ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጦርነት መሀል የተወለዱ ልጆችን ስለ ስሜት የሚያስተምሩት የሶማሊያ ትምህርት ቤቶች
በማዕከላዊ ሶማሊያ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ታዳጊዎች መሬት ላይ ክብ ሠርተው ተቀምጠዋል።
መምህራቸው የምታነብላቸውን ታሪክ በአንክሮ ያደምጣሉ።
ከሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በ500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዱሳማራብ የሚገኘው ዳርየል አካዳሚ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ አዲስ አሠራር እየተዘረጋ ነው።
ተማሪዎች ስለ ስሜት ይማራሉ። ማኅበራዊ ክህሎታቸው እንዲሻሻልም ትምህርት ይሰጣቸዋል።
ተማሪዎች የስድስት እና የሰባት ዓመት ልጆች ናቸው። የተለያዩ ስሜቶች የሚያሳዩ ሰዎችን ምሥሎች እንዲመለከቱ ይደረጋል።
አንደኛው ምሥል ላይ ከሰዎች የተነጠለ ልጅ ይታያል። ልጁ ምን ስሜት እንደሚሰማው ተማሪዎቹ ይጠየቃሉ።
መምህራቸው ኑስሮ መሐመድ ሄርሲ "ልጆቹ ይሄንን ትምህርት በጣም ይወዱታል። ከሌሎች ትምህርቶች አንጻር በጉጉት ነው የሚጠብቁት" ትላለች።
ተማሪዎችን ስለ ስሜት ለማስተማር እና ማኅበራዊ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ መጻሕፍት ተዘጋጅተዋል።
ልጆች የሚሰማቸውን ስሜት እንዲረዱ ያግዛሉ። እንዲህ ያለ ትምህርት በሶማሊያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ነው የተጀመረው።
ተማሪዎች የባህሪ ችግር እንደሚገጥማቸው ከተስተዋለ በኋላ የጋላሙዱግ ግዛት አስተዳደር ዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኘው የተራድኦ ድርጅት 'ቲንክኢኳል' ጋር በመጣመር ነው ትምህርቱ የተጀመረው።
ቲንክኢኳል ስለ ስሜት ማስተማር የሚቻልባቸውን መጻሕፍት ያዘጋጃል። መምህራንንም ያሠለጥናል።
"ዓላማው በቀጣዩ ትውልድ መድልዎን፣ አለመከባበርን እና ነውጥን ማስወገድ ነው" በማለት ነው ትምህርቱን የሚገልጸው።
"ትምህርቱ ርህራሄን ለመፍጠር፣ ጤናማነትን ለማስፋፋት እና በፍቅር የተሞላ ግንኙነት ለመመሥረት እንዲሁም ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ይረዳል" ሲልም ያክላል።
ረዥም የግጭት ታሪክ
ኦስሎ የሚገኘው ፒስ ሪሰርች ኢንስቲትዩት በሠራው ጥናት መሠረት ከስድስት ልጆች አንደኛቸው በግጭት በሚናጥ አካባቢ ነው የሚኖሩት።
በ2024 የወጣው ጥናት እንደሚጠቁመው ወደ 473 ሚሊዮን የሚጠጉ ልጆች በጦርነት ቀጣና ውስጥ ነው የሚኖሩት። ይህ ቁጥር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ ነው።
የተቋሙ የጥናት ክፍል ዳይሬክተር ሲሪ አስ ረስትድ "በ1990ዎቹ አካባቢ 250 ሚሊዮን ልጆች በግጭት ቀጣና ይኖሩ ነበር። ከዚያ ወዲህ ባሉት ዓመታት ቁጥሩ እየጨመረ ነው። ከ250 ሚሊዮን በእጥፍ ጨምሮ 500 ሚሊዮን ደርሷል" ይላሉ።
ሶማሊያን ጨምሮ ሌሎችም የአፍሪካ አገራት ግጭት የተበራከተባቸው ናቸው።
ከአውሮፓውያኑ 1991 ወዲህ ሶማሊያ የእርስ በርስ ጦርነት እና የጎሳ ግጭት ውስጥ እያለፈች ነው።
ከሞቃዲሾ ውጪ ያሉ አካባቢዎችን በአግባቡ የማይቆጣጠረው ደካማው የሶማሊያ መንግሥት አገሪቱን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ከአል-ሻባብ ጋር ውጊያ ውስጥ ነው።
የአረብኛ ትርጓሜው "ወጣቶች" የሆነው አል-ሻባብ ከግጭት ውጪ ሌላ ታሪክ የማያውቁ አማራጭ እና ተስፋ የጨለመባቸውን ወጣቶች እየመለመለ አባሉ ያደርጋል።
