የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምንድን ነው? አሜሪካስ ምን ትፈልጋለች?

አሜሪካ እና ኢራን ከዓመታት በኋላ በኒውክሌር ዙርያ የሚደረገውን የመጀመሪያ ዙር ውይይት ቅዳሜ ዕለት አካሂደዋል።

ይህንን በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ዙርያ የተደረገ የመጀመርያ ደረጃ ውይይት "ገንቢ" እንደነበር ሁለቱም አገራት ገልጸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ እአአ በ 2018 ኢራን እና የዓለም ኃያላን መንግሥታት ተፈራርመውት ከነበረው የኒውክሌር ስምምነት አሜሪካን አስወጥተው የኢኮኖሚ ማዕቀብን በመጫናቸው ኢራን ተቆጥታ ነበር።

ትራምፕ ይህ ድርድር የማይሳካ ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።

ኢራን ለምን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዲኖራት አይፈቀድም?

ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሲቪል ዓላማ ብቻ የታቀደ ነው ትላለች።

የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለማምረት እየሞከርኩ አይደለም ብትልም፣ በርካታ ኃያላን አገራት እንዲሁም የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት (IAEA) እርግጠኛ መሆን አልቻሉም።

በተለይ ደግሞ የአገራቱን እና የተቋሙን ጥርጣሬ ያጠናከረው በ2002 አገሪቱ ሚስጥራዊ የኒውክሌር ማምረቻ ቦታ እንዳላት መታወቁ ነው።

ይህም ኢራን እና ሌሎች አገራት የተፈራረሙትን የኒውክሌር ቁጥጥር ስምምነት (NPT) እንዲፈርስ ምክንያት ሆኗል።

የኒውክሌር ቁጥጥር ስምምነት አገራት ወታደራዊ ያልሆኑ የኒውክሌር ቴክኖሎጂዎችን ለመድኃኒት፣ ግብርና እና ኢነርጂ እንዲጠቀሙ የሚፈቅድ ሲሆን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማምረትን ግን ይከለክላል።

የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምን ያህል የበለፀገ ነው?

እአአ በ2018 አሜሪካ ከኒውክሌር ስምምነት ራሷን ካወጣች በኋላ፣ ኢራን ማዕቀቦች ዳግም መጣላቸውን ተከትሎ ቁልፍ የስምምነቱን ነጥቦች ጥሳለች።

ኢራን በስምምነቱ ተከልክው የነበሩ እና ዩራኒየም ለማበልጸግ የሚረዱ በሺዎች የሚቆጠሩ የተሻሻሉ የማጣርያ ማሽኖችን ገጥማለች።

የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ወደ 90 በመቶ ተጣርቶ የበለፀገ ዩራኒየም ይፈልጋሉ።

በኢራን እና በኃያላን አገራቱ መካከል ተደርሶ በነበረው ስምምነት መሠረት ኢራን እስከ 3.67 በመቶ ብቻ የበለፀገ 300 ኪሎ ግራም ዩራኒየም እንዲኖራት ተፈቀዶላታል።

ይህም ለሲቪል ኒውክሌር ኃይል እና ለምርምር ዓላማዎች በቂ ቢሆንም የኒውክሌር ቦምቦች ማምረት ግን አያስችላትም።

እአአ በመጋቢት 2025 ዓለም አቀፉ ተቆጣጣሪ ድርጅት ኢራን 275 ኪሎ ግራም ዩራኒየም እንዳላት ገልጿል።

ይህም ወደ 60 በመቶ የተጣራ እንደሆነ ይፋ ሆኗል።

ኢራን ዩራኒየምን የበለጠ ካበለፀገች በንድፈ ሀሳብ ደረጃ በርከት ያሉ የጦር መሳሪያዎችን ለመስራት ይበቃታል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢራን ያላትን ዩራኒየም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ጦር መሳሪያ ልትቀይረው እንደምትችል ያምናሉ።

ሆኖም ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመስራት ከአንድ ዓመት እስከ 18 ወር እንደሚፈጅባትም ተናግረዋል።

አንዳንድ ባለሙያዎች "ድፍድፍ" ዩራኒየም በስድስት ወር ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ኒውክሌር መሳርያ ሊገነባ ይችላል በማለት ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ትራምፕ ከቀደመው የኒውክሌር ስምምነት ለምን አወጡ?

የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ቦምብ ለማምረት እየተጠቀመበችበት ነው በሚል ጥርጣሬ እአአ ከ2010 ጀምሮ ሰፊ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥለዋል።

ማዕቀቡ ኢራን ለዓለም አቀፍ ገበያ ነዳጅ እንዳትሸጥ ያደረገ ሲሆን፣ የአገሪቱን 100 ቢሊዮን ዶላር ሀብትም እንዳይንቀሳቀስ አግዷል።

በዚህም የተነሳ ኢራን ኢኮኖሚዋ ሲንኮታኮት፣የመገበያያ ገንዘቧ በከፍተኛ ደረጃ በመውደቁ የዋጋ ንረት ተከስቷል።

እአአ በ 2015 ኢራን እና ስድስት የዓለም ኃያላን አገራት መካከል ከዓመታት ድርድር በኋላ ከስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

ይህ በአሜሪካ፣ቻይና፣ፈረንሳይ፣ሩሲያ፣ጀርመን፣እንግሊዝ እና ኢራን መካከል የተፈረመው ስምምነት መሰረት በኒውክሌር መርሃ ግብሯ እንድትሰራ የተፈቀደላትን ከመገደቡ በተጨማሪ ዓለም አቀፉ ተቆጣጣሪ ተቋም ሁሉንም የኢራን የኒውክሌር ተቋማት እንዲመለከት አጠራጣሪ ስፍራዎችን ደግሞ እንዲፈትሽ ይፈቅዳል።

