በፍኖተ ሰላም ከተማ በቀናት ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ ገበያ ውስጥ በፈነዳ ቦምብ 27 ሰዎች ተጎዱ

በአማራ ክልል የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ፍኖተ ሰላም ከተማ በሁለት ቀናት ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ ላይ በፈነዳ ቦምብ 27 ሰዎች መጎዳታቸውን የፍኖተ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በከተማዋ በሚገኝ የገበያ ስፍራ ላይ ባጋጠመው በዚህ የቦምብ ፍንዳታ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ግብይት ላይ የነበሩ ንጹሃን መሆናቸው ተገልጿል።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት ኃይሎችን ተደጋጋሚ ግጭት እንዲሁም የድሮን ጥቃት ባስተናገደችው ፍኖተ ሰላም ከተማ፤ የቦምብ ፍንዳታው ያገጠመው ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 28/2016 ዓ.ም ነው።

ፍንዳታው የተፈጸመው የከተማዋ እና አጎራባች ወረዳ ነዋሪዎች በየሳምንቱ ቅዳሜ በሚገበያዩበት ሳምንታዊ የገበያ ስፍራ ላይ መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የመንግሥት ኃላፊዎች “የቦምንብ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል” የሚል ስጋት መኖሩን በመጥቀስ ነዋሪዎች እንዳይሰበሰቡ ሲናገሩ እንደነበር ያስታወሱት ነዋሪው፤ በዕለቱም የፀጥታ ኃይሎች በገበያ ስፍራው ላይ “ፓትሮል” እያደረጉ እንደነበር አስረድተዋል። ይሁንና የፀጥታ ኃይሎች ከስፍራው ከሄዱ በኋላ የቦንብ ፍንዳታው ማጋጠሙን ተናግረዋል። ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ “እንደማይታወቅ” ነዋሪው አክለዋል።

አስካሁን የክልሉም ሆነ የከተማዋ አስተዳዳሪዎች ፍንዳታውን በመተመለከተ ያሉት ነገር የለም።

በዚህ ጥቃት አደጋ የደረሰባቸው 27 ንጹሃን ሰዎች ከቀኑ አራት እስከ አምስት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ለህክምና ወደ ፍኖተ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል መምጣታቸውን በዕለቱ በሥራ ላይ የነበሩ የሆስፒታሉ ሐኪም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል ስድስት ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን የገለጹት የጤና ባለሙያው፤ ከአንድ ሰው በቀር ሁሉም የደረሰባቸው ጉዳት “ቀላል ሊባል የሚችል” መሆን ጠቅሰዋል።

“ከ27 ሰዎች ውስጥ፤ ዐይናቸው በመጎዳቱ ‘ሪፈር’ የተባሉ አንድ አርሶ አደር አሉ። ሌሎች ታክመው ወደ ቤታቸው የተመለሱም አሉ” ያሉት የቢቢሲ የሆስፒታል ምንጭ፤ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አርሶ አደር ለተጨማሪ ህክምና ወደ ባሕር ዳር ከተማ መላካቸውን ገልጸዋል።

የቅዳሜ ዕለቱ ክስተት በሁለት ቀናት ልዩነት ውስጥ በፍኖተ ሰላም ከተማ የተፈጸመው ሁለተኛው የቦንብ ጥቃት ነው። ሐሙስ መጋቢት 26/2016 ዓ.ም. በከተማዋ በሚገኘው ዳሞት መሰናዶ ቁጥር አንድ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት 32 ተማሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የምዕራብ ጎጃም ዞን አስታውቆ ነበር።

የፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ምክትል ኮማንደር ሙሉዓም ገሰሰን የጠቀሰው የዞኑ መረጃ እንደሚያመለክተው በዚህ ጥቃት ስድስት ተማሪዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፍኖተ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል ባለሙያ እንደሚገልጹት በዕለቱ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ተማሪዎች ቁጥር 24 ናቸው። ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥ ስድስቱ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ባሕር ዳር ከተማ መላካቸው አስታውሰዋል።

በአሁኑ ሰዓት ሐሙስ እና ቅዳሜ ዕለት ባጋጠሙት ፍንዳታዎች ጉዳት የደረሰባቸው “አራት ገደማ” ሰዎች በሆስፒታሉ ህክምና ላይ እንዳሉ የህክምና ባለሙያው አስረድተዋል።

የሐሙስ ዕለቱን ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠረ አንድ ተማሪ በቁጥጥር ስር እንደዋለ እና በድርጊቱ የተሳተፉ ሌሎች አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሠራ መሆኑን ምክትል ኮማንደር ሙሉዓም መናገራቸውን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስታውቆ ነበር።

በቢሲ የቅዳሜ ዕለቱን የቦንብ ጥቃት በተመለከተ ከምዕራብ ጎጃም ዞን እና ፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎች አልተሳኩም።