“ስለሞት ሁልጊዜም አስባለሁ” ተዋናይ ኪያኑ ሪቭዝ

ብዙዎቻችን ይህችን ዓለም ጥለናት እንደምናልፍ ብናውቅም ስለሞታችን ማሰብ አንፈልግም።

የሞት ሃሳብንም “ኧረ እንዲያው በሩቁ” የምንል ጥቂቶች አይደለንም።

እንደ ሜትሪክስ በተሰኙ ተከታታይ ፊልሞቹ ታዋቂነትን ያተረፈው ካናዳዊው ተዋናይ ኪያኑ ሪቭዝ ከዚህ ለየት ያለ ነው።

“አሁን 59 ዓመቴ ነው እናም ስለ ሞት ሁልጊዜ አስባለሁ” ሲል ስመ ጥሩው የሆሊውድ ተዋናይ ኪያኑ ሪቭዝ ለቢቢሲ ተናግሯል።

አክሎም “ይሄ ጥሩ ነገር ነው” ብሏል።

“ተስፋ የማደርገው ስለሞት ማሰብ ሸባ እንዳያደርገን ነው። ነገር ግን ስለምንተነፍሳት እስትንፋስ ውድ መሆን እንድናስብ እንዲሁም ከሰዎች ጋር ስላለን እና ስለሚኖሩን ግንኙነቶች እንድናደንቅ እንዲያነቃን ነው” ሲልም ተዋናዩ ያስረዳል።

ቢቢሲ ከኪያኑ ጋር ስለ ሞት እና ሕይወት ውድነት ሊያወራ የተቀመጠውም አዲስ እና የመጀመሪያ መጽሐፉን በተመለከተ ባናገረው ወቅት ነው።

መጽሐፉ ከብሪታንያው የሳይንስ ልቦለድ ደራሲ ቻይና ሚየቪል ጋር በጋራ የተጻፈ ሲሆን፣ መሞት ስለሚፈልግ የማይሞት ተዋጊ ሕይወትን የሚቃኝ ነው።

ኪያኑ ከተዋናይነቱ በተጨማሪ ዶግስታር የተሰኘ የሙዚቃ ባንድ ያለው ሲሆን፣ ከቃለ መጠይቁ አንድ ቀን ቀደም ብሎም በዩናይትድ ኪንግደም ማንችስተር ከተማ ውስጥ ተጫውተው ነበር።

ኪያኑ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው የ30 ደቂቃም ቆይታ ስለ አዲሱ ልቦለድ መጽሐፉ ያለውን ፍቅር ገልጿል። ‘ኤልስዌር’ የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ መጽሐፍ መነሻው እጅግ ስኬታማ ከሆነው ከኪያኑ በርሰርከር ከተሰኘው በሥዕሎች ከተሞላው የኮሚክ መጽሐፍ ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት የወጣው እና ሥዕሎችን በዋናነት የያዘው ይህ ‘ኮሚክ’ በኔትፍሊክስ አማካኝነት በካርቱን (አኒሜሽን) ፊልም ሊሠራ ታቅዷል።

ተዋናዩ በጋራ በተጻፈው አዲሱ የልቦለድ ሥራ ላይ የራሱን ሚና ዝቅ አድርጎ ነው የሚመለከተው።

“ልቦለድ አልጻፍኩም፤ ቻይና ነው የጻፈው” ይላል።

ቻይና በበኩሉ ይህንን የማይቀበለው ሲሆን፣ “የኪያኑ ጥንቃቄ የተሞላበት እሳቤ እንዲሁም ሥራዎች ባይካተቱ ኖሮ መጽሐፉ አይኖርም ነበር” ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።

በመጽሐፉ ላይ ያለው ዋነኛ ገጸ ባህርይ ቢ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ቢ ረዥም ጥቁር ፀጉር ያለው ሲሆን፣ አካላዊ ሁኔታውም ከተዋናዩ ኪያኑ ጋር ተመሳሳይነት አለው።

የኮሚክ መጽሐፉም መጀመሪያ ሲወጣ ገጸ ባህርዩ በግል ሕይወቱ በሚያጋጥመው ፈታኝ ሁኔታዎች ጭምር ከኪያኑ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው አንዳንድ አድናቂዎቹ ጠቁመው ነበር።

ኪያኑ በጣም የሚወዳቸውን ሰዎች በሞት ተነጥቋል። ሴት ጓደኛው፣ ሞታ የተወለደች ልጃቸውን፣ እና የልብ ባልንጀራውን ጨምሮ ሌሎች የሚሳሳላቸውን ሰዎችን አጥቷል።

