ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ይዞታውን እያሰፋ ያለው አልሻባብ ለሶማሊያ መንግሥት ኅልውና ያሰጋል?
የሶማሊያ መንግሥት በደቡብ-መካከለኛው የሂራን፣ መካከለኛው እና የታችኛው ሸበሌ ክልል ውስጥ ለወራት የዘለቀውን የአልሸባብ የግዛት መስፋፋት ግስጋሴን ለመቆጣጠር እየታገለ ነው።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በግንባር ቀደም አካባቢዎች ተደጋጋሚ ጉብኝት ማድረግን ጨምሮ የተቀናጀ መከላከል ቢያደረጉም፤ታጣቂዎቹ በሦስቱ ክልሎች ሰፊ ቦታዎችን ከመንግሥት ኃይሎች መልሰው ለመቆጣጠር ችለዋል።
አልሸባብ ከየካቲት ወር ወዲህ በከፈተው መጠነ ሰፊ ጥቃት የሶማሊያ መንግሥት ሠራዊት በከባድ መስዋዕትነት የያዛቸውን አንዳንድ ግዛቶች መልሶ በእጁ ያስገባ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ የተፋፋመ ጦርነት እያካሄደ ነው።
ከየካቲት እስከ ሚያዝያ ባሉት ወራቶች መካከል ቡድኑ በሁለቱ የሸበሌ ክልሎች እና ሂራን ውስጥ ቢያንስ 20 ከተሞችን እና መንደሮችን ተቆጣጥሯል።
በሰኔ፣ በሐምሌ እና በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ተጨማሪ ስምንት ከተሞችን እና መንደሮችን ለመያዝ ችሏል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐሙድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ባካሄዷቸው ዘመቻዎች በርካታ አካባቢዎችን ከአልሻባብ ማስለቀቅ ቢችሉም፤ አሁን ግን ቡድኑ እየበረታ ይዞታውን መልሶ እያሰፋ ነው።
ይዞታውን እያሰፋ ያለው አልሻባብ
አዲሱ የአልሻባብ የማስፋፋት ጥቃት ዘመቻ ዋነኛ ትኩረት በሂራን ላይ ነው። ይህ ክልል ለዓመታት ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ ታጣቂውን እየወጋ የሚገኘው ማአዊስሌይ የተባለው የመንግሥት ደጋፊ ታጣቂ ኃይል የተፈጠረበት ቦታ ነው።
ባለፉት ስድስት ወራት አልሻባብ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ለዓመታት የቆዩ ቁልፍ አካባቢዎችን በመቆጣጠር ይዞታውን በከፍተኛ ሁኔታ እያሰፋ ነው።
በተለይ ባለፈው ሐምሌ አጋማሽ ላይ በአውሮፓውያኑ 2013 የሶማሊያ ኃይሎች በኢትዮጵያ ወታደሮች ድጋፍ ከታጣቂ ቡድኑ የተቆጣጠሯት መሃስ የተባለችውን ቁልፍ ከተማ አልሻባብ መልሶ ይዟታል።
ባይዶዋ ኦን ላይን የተባለው የግል የዜና ድረ ገጽ እንደዘገበው በአሁኑ ወቅት አልሻባብ የሂራን እና የመካከለኛው ሸበሌን ከሚያካትተው ሂርሸበሌ ክልል ግዛት ውስጥ 60 በመቶውን ተቆጣጥሯል። እንዲሁም በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የሚገኙ ሌሎች ወሳኝ ከተሞች በአልሻባብ ተከበው በከባድ ጫና ውስጥ ይገኛሉ።
የሶማሊያ መንግሥት ጥረት
የሶማሊያ መንግሥት የአልሸባብን ጥቃት ለመከላከል እና የተወሰዱበትን ቦታዎች ለማስመለስ ወታደሮቹን እና የጎሳ ሚሊሻዎችን በማሰባሰብ ጥረቱን አጠናክሯል።
በተጨማሪም ከአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች ጋር በመሆን ታጣቂው የከፈተበትን ጥቃት ለመቀልበስ እየጣረ ነው።
በሰኔ ወር በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) ወታደሮች የአልሻባብ ታጣቂዎችን ከሞቃዲሾ አቅራቢያ ከሚገኙ ቁልፍ ከተሞች ለማስወጣት ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ተሰልፈዋል።
በዚህም ጥምሩ ኃይል ለበርካታ ቀናት ያካሄደውን ዘመቻ ተከትሎ ሰኔ መጨረሻ ገደማ ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ በስተሰሜን ምዕራብ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙትን ወሳኞቹን የሳቢድ እና አኖሌ መልሰው ይዘዋል።
ሐምሌ መጨረሻ ላይ አልሸባብ ከከባድ ፍልሚያ በኋላ መንደሮቹን መልሶ ለመቆጣጠር ቢችልም፤ጥምር ኃይሎቹ ግን ታጣቂዎቹን ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ ጥምር ኃይሉ ከዋና ከተማዋ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን እና ሞቃዲሾን ለመከላከል ወሳኝ መስመር ላይ የምትገኘውን የግብርና ከተማ የሆነችውን ባሪሬን ለመያዝ ተንቀሳቅሶ በነሐሴ መጀመሪያ ላይ በእጁ አስገብቷል።
ከተማዋ በመንግሥት ወታደሮች መያዟን "ወሳኝ እርምጃ" ያለው የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስቴር ባሪሬን ለመቆጣጠር ከአልሻባብ ጋር በተደረገው ውጊያ 120 ታጣቂዎች ተገድለዋል ብሏል።
የጥምር ኃይሉ ቀጣይ ዒላማ ትሆናለች ተብላ የምትጠበቀው በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው እና በአልሻባብ ቁጥጥር ስር የምትገኘው አውድሄግሌ ከተማ ናት።
