ትኩረት ልንሰጠው የሚገባው ከወሊድ በኋላ እናቶችን የሚገጥመው የአእምሮ ጤና እክል

ኤሊ በወለደችበት ወቅት የነበራትን ስሜት ስታስታውስ መጀመሪያ ፈንጠዝያ ነበር ትለለች። ያለምንም ሕመም በቤት ውስጥ ነበር የወለደችው። አዲስ እናት መሆኗ ደግሞ ሌላ ደስታዋን የጨመረው ጉዳይ ነው።

ምንም እንኳ በሦስት ቀናት ውስጥ ጥቂት ሸለብታ ብቻ እንቅልፍ ብታገኝም፣ በኋላ ላይ እንቅልፍ በዓይኗ አልዞር አለ።

"ጥሩ የምገልጽበት መንገድ ቢኖር በሕልሜ ይሁን በእውኔ ያልለየ፣ በቅዠት ውስጥ ሆኖ እንደመራመድ ነው። [ስሜቱ] ደግሞ እየተመላለሰ ይመጣ ነበር" ትላለች።

"ከዚያ በኋላ ልጄን አልጋው ላይ እያለ እንደገደልኩት ተሰማኝ። ባሌ ሲመጣ 'እውነት ነው? ልጄን ገደልኩት' እያልኩ ስጠይቀው አስታውሳለሁ።"

ኤሊ ከወሊድ በኋላ በሚከሰት የበርካታ እናቶችን ሕይወት በሚያመሰቃቅለው የአእምሮ ጤና ችግር (ፖስት ፓርተም ሳይኮሲስ) ነበር የተጠቃችው።

ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የአእምሮ ሕመም ምንድን ነው?

ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የአእምሮ ሕመም (postpartum psychosis) ቀዳሚ ምልክቶች ከሆኑት መካከል እናቲቱ ራሷን መሆን ሲያቅታት ወይንም ከእውነታው እየራቀች ስትሄድ ነው።

ምንም እንኳ አዲስ በወለዱ እናቶች ዘንድ እንቅልፍ ማጣት የተለመደ ቢሆንም፣ ከወሊድ በኋላ በሚከሰት ድብታ የምትጠቃ እናት ግን ሙሉ በሙሉ ከእንቅልፍ ጋር ልትፋታ ትችላለች።

በዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ጤና አገልግሎት መረጃ መሠረት የዚህ አእምሮ ሕመም ምልክቶቹ

  • ቶሎ ቶሎ የሚከሰት የስሜት መለዋወጥ፣
  • መቃዠት፣
  • ምክንያት አልባ የጥፋተኝነት ስሜት፣
  • የሌለ ድምጽ መስማት፣
  • እረፍት ማጣት እንዲሁም
  • ግራ መጋባት ናቸው።

ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የአእምሮ ጤና መታወክ አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፍለገው ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ ሆስፒታል ተኝተው በልዩ ባለሙያ ድጋፍ እና ክትትል ማግኘትን ይጠይቃል።

ዋናው ሊጤን የሚገባው ይላሉ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የአእምሮ ሕመሙ ደረጃ ከፍ ባለ ቁጥር ሕክምናውን የሚከታተሉ ሴቶች ለመዳን ወራትን ሊፈጁ እንደሚችሉ ነው ።

ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የአእምሮ ሕመም መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

ምንም እንኳ ረዥም ዓመት በጉዳዩ ላይ ጥናት እና ምርምር ቢካሄድም የዚህ መንስዔ ይህ ነው ብሎ ማመልከት አልተቻለም።

የሕክምና ባለሙያዎች በወሊድ ወቅት በድንገት የሚከሰት የሆርሞን ለውጥ ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ይህ ለውጥ ከፍ ያለ ግራ መጋባት እና ውዥንብር ሊፈጥር ይችላል።

ነገር ግን ማን በዚህ ሊጠቃ እንደሚችል ለመናገር የሚያስችል ተጨባጭ ማስረጃ የለም።

በደም ምርመራ መለየትም የሚቻል ጉዳይም አይደለም።

ከወሊድ በኋላ በአእምሮ ጤና መቃወስ ከተጠቁ አዲስ እናቶች መካከል ግማሽ ያህሉ ከዚህ በፊት የአእምሮ ጤና እክል ገጥሟቸው አያውቅም።