መጽሐፉ ላይ ከተሳለው ገጸ ባህርይ ተመሳሳይ ቢሆኑም የሚለያያቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ገጸ ባህርዩ ቢ፣ 80 ሺህ ዓመታትን በዚህች ዓለም ላይ የኖረ ሲሆን፣ ግማሽ ሟች ግማሽ ደግሞ አምላክ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ “ጠበኛ እንዲሆን የተረገመ” ሲሆን፣ ይህም በሰላማዊነቱ ከሚታወቀው ኪያኑ ጋር ጭራሽ አይገናኝም።

በለስላሳ ባህርዩ የሚታወቀው ተዋናዩ በሆሊውድ ካሉ በመልካም ስብዕናው በተደጋጋሚ ከሚነሱት አንዱ ነው። በአንጻሩ ቢ ሰዎች ደረታቸው ላይ ገብቶ እጆቻቸውን መገንጠል እንዲሁም ጭንቅላታቸውን መቅላት የሚችል እንደሆነ ኪያኑ ይናገራል።

ለዚህም መነሻው “በሠራኋቸው በድርጊት የተሞሉ (አክሽን) ፊልሞች ተጽእኖ ይመስለኛል” ሲልም በተከታታዮቹ ስፒድ እና ጆን ዊክ ፊልሞች ላይ የተወነው ኪያኑ ያስረዳል።

የኮሚክ መጽሐፉ ሲወጣ በዘርፉ ባሉ ገምጋሚዎች አዎንታዊ ምላሽ የተሰጠው ሲሆን፣ ኪያኑ እና ቻይናም በዚህ መጽሐፍ ያንኑ ስኬት ለመድገም ተስፋን ሰንቀዋል።

መጽሐፉ መግቢያዎቹ ገጾች ላይ የተኩስ ልውውጥን ያካተተ ሲሆን፣ ደም አፋሳሽ ጭብጦችን ስለመያዙ ምንም ጥርጥር የለውም።

በቴሌቪዥን መስኮት የሚታዩ እና በመጻህፍት ላይ የሰፈሩ ደም መፋሰሶች ከገሃዱ ዓለም ጋር ስላላቸው አወዛጋቢ ግንኙነት ቢቢሲ ኪያኑን ጠይቆታል።

ኪያኑ ይህንን የማይስማማበት ሲሆን “ሰዎች ብርዝርክርን ካነበቡ በኋላ መጽሐፉ ላይ እንዳለው የሰዎችን ክንድ መገንጠል እንዲሁም ራስ መቁረጥ እንደማይጀምሩ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲል ተናግሯል።

“መጽሐፉ በውስጡ የፍቅር ታሪክን ይዟል። አንብበው ምንናልባት በሕይወታቸው ፍቅር ከሌላቸው ፍቅር ሊያገኙ እንደሚችሉ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል።

ቻይናም በስክሪኖች ላይ በሚታዩ ደም መፋሰሶች እና በገሃዱ ዓለም መካከል ግንኙነት አለው የሚለውን እሳቤ በጽኑ ይቃወማል። ማምለጫ መንገድም እንደሆነ ነው የሚከራከረው።

ሙሉ ምናባዊ ዓለምን በዚህ መጽሐፉ ያሰፈረው ኪያኑ ከእውነተኛው ዓለም ለማምለጥ እየሞከረ ይሆን?

“በምናብ ሌላ ዓለምን የመፍጠር እሳቤ በሆነ መንገድ ያጽናናል” ሲል ተዋናዩ ይናገራል።

“ከህመም የሚወለድ የፈጠራ ሥራም ጠንካራ ነው” ይላል።

መፍጠር እና ለሰዎች ማጋራት ታላቅ ነገር ነው የሚለው ኪያኑ “ሰዎች የምንነግራቸውን ታሪኮች እንደሚወዱ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ።

በርካቶች መጽሐፉን ወደዉት፣ የተሳካ ከሆነ ኪያኑ ከሽያጩ የሚገኘውን ገቢ ምን ያደርግበት ይሆን?

ተዋናዩ በለጋስነቱ የሚታወቀስ ሲሆን፣ የንብረትም ሆነ የገንዘብ ባለቤት መሆን እንደማይወድ በርካታ ጊዜ ተጽፏል።

ኪያኑም ይህንን የማያምንበት ሲሆን “በእርግጠኝነት ሁሉንም ነገር ዝም ብሎ የሚሰጥ ሰው አይደለሁም። አንዳንድ ነገሮች ሲኖሩኝ ደስ ይለኛል” ብሏል።