ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሰሜን አሜሪካ በቅዝቃዜ ምክንያት የበርካታ ሰዎች ሕይወት አለፈ
በአሜሪካ እና ካናዳ እየጨመረ ካለው ከባድ የአርክቲክ በረዶ ጋር በተያያዘ ቢያንስ የ38 ሰዎች ሕይወት አልፏል።
ባለሥልጣናቱ እንደገለጹት በመላው አሜሪካ 34 ሰዎች ሞተዋል። ክፉኛ የተጠቃችው አካባቢ በኒው ዮርክ ግዛት የምትገኘው ባፈሎ ከተማ ናት።
በካናዳዋ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ግዛት ሜሪት ከተማ አቅራቢያ በረዷማ መንገድ አውቶብስ አንሽራትቶ አራት ሰዎች ሞተዋል።
የክረምቱ ማዕበል ስፋት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሏል። በዚህም ከካናዳ እስከ ሪዮ ግራንዴ በደቡብ በኩል ተዘርግቷል።
የአየር ትንበያ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ቅዝቃዜው በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ቢቀንስም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ሰዎች ጉዞ እንዳያደርጉ መክረዋል።
አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ያጋጠመው የኃይል መቆራረጥ መስተካከሉ ተገልጿል።
በርካታ በረራዎች በመሰረዛቸው ብዙዎች ለፈረንጆች ገና በዓል ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዳይሄዱ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
እሁድ ዕለት ከ55 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አሜሪካውያን ቀዝቃዛ አየር እንደሚኖር ማስጠንቀቂያዎች ደርሷቸዋል።
የከባቢ አየር ግፊት የክረምት አውሎ ነፋስ ከባድ በረዶ እና ንፋስ በማስከተሉ በመላው አሜሪካ ጉዞዎች ተስተጓጉለዋል።
የበፈሎ ነዋሪ ሆኑት የኒው ዮርክ ገዥ ካቲ ሆቹል "ይህ ለበፈሎ እጅግ አውዳሚው አውሎ ንፋስ ሆኖ በታሪክ ይመዘገባል” ብለዋል።
እሑድ ማምሻውን ለጋዜጠኞች ሲናገሩም “ወደ ጦርነት ቀጠና እንደመሄድ ነው። በመንገዱ ዳር ያሉትን ተሽከርካሪዎች አስደንጋጭ ናቸው” ብለዋል ።
ነዋሪዎቹ “ለሕይወት አስጊ በጣም አደገኛ ሁኔታ” አጋጥሟቸዋል። በአካባቢው ያለ ማንኛውም ሰው በቤት ውስጥ መቆየት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
በኤሪ ካውንቲ 12 ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን አንዳንዶቹ በመኪናዎች ውስጥ ሞተው ተገኝተዋል።
በቨርሞንት፣ ኦሃዮ፣ ሚዙሪ፣ ዊስኮንሲን፣ ካንሳስ እና ኮሎራዶም ከለው ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ጋር በተያያዘ ሞት ተዘግቧል።
የምዕራብ አሜሪካ ሞንታና ግዛት በቅዝቃዜው ክፉኛ የተጠቃች ሲሆን የሙቀት መጠኑ ወደ -45 ዲግሪ ወርዷል።
በካናዳ ደግሞ የኦንታርዮ እና የኩቤክ ግዛቶች አውሎ ነፋሱን እያስተናገዱ ነው።
በኩቤክ ወደ 120,000 የሚጠጉ ሰዎች እሑድ ዕለት መብራት አልነበራቸውም። አንዳንድ ቤቶችን መብራት ለመጠገን ጥቂት ቀናትን ሊወስድባቸው እንደሚችል ባለስልጣናት ተናግረዋል።