አብዛኞቹ ተዋጊዎች አልተማሩም፤ ሥራ የማግኘት ዕድላቸውም ጠባብ ነው።
አል-ሻባብ ታዳጊዎቹ አንዳች መጠለያ ወይም የእኔነት ስሜት የሚሰጣቸው ቡድን ውስጥ እንዳሉ እንዲሰማቸው ያደርጋል።
ፖቨርቲ አክሽን የተባለው የባለሙያዎች ቡድን እንደሚገልጸው ታዳጊዎች ለነውጥ በለጋ ዕድሜያቸው ሲጋለጡ ለዓመታት የሚዘልቅ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል። በልጅነታቸው የገጠማቸው ነውጥ ችላ ተብሎ ከታለፈ ከተጽዕኖው ለመላቀቅ ይቸገራሉ።
ጭንቀት፣ ቁጡነት እና ብቸኛነትን መምረጥ በእነዚህ ታዳጊዎች ላይ ይስተዋላል።
የለውጥ መንገድ
ሶማሊያን ጨምሮ በአፍሪካ አገራት የአእምሮ ሕክምና ውስንነት በመኖሩ ታዳጊዎች እንዴት ስሜታቸውን መቆጣጠር እንደሚችሉ ሳይማሩ ያድጋሉ።
ዬል ሴንተር ፎር ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ ተባባሪ መሥራች ዶ/ር ሮቢን ስተርን እንደሚሉት ልጆች ስለ ማኅበራዊ ክህሎት እና ስሜት መማር ይችላሉ።
ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ልጆች ሲያድጉ ግጭት መፍታት እንዲችሉ ያግዛል።
የኮሎምቢያ የእርስ በእርስ ጦርነት ማክተምን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 2020 የማኅበራዊ ክህሎት እና ስሜት ትምህርት ተጀምሯል።
ትምህርቱ ልጆች ስለራሳቸው ያላቸው ግንዛቤ እንዲጨምር እና የተሻለ ማኅበራዊ ክህሎት እንዲኖራቸው ማድረጉን መመልከትም ተችሏል።
መምህርቷ ኑስሮ መሐመድ ሄርሲ እንደምትለው፣ ተማሪዎቿ ስለ ስሜት መማር ከጀመሩ ወዲህ ለውጥ እያሳዩ ነው።
"ንዴቱን መቆጣጠር የማይችል አንድ ተማሪያችን አሁን የተረጋጋ መሆኑን አስተውለናል። ራሱን ከጓደኞቹ ይነጥል ነበር። አሁን ግን ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር ይቀላቀላል፤ በዚህም ምቾትም ይሰማዋል" ትላለች።
መምህርቷ ተማሪ ሳለች ይህን መሰል ትምህርት አግኝታ ቢሆን ትመኛለች።
"ትምህርቱ የተጀመረው ዘግይቶ ነው። አሁን ግን ቅድሚያ የምንሰጠው ትምህርት ሆኗል። ልጆች ስሜታቸውን መቆጣጠር እና ደግ መሆንን ይማራሉ። ከራሳቸውን ባሻገር ለማኅበረሰባቸው የሚያበረክቱም ይሆናሉ" ትላለች።
በጋልሙድግ ግዛት የትምህርት ሚኒስቴር ሞሐመድ ዶሪ ይህ ትምህርት እንዲሰጥ ለማድረግ ጫና አሳድረዋል።
"ተማሪዎች ሲጨነቁ እና የባህሪ ችግር ሲያሳዩ መምህራን አስተውለዋል። ይህም የመማር ክህሎታቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል" ይላሉ።
ትምህርቱ ሲጀምር ብዙም ተቀባይነት እንዳላገኘ ይናገራሉ።
"ትምህርቱ ለሶማሊያ አዲስ ነው። ችግሩ መኖሩን ያወቅነው መምህራኑ ከነገሩን በኋላ ነው። የስሜት ችግር ተማሪዎችን እየጎዳቸው ነበር" ሲሉ ያስረዳሉ።
ትምህርቱ ለሶማሊያ ባህል እንግዳ ነው ያሉ ወላጆች ተቃውሞ ቢያሰሙም በጊዜ ሂደት የትምህርቱን አስፈላጊነት መረዳታቸውን ይናገራሉ።
ስለ ማኅበራዊ ክህሎት እና ስለ ስሜት የሚሰጥ ትምህርት በመላው ሶማሊያ እንዲተገበር ይሻሉ።
"የሰዎችን መሠረታዊ ፍላጎት የሚመለከት ትምህርት ነው። የልጆችን አእምሮ ለማጎልበትና ለወደፊቱ ዓለም ብቁ የሆኑ ታዳጊዎች ለመፍጠር እንደ ብሔራዊ አሠራር መተግበር አለበት" ሲሉ ያስረዳሉ።
ትምህርቱን የሚወስዱ ተማሪዎች በአንክሮ መከታተላቸውን ቀጥለዋል።
አንድ የሰባት ዓመት ታዳጊ "በመጻሕፍቱ ላይ ያሉት ታሪኮች ደስ ይሉኛል" ይላል።
መምህራቸው ታሪኮች ካነበበችላቸው በኋላ ስለ ስሜት ውይይት ለማድረግ በጉጉት ነው ተማሪው የሚጠብቀው።
"የተለያዩ ስሜቶችን እንማራለን። አሁን ከቤተሰቦቼ ጋር ማውራት ቀላል ሆኖልኛል" ይላል።