በምላሹም አገራቱ ማዕቀቡን ለማንሳት ተስማምተዋል።

ይህ ስምምነት እስከ 15 ዓመታት እንዲቆይ ታስቦ የነበረ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ የተጣሉት ገደቦች ተግባራዊ መሆን አይችሉም።

ዶናልድ ትራምፕ እአአ በ 2018 ወደ ሥልጣን ሲመጡ የስምምነቱ ቁልፍ ምሰሶ የነበረችውን አሜሪካን ከስምምነቱ አስወጡ።

በወቅቱ ስምምነቱ ቋሚ አይደለም እንዲሁም የኢራንን የባሊስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራምን እና ሌሎች ጉዳዮችን የማይመለከት በመሆኑ "መጥፎ ስምምነት" ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።

ትራምፕ አዲስ እና ሰፊ ስምምነት ከኢራን ጋር እንዲደረስ ለማስገደድ በሚል ማዕቀቦችን በድጋሚ ጥለዋል።

የትራምፕ ውሳኔ ስምምነቱን በሚቃወሙት የአሜሪካ ቀጠናዊ አጋሮች በተለይም የእስራኤል ተጽዕኖ አለበት።

ኢራን አሁንም በድብቅ የኒውክሌር መርሃ ግብሯን እያካሄደች መሆኑን እስራኤል ትገልጻለች።

አክላም ኢራን ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን ለማጠናከር ያገኘችውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የማዕቀብ እፎይታ ልትጠቀም ትችላለች ስትል አስጠንቅቃለች።

አሜሪካ እና እስራኤል ምን ይፈልጋሉ?

ትራምፕ ከኢራን ጋር ድርድር እንደሚያደርጉ ሲገልጹ እስራኤል መገረሟን መሸሸግ አልቻለችም።

ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም አገራቸው ካደረገችው ስምምነት "የተሻለ" ስምምነት እንደሚያደርጉ ሲናገሩ ነበር።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ኢራን አዲስ ስምምነት ካላደረገች "ጥቃት ይጠብቃታል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ማይክ ዋልትዝ እንዳሉት ትራምፕ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር "ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ" እንደሚፈልጉ ገልፀው "ማበልጸጉም ቢሆን፣ የጦር መሣሪያ መታጠቁም፣ የስትራቴጂካዊ ሚሳኤል ፕሮግራሟ [መፍረስ አለበት]" ብለዋል።

ምንም እንኳን ትራምፕ "ቀጥታ ድርድር" እንደሚኖር ቢናገሩም የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በኦማን የሚደረገው ድርድር ቀጥተኛ ያልሆነ ነው ብለዋል።

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን ገልፀው ነገር ግን ትራምፕ በመጀመሪያ ምንም ዓይነት "ወታደራዊ አማራጭ" ሊኖር እንደማይችል መስማማት አለባቸው ብለዋል ።

ትራምፕ ከኢራን ጋር ስለሚደረግ ድርድር ከተናገሩ በኋላ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድርድሩ እንዳሉት ተቀባይነት የሚኖረው ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለማጥፋት ስትስማማ ነው ብለዋል።

ያ ማለት አሉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር "ወደ ውስጥ ገብተን፣ ተቋማቶቹን ስናወድም እና በአሜሪካ ቁጥጥር እና አስፈጻሚነት ሁሉንም መሳርያዎች ስናፈራርስ ነው።"

የእስራኤል ትልቁ ስጋት ትራምፕ እንደ ዲፕሎማሲያዊ ድል ከኢራን የሚቀርብን የአጭር ጊዜ ስምምነትን ይቀበላሉ የሚል ነው።

እስራኤል ቀደም ሲል በነበረው የኃያላን አገራት ስምምነት ውስጥ ራሷን ያላሳተፈች ሲሆን፣ ምንም እንኳ ምንም አይነት ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ባይቀርብበትም የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አላት ተብሎ ይገመታል።

አሜሪካ እና እስራኤል ኢራንን ሊያጠቁ ይችላሉ?

አሜሪካም ሆነች እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር መሠረተ ልማትን በቦምብ ለመደብደብ ወታደራዊ አቅም አላቸው።

ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ የሚያስከትለው ውጤት እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል ውስብስብ እና አደገኛ ነው።

የኢራን ቁልፍ የሆኑ የኒውክሌር ተቋማት ከመሬት በታች የተቀበሩ በመሆናቸው፣ በጣም ግዙፍ ቦምቦች ብቻ ናቸው ሊደርሱባቸው የሚችሉት።

ምንም እንኳ እነዚህን ቦምቦች አሜሪካ የታጠቀች ቢሆንም እስራኤል ግን ይኑራት አይኑራት አይታወቅም።

ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ ኢራን ከሞላ ጎደል በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ ተቋማትን በማጥቃት እንዲሁም ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ ራሷን ልትከላከል ትችላለች።

ለዚህ አይነት ተግባር ዩናይትድ ስቴትስ በባህረ ሰላጤው ላይ ያለውን የጦር ሠፈሯን እንዲሁም የአውሮፕላን ተሸካሚዎቿን መጠቀም ያስፈልጋታል።

ነገር ግን ትልቁን የአሜሪካ አየር ማረፊያ የምታስተናግደው ኳታር የሚደርስባትን አጸፋ በመስጋት ብቻ ኢራንን ለማጥቃት ላትስማማ ትችላለች።