እርግዝናን የሞት እና የሕይወት ጉዳይ የሚያደርገው አሳሳቢው የጤና እክል

"ይህንን ልጅ ለማግኘት ጸልያለሁ፤ ነገር ግን አሁን ካለሁበት የተዳከመ ሁኔታ አንጻር ያለሁበት ሁኔታ ቶሎ እንዲያበቃ ፈልጌ ነበር።"

በኦንታርዮ ካናዳ የምትኖረው ክሪስታቤል ንጉቤ ነፍሰጡር መሆኗን ለመጀመሪያ ጊዜ ባወቀች ጊዜ በጣም ደስተኛ ነበረች።

የ30 ዓመቷ ክሪስታቤል ለዓመታት ወልዳ ለመሳም ስትጸልይ ነበር።

ደስታዋ ግን ብዙም ሳይቆይ ወደ ሐዘን ተለወጠ።

በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የእርግዝናዋ ደስታ ከጤንነቷ ጋር በምታደርገው ግብ ግብ ተተካ።

ክሪስታቤል ከባድ የማቅለሽለሽ እና ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ማስመለስ ነበራት።

የምግብ ሽታ ይህንን ሕመሟን ይቀሰቅሰዋል።

ብዙም ሳይቆይ ያለባትን የማያቋርጥ ማስመለስ በመፍራት ውሃ መጎንጨት አቆመች።

ያሏት ምልክቶች ነፍሰጡር እናቶች ጠዋት ጠዋት የሚገጥማቸው ሕመም ዓይነት አይደለም፤ ከዚያ ጠንከር ያለ ነው።

ብዙ እናቶች በመጀመሪያዎቹ የእርግዝና ሳምንታት፣ በተለይም ከስድስት እስከ 14 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ በሚኖር የሆርሞን ለውጦች የተነሳ ሕመሞች ያጋጥሟቸዋል።

የክሪሳታቤል ሁኔታ በጣም የከፋ ነበር።

በመጨረሻ እስከ 39ኛው የእርግዝና ሳምንት ሊቀጥል የሚችል፣ የሚያዳክም ለድርቀት እና ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሊያጋልጥ የሚችለው ሃይፐርሜሲስ ግራቪዳረም (ኤችጂ) እንዳለባት በምርመራ ታወቀ።

ኤችጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም ዙሪያ ትኩረት አግኝቷል።

የዌልሷ ልዕልት ካትሪን በሦስቱም የእርግዝናዋ ጊዜያት የነበራትን ተመሳሳይ ልምድ በግልጽ አካፍላለች።

በዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት መረጃ መሠረት በአገሪቱ ውስጥ ከሚከሰቱ 100 እርግዝናዎች መካከል እስከ ሦስት የሚደርሱት ይህ የጤና እክል ያጋጥማቸዋል።

ይኹን እንጂ የጤና ባለሙያዎች በሽታው በበቂ እንዳልተነገረለት ያስረዳሉ። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተጽእኖ በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ አድርጎታል።

ክሪስታቤል "በጣም ይርበኝ፣ በሕመም እሰቃይ ነበር። ነገር ግን መብላት አልቻልኩም" ካለች በኋላ "እንዳያስመልሰኝ ስለምፈራ ውሃ እንኳን መጠጣት አልቻልኩም" ስትል በወቅቱ ይሰማት የነበረውን ተናግራለች።

በአእምሮ ጤንነቷ ላይ ያለውን ከባድ ጫና ስታብራራም የመነጠል እና በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች እንዳልተረዷት ይሰማት እንደነበር ገልጻለች።

ምርመራ ለማግኘት ያለው ተግዳሮት

በብዙ የዓለም ክፍሎች ባለው ውስን የሕክምና ተደራሽነት የተነሳ ኤችጂ ብዙ ጊዜ ሳይታወቅ እንዲቀር አድርጓል።

አንዳንድ ሴቶች በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱት ከባድ ሕመሞች እንደ ድክመት ወይም ማጋነን ስለሚቆጠርባቸው መገለል ይደርስባቸዋል።

