አልሸባብ የኢትዮጵያ ጦር ያስለቀቀውን ከተማ ከሶማሊያ ሠራዊት መልሶ ተቆጣጠረ

የሶማሊያው ታጣቂ ቡድን አልሸባብ ከ11 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ጦር እንዲለቅ የተደረገውን እና በሶማሊያ መንግሥት ሠራዊት ስር የነበረችውን ማሃስ ከተማ ዳግም በቁጥጥሩ ስር ማስገባቱ ተሰማ።

ቢቢሲ ሶማሊኛ ዛሬ ማለዳ ባወጣው ዘገባ መሠረት በማዕከላዊ ሶማሊያ ሂራን ክልል ውስጥ የምትገኘው ማሃስ ትናንት እሁድ ከባድ ውጊያ ተካሂዶባታል።

በከተማዋ በመንግሥት ወታደሮች እና ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው በሚነገርለት በአልሸባብ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደው ከባድ ውጊያ በርካቶች መሞታቸው ተሰምቷል።

አልሸባብ በከተማዋ ላይ ጥቃት የፈጸመው ተቀጣጣይ ፈንጂ በጫኑ መኮኖች በመታገዝ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።

የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር በአካባቢው ስላለው ግጭት ባወጣው አጭር መግለጫ የአካባቢ እና የመንግሥት ኃይሎች በርካታ የአልሸባብ ታጣቂዎችን መግደላቸውን ገልጿል።

ነገር ግን ሚኒስቴሩ ምን ያህል ታጣቂዎች እንደተገደሉ የገለፀው ነገር የለም።

የአከካባቢው ነዋሪዎች በአልሸባብ እና በመንግሥት ወታደሮች መካከል በነበረው ውጊያ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን የደረሰውን ጉዳት ለማረጋገጥ የሚያስችል የገለልተኛ ወገን መረጃ የለም።

የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር የመንግሥት እና አካባቢ ኃይሎች ከከተማዋ ውጪ ወደ ማሃስ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ ናቸው ብሏል።

ማሃስ በማዕከላዊ ሶማሊያ በሂራን ክልል ካሉ አውራጃዎች መካከል አንዷ ስትሆን ከዚህ ቀደም እአአ በ2014 በአልሸባብ ቁጥጥር ስር በነበረችበት ወቅት በአገሪቱ ተሰማርቶ ባለው በኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲለቅ ተደርጎ ነበር።

በደቡብ እና መካከለኛው ሶማሊያ ሰፊ አካባቢዎችን የሚቆጣጠረው አልሸባብ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ለ20 ዓመታት ያህል ሲዋጋ ቆይቷል።

ታጣቂ ቡድኑ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥትን በኃይል በማስወገድ እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት ይፈልጋል።

በአፍሪካ ኅብረት የሚመራው የሰላም አስከባሪ ኃይል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 እና 2023 ታጣቂ ቡድኑ እንዲያፈገፍግ እና ከማጥቃት ይልቅ መከላከል ላይ እንዲያተኩር አድርጎ ነበር።

ቡድኑ በርካታ ተከታታይ ወታደራዊ ጥቃቶች ቢፈጸምበትም አሁንም በሶማሊያ ትልቅ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል።

የሶማሊያ መንግሥት ቡድኑ ተዳክሟል ሲል ያስተባብላል።

የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ትናንት በማዕከላዊ ሶማሊያ ቁልፍ በሆነችው ማሃስ ከተማን በያዘ ጊዜ 63 የሶማሊያ ወታደሮችን መግደሉን እና 84 ሰዎችን ማቁሰሉን አስታውቋል።

የቡድኑ ልሳን የሆነው 'ራዲዮ አንዳሉስ' እንደዘገበው በሂራን ክልል በማሃስ ከተማ ላይ ያነጣጠረው ጥቃት በከተማዋ እና በአካባቢው ከመንግሥት ደጋፊ ኃይሎች ጋር ከፍተኛ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት "በዋና ወታደራዊ ካምፕ ላይ ያነጣጠረ የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ፈንድቷል" ብሏል።

አልሸባብ ከተማይቱን መቆጣጠሩን ያሳያል ያላቸውንም ምሥሎችንም በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ ለቅቋል።

'ዘ ዴይሊ ሶማሊያ' በኤክስ ገፁ ላይ እንደዘገበው ከተማዋን ሲከላከሉ የነበሩት የማአዊስሊ ሚሊሻዎች ከተማዋን ለቅቀው ለመውጣት ተገድደዋል።

የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምላሽ ባይሰጡም የአገሪቱ መከላከያ ግን ከከተማዋ አቅራቢያ ባለች ከተማ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት መመከቱን ተናግሯል።

የቡድኑን ጥቃት ተከትሎ ከማሃስ ያፈገፈጉት ወታደሮች ወደ አጎራባቿ ጋልጉዱድ ክልል ጉሪኤል ከተማ መግባታቸው ታውቋል።

ማሃስ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ አልሸባብ በደቡብ መካከለኛው ሶማሊያ ከያዛቸው ትልልቅ ከተሞች ሦስተኛዋ ነች።

ታጣቂዎቹ በሚያዝያ እና በሐምሌ ወር ውስጥ አዳን ያባል እና ሞቆኮሪ ከተሞችን ይዘዋል።

ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ አልሸባብ በታችኛው ሸበሌ፣ በመካከለኛው ሸበሌ እና ሂራን ክልሎች ውስጥ ከ20 በላይ አካባቢዎችን እንደገና በመቆጣጠር ከ2022 ጀምሮ ማዕከላዊ መንግሥት ያገኘውን ስኬት እየቀማ ነው።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ ባካሄዷቸው ዘመቻዎች በርካታ የሶማሊያ አካባቢዎችን ከአልሻባብ በማስለቀቅ ቡድኑን ማዳከም ችለው ነበር።

ነገር ግን ባለፉት ወራት ቡድኑ እየተጠናከረ ጥቃቶችን በመፈጸም በመንግሥት ኃይሎች የተያዙ ቦታዎችን በቁጥጥሩ ስር እያስገባ ይገኛል።