ባለፈው መጋቢት በቡድኑ እጅ የገባችው ይህች ከተማን መቆጣጠር ከተቻለ በታጣቂዎች ጥቃት ያልተቋረጠ ስጋት ውስጥ ለምትገኘው ሞቃዲሾ እፎይታን የሚያስገኝ ይሆናል።
የሶማሊያ ሠራዊት እና የመንግሥት አጋር የሆኑት ታጣቂዎች ባለፉት ወራት በታጣቂው ቡድን ተከታታይ ሽንፈት በገጠማቸው በመካከለኛው ሸበሌ ላይ የፀረ ማጥቃት ዘመቻ ለማካሄድ ዕቅድ ሲያወጡ ቆይተዋል። ለዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ የአካባቢ ታጣቂዎችን በማሰለፍ ሚያዝያ ወር ላይ በአልሻባብ የተያዘችውን ስልታዊ ከተማ አዳን ያባን ለማስመለስ እየተዘጋጁ ነው።
የሶማሊያ መንግሥት ለአፍሪካ ኅብረት ኃይል ወታደር ካዋጡት አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ጂቡቲ የታጣቂ ቡድኑን መስፋፋት ለመግታት ተጨማሪ ወታደሮችን እንድታሰማራ ጠይቆ ስምምነት ማግኘቱን ተናግሯል።
በተጨማሪም የሶማሊያ መንግሥት አልሻባብ ገንዘብ የሚያገኝባቸውን መዋቅሮች ለማቋረጥ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።
በዚህም ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የባንክ አካውንቶችን የዘጋ ሲሆን፣ነጋዴዎችም ከቡድኑ በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት ገንዘብ እንዳይሰጡ እያደረገ ነው።
የሶማሊያ መንግሥት የገጠመው ተደራራቢ ጫና
ከፊል ራስ ገዝ ከሆኑት ክልላዊ ግዛቶች፣ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካላቸው የተቃዋሚ መሪዎች እና ከተለያዩ ወገኖች ጋር ማብቂያ በሌለው ውዝግብ ውስጥ የሚገኘው የሶማሊያ መንግሥት ትኩረቱን ሙሉ ለሙሉ አልሻባብን በመፋለም ላይ ለማድረግ አልቻለም።
በአሁኑ ወቅት የሶማሊያ መንግሥት በተደጋጋሚ በተደረጉት የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች እና የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓትን መልሶ በማወቀር ላይ ከተቃዋሚዎች ጋር ውዝግብ ውስጥ ይገኛል።
ሐምሌ አጋማሽ ላይ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና ፕሬዝዳንት ሞሐሙድ በምርጫ ጉዳይ ላይ ቢነጋገሩም መስማማት ሳይችሉ ተለያይተዋል።
በተጨማሪም መንግሥት ከቅርብ ወራት ወዲህ በደቡብ ምዕራብ ጌዶ ክልልን ከፊል ራስ ገዝ ከሆነችው የጁባላንድ ክልላዊ መንግሥት ለመንጠቅ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች እና የጦር መሳሪያዎችን አሰማርቷል።
በነሐሴ መጀመሪያ ላይ በጌዶ የመንግሥት የፀጥታ ኃላፊ አብዲራሺድ ሐሰን አብዲኑር (ጃናን) በክልሉ ጁባላንድን የሚቀናቀን አዲስ ክልላዊ መንግሥት ለማቋቋም ማቀዱን አስታውቋል።
ይህ ደግሞ በበለድ ሃዎ እና በዶሎ ከተሞች በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የተካሄደውን ለሳምንታት የዘለቀ ግጭት ተከትሎ ይፋ የሆነ ክስተት ነው።
በሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ውስጥ የሚደረጉ ፖለቲካዊ ለውጦች አልሸባብን በብቃት በመዋጋት በኩል ያለውን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ሊያዳክምበት ይችላል።
የፖለቲካ እና የፀጥታ ባለሥልጣናት ከኃላፊነታቸው መነሳት በተዋጊዎች መካከል ቅሬታን በመፍጠር የመዋጋት ሞራላቸውን አዳክሞ በቅርቡ እንደታየው በአልሻባብ ተከታታይ ሽንፈት እንዲገጥማቸው ለማድረግ ምክንያት ሊሆን እንሚችል ተንታኞች ይናገራሉ።
ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ የምትገኘው ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው የፑንትላንድ ግዛትም በበኩሏ የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናትን የሚያነሳው ከአልሻባብ ጋር በተደረገ ስምምነት ነው በማለት ወንጅላ ክስቱን ልትጠቀምበት ሞክራለች።
መንግሥት በአልሻባብ ተዋጊዎች ላይ ለሚያካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ የሚያስፈልገውን አብዛኛውን ወጪውን የሚሸፍነው ከለጋሾች ከሚያገኘው ገንዘብ በመሆኑ ተጨማሪ ጫናን ፈጥሮበታል።
በሶማሊያ እያጋጠመ ያለው ተደራራቢ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና የገንዘብ ጫና ፌደራል መንግሥቱ በአልሻባብ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ፍጥነቱን ጠብቆ ለውጤት እንዳይበቃ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።