ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን ለኢትዮጵያ ድሮን መላኳን አሜሪካ ገለጸች
ኢራን ሞሃጀር-6 የተባሉ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች (ድሮን) ለኢትዮጵያ ልካ እንደነበረ አሜሪካ ገለጸች።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ቃል አቀባይ ትናንት ማክሰኞ 8/2015 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ፤ ኢስላሚክ ሪፐብሊክ ኢራን ከአንድ ዓመት በፊት ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን ለኢትዮጵያ መላኳን ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ቬዳንተ ፓቴል እንዳሉት፤ ኢራን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በዩክሬን ላይ ወረራ ለፈጸመችው ሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ልካለች።
“ኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለሁለቱ አገራት የላከችው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ምክረ ሐሳብ ቁጥር 2231 በመተላለፍ ነው” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ጨምረው እንደተናገሩት ኢራን ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች ወደ ሩሲያ መላኳን አሜሪካ ለተባበሩት መንግሥታት አስታውቃለች።
በጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ሐሳብ 2231 መሠረት ኢራን በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቀድማ ፍቃድ ካላገኘች በቀር የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ ግብዓቶችን እና ቁሶችን ወደ ሌሎች አገራት ማስተላለፍ አትችልም ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ከዚህ በተጨማሪም ከሰው አልባ አውሮፕላኖቹ አንዱ አምራች የሆነው ኮድስ አቪዬሽን በውሳኔ ሐሳቡ መሠረት ንብረቱ እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል ብለዋል።
“ሁሉም አገራት የዚህ ኩባንያ ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ ማገድ ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል ቬዳንተ ፓቴል።
በሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት የፌደራሉ መንግሥት ኢራን፣ ቱርክ እና ቻይና ሠራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጥቅም ላይ ማዋሉን የሚገልጹ በርካታ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይቷል።
ምንም እንኳን ቢቢሲ በዚህ ጦርነት የትኞቹ ድሮችን ለየትኛውን ወታደራዊ ተልዕኮ ጥቅም ላይ ውለዋል የሚለውን ማረጋገጥ ባይችልም፣ ጠቅላይ ሚንሰትር ዐቢይ አሕመድ ግን ድሮን በዚህ ጦርነት ጥቅም ላይ እንደዋለ አመላክተው ነበር።
የአገሪቱ አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄነራል ይልማ መርዳሳም ሕዳር/2013 ዓ. ም በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በቀረቡበት ወቅት ኢትዮጵያ በዚህ በጦርነት ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቅም ላይ እንዳዋለች አረጋግጠው ነበር።
ይሁን እንጂ የአየር ኃይሉ አዛዡ፤ ጦሩ የትኞቹን ሰው አልባ አውሮፕላኖች እየተጠቀመ እንደሆነ ያሉት ነገር የለም።
ሞሃጀር-6
ሞሃጀር-6 በስለላ፣ በቅኝት እና የጥቃት ዒላማዎችን ለይቶ ጥቃት የመፈጸም ተልዕኮዎችን በማሳካት የተዋጣለት ሰው አልባ አውሮፕላን ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ቃል አቀባዩ በኮድስ አቪዬሽን የሚመረተው ሞሃጀር-6 አየር ላይ ከወጣ እስከ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት መሸፈን እንደሚችል ተናግረዋል።
ሞሃጀር-6 እስከ 40 ኪሎ ግራም ክብደት ጭኖ 18ሺህ ጫማ ከፍታ ድረስ ተነስቶ ለ12 ሰዓታት አየር ላይ ሊቆይ ይችላል።
ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ጥቅም ላይ አውላቸዋለች ከሚባሉት ሰው አልባ አውሮፕላኖች መካከል ሌላኛው ቱርክ ሠራሹ ባይራክታር ቲቢ-2 ነው።
ባይካር ዲፌንስ የሚያመርተው ይህ ድሮን እስከ 150 ኪሎ ግራም ክብደት ይዞ መብረር የሚችል ሲሆን እስከ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ሆኖ ድሮኑን መቆጣጠር ይቻላል።
በአምራቹ ድረ ገጽ ላይ እንደሰፈረው የዚህ ድሮን ክንፍ ርዝመት 12 ሜትር፣ ቁመቱ 2.2 ሜትር፣ ርዝመቱ 6.5 ሜትር ሲሆን 300 ሊትር ነዳጅ የመያዝ አቅም አለው።
ይህ ድሮን የሰው ቁጥጥር ሳይደረግበት በራሱ ሥርዓት መነሳት እና ማረፍ የሚችል ሲሆን ከ18 ሺህ አስከ 27 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ተልዕኮውን ይወጣል።