በናይጄሪያ አቡጃ የመጀመሪያዋን ልጅ የጸነሰችው ኔንይ እንዲሁ በሚታይባት ምልክት ክብደት የተነሳ በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች መነጋገርያ ሆናለች።

በእርግዝና ወቅት የሚከሰተውን ማቅለሽለሽ እና ድካም ጠብቃው የነበረ ቢሆንም፣ ከዚያ በተለየ የማያቋርጥ ማስመለስ፣ ከባድ ድርቀት እና በተደጋጋሚ የሕክምና ባለሙያ ድጋፍ ማግኘት አስፈለጋት።

በኋላ ላይም በጤና ተቋም ተኝታ ክትትል እንድታደርግ ተደረገ።

"ከዚህ በፊት ስለ ሃይፐርሜሲስ ግራቪዳረም ሰምቼ አላውቅም ነበር" ብላለች ኔንይ።

ልክ እንደሌሎች ለመጀመሪያ ጊዜ እናት እንደሆኑት ምን እየሆነ እንዳለ አልገባኝም ነበር። ሁኔታው እየተባባሰ በሄደ ወቅት እንኳ የጤና ባለሙያዎች እርዳታ ለማግኘት ዘግይቻለሁ።

"የጤና ባለሙያው ቀለል አድርጎ ይህ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም ነው" ብሎ ማለፉን ታስታውሳለች።

ኔንይ ግን ሁኔታዋ የተለመደ እንዳልሆነ ታውቅ ነበር። የአምስት ወር ነፍሰጡር ሆናም በጣም ያስመልሳት ነበር።

ደም ማስመለስ ስትጀምር ነው የሕክምና ባለሙያዎችን እርዳታ ያገኘችው።

ባለሙያዎች ኤችጂን በምርመራ በቀላሉ ማወቅ ከተለመዱ የእርግዝና ምልክቶች ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ አስቸጋሪ ነው ይላሉ።

በናይጄሪያ ኢቦኒ የጽንስ እና ማህጸን ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ንኪሩካ ኡቼ ንዊዳጉ፣ ሰዎች ውጤቱ ከባድ ሊሆን ስለሚችል ኤችጂ ቀለል አድርገው መመልከት እንደሌለባቸው ያስጠነቀቅቃሉ።

"ጠዋት ጠዋት የሚኖር ሕመም ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ ሊያስከትል ይችላል። በዚህ ወቅት አብዛኞቹ ሴቶች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ማከናወን እና መመገብ ይችላሉ" ይላሉ ዶክተር ኡቼ ንዊዳጉ።

"ኤችጂ ግን በተቃራኒው አቅምን አሟጣጭ ነው። የእናቲቱን አቅም ያዳክማል፤ መሠረታዊ ተግባራትን እንኳን ማከናወን እንዳትችል ያደርጋል።"

"መጀመሪያ ላይ አስጊ የማይመስሉ የኤሌክትሮላይት አለመመጣጠንን ጨምሮ የአካል ክፍሎች ሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል" በማለት ያስጠነቅቃሉ።

የማህጸን እና ጽንስ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር አዲኒያ አኪሴኩ በበኩላቸው ኤችጂ ጨቅላውንም ሊጎዳ ይችላል ይላሉ።

"እናት በጊዜው ካልታከመች፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረቱ ዝቅተኛ ክብደት ያለው ልጅ እንዲወለድ ያደርጋል፤ አልፎ ተርፎም ጨቅላው ከሚጠበቅበት ጊዜ ቀድሞ እንዲወለድ ያደርጋል።"

ኤችጂ በዘር የሚተላለፍ ነው?

