'ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ብቸኛው እንቅፋት ኔታንያሁ ናቸው'- የታጋቾች ቤተሰቦች

የእስራኤላውያን ታጋቾች ቤተሰቦች አደባባይ በመውጣት በጋዛ የሚካሄደው ጦርነት እንዲያበቃ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ መንግሥታቸውን ጠይቀዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሐማስ ታግተው የሚገኙ እስራኤላውያን ቤተሰቦች ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ እና ታጋቾችን ለመመለስ እንዳይቻል "አንደኛው እንቅፋት" ናቸው አሉ።

ዘ ሆስቴጅስ ኤንድ ሚሲንግ ፋሚሊስ ፎረም በማኅበራዊ ሚዲያ ገፁ ላይ ባለፈው ሳምንት እስራኤል በኳታር ላይ የፈጸመችው የአየር ጥቃት የሚያሳየው "ስምምነት ሊደረስ በተቃረበበት ጊዜ ሁሉ ኔታንያሁ እንደሚያከሽፉት ነው" ብሏል።

የቡድኑ አስተያየት የተሰማው ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ የሐማስ መሪዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ መፈፀሟን ተከትሎ ነው።

ሐማስ በጥቃቱ አምስት አባላቱ እና አንድ የኳታር የደህንነት ኃላፊ መገደሉን አስታውቋል።

ቅዳሜ ዕለት ኔታንያኑ የሐማስ አመራሮችን በኳታር ማስወገድ መቻል ታጋቾችን ለማስለቀቅ እና ጦርነቱን ለማስቆም "ዋነኛውን እንቅፋት ማስወገድ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐማስን የተኩስ አቁም በማስተጓጎል እና በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት በማራዘም ከስሰውታል።

እስራኤል ከኳታር ጥቃት በኋላ ዓለም አቀፍ ውግዘት ከደረሰባት በኋላ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ቅዳሜ ዕለት ወደ እስራኤል የሄዱ ሲሆን ከኔታንያሁ ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሏል።

ይሁን እንጂ የታጋቾች ቤተሰቦች የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተያየት ልጆቻችንን "ወደ ቤታቸው ለመመለስ ባለመቻላቸው የሚያቀርቡት ምክንያት ነው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"በኳታር የተፈፀመው ጥቃት ያለምንም ማንገራገር 48 ታጋቾችን ለማስለቀቅ እና ጦርነቱን ለማብቃት አንድ እንቅፋት፣ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፣ እንዳሉ የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

"አሁን ጊዜው ምክንያት እየደረደሩ ስልጣን ላይ ሙጭጭ ብሎ ለመቆየት የሚደረገው ጥረት ማብቂያ ነው።"

ቡድኑ አክሎም የኔታንያሁ "እንቅፋት መሆን"፤ "የ42 ታጋቾችን ሕይወት ዋጋ አስከፍሏል እንዲሁም ብዙ በሕይወት የሚተርፉ ተጨማሪ ታጋቾችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል" ብሏል።

ሩቢዮ ወደ እስራኤል ከማምራታቸው በፊት የዩኤስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኳታር ላይ በተፈጸመው ጥቃት ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልፀው ነገር ግን የአሜሪካ እና የእስራኤል ግንኙነት "በጣም ጠንካራ ነው" ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።

"በዚህ ደስተኛ አለመሆናችን ግልጽ ነው፤ ፕሬዝዳንታችን በዚህ ደስተኛ አልነበሩም።አሁን ወደ ፊት መሄድ እና ቀጥሎ ምን መሆን እንዳለበት ማወቅ አለብን" ብለዋል ሩቢዮ።

አክለውም ዶናልድ ትራምፕ ቅድሚያ የሚሰጡት ሁሉም ታጋቾች እንዲለቀቁ እና የጋዛ ጦርነት እንዲያበቃ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዶሃ የተፈፀመው ጥቃት ኳታር ከአሜሪካ ጋር ለመስራት ያላትን ፍላጎት ያወሳስበዋል ወይ ለሚለው ጥያቄ ሩቢዮ ሲመልሱ "በበርካታ ግንባሮች ጥሩ አጋር ናቸው" ብለዋል።

ኳታር በባሕረ ሰላጤው አካባቢ የአሜሪካ ዋነኛዋ ወዳጅ ናት። በግዛቷ ውስጥም ግዙፍ የአሜሪካ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ይገኛል።

ኳታር በግዛቷ ውስጥ በእስራኤል የተፈጸመውን ጥቃት "የፈሪ ዱላ" እና "ዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ የጣሰ" በማለት አውግዛዋለች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ጥቃቱ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ባቀዱት የሐማስ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ያነጣጠረ "በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ተገቢ ነው" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ የእስራኤል ኃይል በጋዛ ከተማ የሚያደርገውን ጥቃት ተደጋጋሚ የአየር ድብደባዎች በመፈጸም አጠናክሮ ቀጥሏል።

ጦሩ ትልልቅ የመኖሪያ እና የገበያ ሕንጻዎችን በማውደም ወደ ትብያነት ቀይሯቸዋል።

እስራኤል ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን የምድር ዘመቻዋን ለማጠናከር ማሰቧን በሚያመላክት መልኩ በፍጥነት ለቅቀው እንዲወጡ አስጠንቅቃለች።

ነዋሪዎች የእስራኤል ጦር ትምህርት ቤቶችን እና ጊዜያዊ መጠለያዎችን አንዳንዴ ለአጭር ጊዜ ከሚሰጥ ማስጠንቀቂያ በኋላ ጭምር እንደሚያጠቃ ይናገራሉ።

ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ኃይል 250,000 ነዋሪዎች ከተማዋን ለቅቀው ወደ ደቡብ መሄዳቸውን ተናግሯል።

ኔታንያሁ የጋዛ ከተማን ለመውረር ያቀረቡት ዕቅድ ዓለም አቀፍ ውግዘት ያጋጠመው ሲሆን፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ረሃብ መከሰቱ በታወጀበት አካባቢ የሚኖር የወታደራዊ ዘመቻ መጠናከር ሰላማዊ ዜጎችን "ወደ በለጠ ጥልቅ ስቃይ ይከታቸዋል" ብሏል።

መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ሰዎችን ካገተ በኋላ የእስራኤል ጦር በከፈተው ወታደራዊ ዘመቻ 64,605 መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።