ስለዚህ የሚያጋጥማቸው ቅዠት ፈጽሞ የማይጠብቁት እና የሚያስፈራ ነው።

ለኤሊ ይህ ዓይነት የአእምሮ ሕመም ፈጣን ነበር።

"ቤት ውስጥ ለሰዓታት በምጥ ላይ እያለሁ ጀምሮኝ ይሆን ስል አስባለሁ፤ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ባለቤቴን መቀስቀስ አልፈለግኩም ነበር" ብላለች።

ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የአእምሮ ሕመም ከወለዱ 1000 እናቶች መካከል ሁለቱን ያጠቃል።

ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ድብታ ግን ከ10 እናቶች አንዷን የሚያጠቃ ሲሆን፣ ይህ ግን (postpartum psychosis) ከዚያ ያነሰ ነው።

ባለሙያዎች በፊት ከሚታሰበው በላይ በርካታ እናቶች በዚህ ሕመም መጠቃታቸውን ያምናሉ።

ለበርካታ ዓመታት ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ድብታ ችላ ተብሎ የነበረ ሲሆን፣ ዶክተሮች ግን ወላጆች ለአእምሮ ጤና የሚሰጡት ዝቅ ያለ ግምት በቂ ድጋፍ እንዳያገኙ እያደረገ ነው ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሚገኝ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ባካሄደው ጥናት ከወሊድ በኋላ በሚከሰት የአእምሮ ሕመም ላይ አሁንም በአዋላጅ ወይንም በአጠቃላይ ዶክተሮች ዘንድ የተሳሳተ እውቀት አለ።

በዚህም የተነሳ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ በመድረስ የእንቅልፍ ክኒን ብቻ እንደሚያዙ በጥናት ተደርሶበታል።

ኤሊ ለተከታታይ ቀናት የእንቅልፍ ማጣት እና ምርጥ እናት ለመሆን የሚደረግ ጫና ሕመሙን እንደሚያባብሰው ትናገራለች።

ከዚህም በተጨማሪ ኤሊ የባይፖላር ሕመም እንዳለባት ማወቋ የበለጠ ጤናዋ አደጋ ውስጥ መሆኑን እንድትረዳ አድርጓታል።

የባይፖላር ዲስኦርደር ሕመም ተጠቂ የሆኑ 25 በመቶ እናቶች የመጀመሪያ ልጃቸውን በሚወልዱበት ወቅት በዚህ አእምሮ ሕመም ሊጠቁ ስለሚችሉ በሆስፒታል ተኝተው ክትትል ሊደረግላቸው እንደሚገባ የካርዲፍ ዩኒቨርስቲ ጥናት ያሳያል።

በካርዲፍ ዩኒቨርስቲ የሥነ አእምሮ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ኢያን ጆንስ በልጅነታቸው ወቅት የአእምሮ ቁስል ወይንም ትራውማ ያለባቸው እናቶች በፖስትፓርተም ሳይኮሲስ የመጠቃታቸው ዕድል ከፍ ይላል ይላሉ።

አክለውም የሆርሞን መጨመር እና ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች ሌሎች ትልቁ ምክንያቶች መሆናቸውንም ይጠቁማሉ።

ምን ሊረዳ ይችላል?

ከወሊድ በኋላ በሚከሰት የአእምሮ ጤና ችግር የተጠቁ እናቶች ተገቢውን ሕክምና እና ድጋፍ ካላገኙ ራሳቸውን ሊጎዱ እንደሚችሉ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ።

በዩኬ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ የተደረጉ ጥናቶች እንዲህ ዓይነት ሕመም የገጠማቸውን እናቶች ከልጆቻቸው ጋር አንድ ላይ በማቆየት እና የቅርብ ክትትል በማድረግ ማከም የተሻለ ነው።