ጥናቶች ሃይፐርሜሲስ ግራቪዳረም (ኤችጂ) በዘር የሚተላላፍ ነው ብለው ሙሉ በሙሉ አልደመደሙም።

ይኹን እንጂ በደቡባዊ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ማርሌና ፌዞ ኤችጂ የገጠማቸውን ቤተሰቦች በሚመለከት የዘር ግንኙነትን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ አለ ይላሉ።

ዶ/ር ፌዞ አክለውም ኤችጂ ያለባቸው ሴቶች በእርግዝና ወቅት ከፍ ያለ የጂዲኤፍ 15 ሆርሞን አላቸው።

ይህ ሆርሞን እብጠትን፣ የምግብ መፈጨትን እና የሕዋሳት ዕድገትን ይቆጣጠራል።

እነዚህ ሴቶች ከእርግዝና በፊት ዝቅተኛ ለሆነ ሆርሞን የተጋለጡ ናቸው።

"ይህ በሆርሞን ላይ ያለው ለውጥ ከፍ ያለ ስሜትን እንደሚፈጥር እና ሃይፐርሜሲስን እንደሚያስከትል ተገንዝበናል" ብለዋል።

የሕክምና አማራጮች

የኤችጂን ምልክቶችን ለመቀነስ የሚረዱ እና በእርግዝናው የመጀመሪያዎቹ 12 ሳምንታት ጨምሮ ሊታዘዙ የሚችሉ መድኃኒቶች አሉ።

እነዚህም ፀረ ሕመም (ፀረ ኤሜቲክ) መድኃኒቶች፣ ስቴሮይድ ወይም የሁለቱንም ጥምረት ያካትታሉ።

ነገር ግን ማስመለስን መቆጣጠር በማይቻልበት ጊዜ እናቶች በሰውነታቸው ውስጥ ያለውን ፈሳሽ ለማሻሻል እና የምግብ ድጋፍ ለማግኘት ሆስፒታል ተኝተው መታከም ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

እነዚህም ብዙ ጊዜ በደም ሥር የሚሰጡ ይሆናል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕክምና ባለሙያዎች እንደ ኤሌክትሮላይት አለመመጣጠን ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሕሙማን የቅርብ ክትትል ሊደረግላቸው ይችላል ብለዋል።

የአእምሮ ጤና ድጋፍም እንዲሁ ወሳኝ ነው። በኤችጂ ምክንያት የሚገጥመው የሥነ ልቦና ጉዳት ከወሊድ በኋላም ሊቀጥል ይችላል።

እንደ ዶ/ር አኪሴኩ ገለጻ፣ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ፣ ኤችጂ ዘላቂ የሆነ የሥነ ልቦና ተጽእኖ እንደ ጭንቀት እና ድብርት ሊያስከትል ይችላል።

ኔንዬ ለብዙ ወራት አካላዊ እና ስሜታዊ ጭንቀትን እንደታገለች እና ከወለደች በኋላም የኤችጂ ተጽዕኖ አብሯት መዝለቁን ትናገራለች።

"ራሴን መምሰል አቆምኩ" ትላለች። "ሰዎች ቆዳዬ ለምን እንደገረጣ ይጠይቁኛል።"

አክላም "ከወሊድ በኋላ ለደረሰብኝ የመንፈስ ጭንቀት የገጠመኝ መገለል አስተዋጽኦ ያደረገ ይመስለኛል" ብላለች።

ከባድ ጉዳዮች ሴቶች የችግሩን ዘላቂ ውጤት እንዲቋቋሙ ለመርዳት የሥነ ልቦና ድጋፍን ጨምሮ ተጨማሪ ሕክምናዎች ሊፈልጉ ይችላሉ።

ዶ/ር ኡቼ ንዊዳጉ ኤችጂ ብዙ ጊዜ የማይታወቅ በመሆኑ ብዙ ሴቶች በዝምታ ስለሚሰቃዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ አስፈላጊነትን አበክረው ገልጸዋል።

አፋጣኝ ድጋፍ ሁኔታውን ለመቆጣጠር እና በእናቲቱም ሆነ በጽንሱ ላይ ከባድ የጤና አደጋዎችን ለመከላከል ቁልፍ ነው።

ይህ ደግሞ ስቃይን ለማቃለል ብቻ ሳይሆን ሕይወትንም ለማዳን ያስችላል።