ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል በፍልስጤማውያን እስረኞች ላይ "የተደራጀ እና ሰፊ መንግሥታዊ የስቅይት ፖሊሲ" እየተገበረች መሆኑን የተመድ ኮሚቴ ገለጸ
እስራኤል "በተጨባጭ የሚታይ የተደራጀ እና ሰፊ መንግሥታዊ የስቅይት ፖሊሲ" እየተገበረች ስለመሆኑ ማስረጃ ማግኘቱን የተባበሩት መንግሥታት የባለሙያዎች ኮሚቴ አስታወቀ። ኮሚቴው፤ እስራኤል በእስር ላይ ያሉ ፍልስጤማውያን ላይ የምትፈጽማቸው 'የስቅይት ተግባራት'፤ "ጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል" ተብለው የሚፈረጁ እንደሆኑ ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
በእስራኤል ላይ ይህንን ውንጀላ ያቀረበው 10 ገለልተኛ ባለሙያዎችን የያዘው የጸረ ስቅይት ኮሚቴ (Committee against Torture) ነው።
ኮሚቴው፤ የጸረ ስቅይት ስምምነት ፈራሚ አገራትን የአተገባበር ሁኔታ በተመለከተ በየጊዜው መደበኛ ግምገማ ያካሂዳል። ግምገማው የሚካሄደው ከአገራቱ መንግሥታት እና ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ቡድኖች የሚቀርቡ የምስክርነት ቃሎችን በመቀበል ነው።
ኮሚቴው፤ የእስራኤልን የጸረ ስቅይት ስምምነት ትግበራ ግምገማ ባደረገበት ወቅት የእስራኤል እና የፍልስጤም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ቡድኖች በአገሪቱ ማቆያ ማዕከላት ውስጥ ስላለው አሰቃቂ ሁኔታ ዝርዝር ገለጻ ሰጥተዋል።
በቡድኖቹ ገለጻ መሰረት፤ በመስከረም 2016 ዓ.ም. ከተፈጸመው የሀማስ ጥቃት ወዲህ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ታስረዋል።
እስራኤል፤ የማቆያ ማዕከላት አስተዳደር እንዲሁም "ሕገ ወጥ ተዋጊዎች" በሚል ስያሜ የሚጠሩት የጦርነት እስረኛ ተብለው መፈረጅ የማይችሉ ተጠርጣሪዎችን የተመለከቱ ሕግጋት አሏት። በእነዚህ ሕግጋት መሰረት፤ በዚህ መልኩ የሚታሰሩ ሰዎችን ለረዥም ጊዜ ማሰር እና ጠበቃ ወይም የቤተሰብ አባል እንዳያገኙ ማድረግ ይቻላል።
በርካታ ፍልስጤማውያን የቤተሰብ አባሎቻቸው በእስር ላይ መሆናቸውን እንኳን ለማወቅ እንኳ ወራትን እንደሚጠብቁ መናገራቸውን ኮሚቴው አስታውቋል። ይህ ድርጊት "አስገድዶ መሰወር" ተብሎ ሊፈረጅ እንደሚችል በመንግሥታቱ ድርጅት የተመሰረተው ኮሚቴ ገልጿል።
ኮሚቴው በተለይም እስራኤል ሕገ ወጥ ተዋጊዎችን የተመለከተውን ሕጓን፤ ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች እና አረጋውያንን ጨምሮ በርካታ ፍልስጤማውያንን ለማሰር እንደምትጠቀምበት መገለጹን ተችቷል።
ትናንት ይፋ የተደረገው የኮሚቴው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ ከፍልስጤማውያኑ መታሰር በላይ አስከፊ የሆነው በማቆያ ማዕከላቱ ውስጥ አለ የተባለው ሁኔታ ነው።
ፍልስጤማውያን በመደበኛ ሁኔታ ምግብ እና ውሃ እንደሚከለከሉ እንዲሁም ከፍተኛ ድብደባ፣ የውሾች ጥቃት፣ በኤሌክትሪክ ሾክ መደረግ፣ በውሃ መታፈን እና ወሲባዊ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ማስረጃዎች ጠቁመዋል። የተወሰኑት ታሳሪዎች እጅ እና እግራቸው በቋሚነት እንደሚታሰር፣ መጸዳጃ ቤት መጠቀም እንደሚከለከሉ እንዲሁም ዳይፐር እንዲለብሱ እንደሚገደዱ ተገልጿል።
የጸረ ስቅይት ኮሚቴው፤ ይህ ዓይነቱ የእስር ሁኔታ "የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል" ብሎ መፈረጅ እንደሚቻል ደምድሟል። "በተጨባጭ የሚታየው" የእስራኤል "የተደራጀ እና ሰፊ መንግሥታዊ የስቅይት ፖሊሲ"፤ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ከሚካተቱ ድርጊቶች አንዱ እንደሆነም አስታውቋል።
እስራኤል፤ በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸመች ስለመሆኑ የቀረቡባትን ተደጋጋሚ ውንጀላዎች በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።
ከጸረ ስቅይት ኮሚቴው አባላት አንዱ የሆኑት የዴንማርክ ዜጋው ፒተር ቬደል ኬሲንግ፤ እርሱ እና ባልደረቦቹ በሰሟቸው ነገሮች "እጅጉን መደንገጣቸውን" ተናግሯል። በእስራኤል ላይ የሚቀርቡትን የስቅይት ውንጀላዎች በተመለከተ ምርመራ ወይም ክስ አለመካሄዱ እጅጉን እንዳሳሰባቸውም ገልጿል።
እስራኤል በእነዚህ ውንጀላዎች ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንድታስጀምር እንዲሁም ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን ጨምሮ ድርጊቱን የፈጸሙ ሰዎችን ተጠያቂ እንድታደርግ የኮሚቴው አባላት ጥሪ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት አድሏዊ ነው የሚል ክስ ለረዥም ጊዜ ስታሰማ የቆየችው እስራኤል፤ የኮሚቴውን ግኝቶች በተመለከተ ይፋዊ አስተያየት አልሰጠችም። ነገር ግን ኮሚቴው ምስክርነቶችን በሰማበት ወቅት የተገኙት በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር ዳንኤል ሜሮን፤ የቀረቡትን የስቅይት ውንጀላዎች "ሐሰተኛ መረጃ" ሲሉ አጣጥለዋቸዋል።