'ጋዛ እየነደደች ነው': በከባድ የአየር ድብደባ መካከል እስራኤል የጀመረችው የእግረኛ ሠራዊት ጥቃት

ከወደመ ሕንጻ ውስጥ በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቃሬዛ እየወጣች ያለች ታዳጊ ሴት ልጅ በጭንቀት ውስጥ ሆና

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "ኃይለኛ ዘመቻ" ያሉት በጋዛ ሰርጥ መጀመሩን ማረጋገጣቸውን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ከተማ ላይ የምትፈጽመውን ከባድ የአየር ድብደባ አጠናክራለች። የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ በኤክስ ላይ "ጋዛ እየነደደች ነው" ሲሉ አስፍረዋል።

ከአንድ ሳምንት በኋላ ሁለት ዓመት የሚሞላው እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ያለው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ አሁን ተባብሶ ቀጥሏል።

እስራኤል ጋዛን ለመቆጣጠር ባወጣችው ዕቅድ መሠረት ከባድ የአየር ድብደባ እና የእግረኛ ሠራዊት ጥቃት በጋዛ ላይ ከፍታለች።

በዚህም ጋዛ ውስጥ ያሉ ሕንጻዎች በእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች እየወደሙ ሲሆን፣ ይህንንም የእስራአል የመከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ "ጋዛ እየነደደች ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ ባልተጠበቀ ሁኔታ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ሰዎችን ካገተ በኋላ እስራኤል በጋዛ ላይ ከባድ ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።

በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንዳለው ከ60 ሺህ በላይ የጋዛ ነዋሪዎች ተገድለዋል። አሁን የተከፈተው ጥቃት ደግሞ የሚሞቱትን ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምረው ተሰግቷል።

እነዚህ ፎቶግራፎች በጋዛ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በጥቂቱ የሚያሳዩ ናቸው።

የአል-ጋፍሪ ሕንጻን ሲያወድም የሚወጣ ከባድ ጭስ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል የአየር ድብደባ በጋዛ ከተማ የሚገኘውን የአል-ጋፍሪ ሕንጻን ሲያወድም የወጣ ጭስ። ኔታንያሁ የጋዛ ከተማ የሐማስ የመጨረሻዋ ወሳኝ ይዞታ እንደሆነች እና በቁጥጥራቸው ስር ለማስገባት ዝተዋል፤ ነገር ግን ይህ ዕቅዳቸው ዓለም አቀፍ ትችት አስከትሎባቸዋል።
የጋዛ ነዋሪዎች ያላቸውን ይዘው ለመውጣት ከባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኝ የተጨናነቀ ረጅም መንገድ ላይ ሆነው የሚያሳይ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል ባለፈው ወር በጋዛ ላይ ጥቃት መፈጸም ከጀመረች በኋላ ግዛቲቱ ከፍተኛ የጅምላ መፈናቀል ገጥሟታል
የተኛውን ሕጻን ልጁን ታቅፎ ሌላኛውን በጀርባው አዝሎ ከጋዛ በእግሩ ለመውጣት በመጓዝ ላይ ያለ አባት

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአየር ጥቃቱ በቀጠለበት ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ወደ ደቡባዊ ጋዛ ለመጓዝ እየሞከሩ ነው
ረጅም ሕንጻ ተመትቶ አስፈሪ የእሳት ነበልባል እና ጭስ ሲወጣ የሚያሳይ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ሠራዊት ነዋሪዎች ከጋዛ ለቀው እንዲወጡ ካዘዘ በኋላ በርካታ ረጃጅም ሕንጻዎች በአየር ጥቃት ተመትተዋል
በአቧራ እና አሸዋ የተሸፈነ የእስራኤል ወታደራዊ ተሽከርካሪ የድንበር አጥርን ሲያልፍ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በጋዛ ከተማ ላይ ጥቃት የከፈተችው የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እስራኤል ውስጥ ከኔታኒያሁ ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው። የተባበሩት መንግሥታት አጣሪ ኮሚሽን እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ፈጽማለች ብሎ ደምድሟል፤ እስራኤል ግን አስተባብላለች
ደማቅ የሌሊት ልብስ ለብሳ በጀርባዋ እቃ ተሸክማ በሕንጻ ፍርስራሾች ውስጥ የምትራመድ ታዳጊ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አስካሁን 350 ሺህ የሚደርሱ ፍልስጤማውያን አካባቢያቸውን ለቀው መውጣታቸውን የእስራኤል ጦር ኃይል የገመተ ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ግን በጋዛ እንዳሉ ይታመናል
ከፍንዳታ በኋላ የሚወጣ ጥቁት ጭስ እና በዙሪያው የፈራረሱ ሕንጻዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከባዱ የአየር ድብደባ መካሄድ የጀመረው እስራኤል መጠነ ሰፊ የእግረኛ ወረራ እንደምታካሂድ ለረጅም ጊዜ ስታስጠነቅቅ ከቆየች በኋላ ነው። የፍልስጤም ባለሥልጣናት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል
በመኪና፣ በፈረስ በሚጎተት ጋሪ እና በእግር ፍልስጤማውያን ወደ ማዕከላዊ ጋዛ እየተጓዙ ነው። ብዙ እቃ የጫኑ ትናንሽ መኪኖች እና የጭነት ተሽከርካሪዎች በማታ ይታያሉ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, "የእስራኤል ጦር የአል-ራሺድ የባሕር ዳርቻ መንገድን ከጋዛ ለመውጣት ለሚፈልጉ ሲቪሎች ብቸኛው የተፈቀደ መስመር አድርጎ ሰይሟል። ነዋሪዎቹ መጨናነቅ፣ ረጅም የመኪኖች ሰልፍ እና ለብዙ ሰዓታት መዘግየት እንዳለ ይገልጻሉ፣ በርካታ ቤተሰቦች በመንገድ ዳር ቆመው ያሉት የአየር ጥቃቱ በቀጠለበት ጊዜ" ሲል የቢቢሲ ጋዛ ዘጋቢ ራሽዲ አቡአሉፍ ተናግሯል።
የጋዛ ሰርጥ ካርታ