በፈረንሳይ እና ቤልጂየም ደግሞ እነዚህን እናቶች ለማከም የተዘጋጁ የሕክምና ክፍሎች አሉ።

ኤሊ "ለእኔ በእእምሮዬ ውስጥ የሆነ ባልቦላ እንደጠፋ ነው የተሰማኝ፤ ደግሞ የሚታይ ነበር" ትላለች።

ስለተፈጠረው ነገር ሙሉ በሙሉ ማስታወስ ብትቸገርም ቤቷ ደረጃ ላይ ቆሟ ባሏ ወደ ሆስፒታል ሲደውል ታስታውሳለች።

"በጣም ነበር የፈራሁት። እርዳታ ማግኘት ፈልጌ ነበር። እጮህ ስለነበር የአዋላጅ ሐኪሞች ኃላፊዋ ከልጄ ጋር ተኝቼ ሕክምናውን እንድከታተል በጣም ታግላልኛለች" ትላለች ኤሊ።

"ከምንም ከምን በላይ ጠቃሚው ነገር የእኔን ደኅንነት ማረጋገጥ ነበር። ያ ነበር ቀዳሚ ትኩረታቸው።"

"I'm not myself you see " የሚል መጽሐፍ የጻፈችው አሪያኔ ቢስቶን ደግሞ ከወሊድ በኋላ ባጋጠማት የአእምሮ ሕመም ወቅት ከልጇ ጎን ድራገን ሲያንዣብብ ይታያት እንደነበር ትናገራለች።

ሰው አልባ አውሮፕላን ሲበር ይሰማት እንደነበርም ጽፋለች።

ወደ ሆስፒታል ከመጣች በኋላ ልጇ በቅርቧ ሆኖ በቂ እንቅልፍ እንድታገኝ ከተደረገ በኋላ ከሕመሟ ማገገሟን ትናገራለች።

ሕመሟ በመሠረታዊነት እንደለወጣት የምትናገረው አሪያኔ፣ መቼ ከሆስፒታል መውጣት እንዳለባት፣ ልጇን ጡት ማጥባት ይኑርባት አይኑርበት የሚሉት ወሳኝ ነጥቦች እነደነበሩ ትናገራለች።

በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ክሌር ዶልማን ሕክምና እየወሰዱ ጡት ማጥባት እናቶች የሚወስኑት ከፍተኛው ውሳኔ መሆኑን ይናገራሉ።

በአንዳንድ አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ እናት መሆን በማኅበረሰቡም፣ በባህልም ትልቅ ክስተት ነው።

በአንዳንድ ባሕሎች አራስ እናቶች ለ40 ቀናት ያህል ከቤት ሳይወጡ እንዲቆዩ ይደረጋል።

እነደ ሕንድ ባሉ አገራት ደግሞ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የአእምሮ ሕመም በክፉ መንፈስ እንደመያዝ ይቆጠራል።

በሌላ አገር ባህል ደግሞ የእናቲቱ አለመቻል ተደርጎ ይወሰዳል።

በሆንክኮንግ ደግሞ አዲስ የወለዱ እናቶች የባሕላዊ ሥነ ሥርዓት እና ክዋኔዎች ላይ እንዲሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን ያንን አለማድረግ በማኅበረሰቡ ፊት ለመቆም አያስችልም።

ሌላ ልጅ መውለድ ቢፈልጉስ?

ከወሊድ በኋላ የአእምሮ ሕመም ከገጠማቸው ሁለት እናቶች መካከል አንዷ እንዳለመታደል ሆኖ ዳግም በምትወልድበት ወቅት ተመሳሳይ ችግር ሊያጋጥማት እንደሚችል በማንቸስተር እና ካርዲፍ ዩኒቨርስቲዎች የተሠራ ጥናት ያሳያል።

ብዙ ልጆች ያላቸው እናቶች አስቀድመው የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ማቀድ ይችላሉ ትለለች ኤሊ።

እንቅልፍ እንዲያገኙ ተጨማሪ ቤተሰብ ወይንም ጓደኛ በዙሪያቸው እንዲሆን ይፈልጉ እንደሆን ከመውለዳቸው በፊት አስቀድመው መወሰን ይኖርባቸዋል።

"ጥሩ ወላጅ መሆን እንዲችሉ ግን ለራሳቸው ቅድሚ ለመስጠት" መዘጋጀት እንዳለባቸው ኤሊ ትመክራለች።