቱ መግለጫ አውጥቷል።

የቀጠናው አስተዳደር እንዳለው በቅርብ ያለው ፖሊስ ጣቢያ እሳቱ ከተነሳበት ቦታ 90 ደቂቃ ስለሚርቅ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪዎች ዘግይተው ደርሰዋል።

ላ ሪፐብሊካ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው የጠፉት ማዕድን አውጪዎች ቤተሰቦች ወደ ስፍራው እንዳይገቡ ተከልክለዋል።

ፔሩ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ከሚያመርቱ አገራት ዋናዋ ናት። በዓመት ከ100 ቶን በላይ ወርቅ ይመረታል። ይህም በመላው ዓለም ጥቅም ላይ ከሚውለው ወርቅ 4 በመቶው ነው።

ባለፈው ቅዳሜ የተነሳው የእሳት አደጋ በዓመታት ውስጥ ከገጠሙ አደጋዎች የከፋው እንደሆነ ተገልጿል።

በአጠቃላይ በአገሪቱ የማዕድን ዘርፍ በዓመት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሞታሉ።