ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቢቢሲ ድብቅ ቀረጻ በህጻናት ወሲብ ንግድ ውስጥ የሚሳተፉ ኬንያውያን ሴቶችን አጋለጠ
የቢቢሲ አፍሪካ አይ ምርመራ፤ ኬንያ ውስጥ "ማዳም" ተብለው የሚጠሩ ሴቶች እንዴት እስከ 13 ዓመት ዕድሜ ድረስ ያሉ ህጻናትን ለወሲብ ንግድ እንደሚያቀርቡ አጋለጠ።
በኬንያ ሪፍት ቫሊ ውስጥ የሚገኘው ማይ ማሂዩ ከተማ ጎዳናዎች ቀን እና ሌሊት በሚጓዙ የጭነት እና ተሳቢ ተሽከርካሪዎች መተላለፊያ ነው።
እነዚህ ተሽከርካሪዎች ከመላ የሀገሪቱ ክፍሎች የጫኗቸውን ሸቀጦችን እና ሰዎችን ወደ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያጓጉዛሉ።
ከኬንያ ዋና ከተማ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው እና ቁልፍ የትራንስፖርት ማዕከል የሆነችው ማይ ማሂኡ በወሲብ ንግድ ትታወቃለች። ሌላኛው የከተማው ገጽታ ግን የህጻናት ጾታዊ ጥቃት መራቢያ ማዕከልም መሆኑ ነው።
ሁለት ራሳቸውን የደበቁ መርማሪዎች፤ እንዴት 'ማዳም' መሆን እንደሚችሉ ለመማር የመጡ የወሲብ ንግድ ተዳዳሪዎችን መስለው ወራትን በማሳለፍ በከተማው የወሲብ ንግድ ስራን መርምረዋል።
የመርማሪዎቹ ድብቅ ቀረጻ፤ የሚያከናውኑት ተግባር ህገ ወጥ መሆኑን የሚያውቁ ሁለት የተለያዩ ሴቶች በወሲብ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚገኙ እና እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሴት ልጆችን ሲያስተዋውቋቸው አሳይቷል።
ቢቢሲ ያሰባሰባቸውን ማስረጃዎች በሙሉ በመጋቢት ወር ለኬንያ ፖሊስ አስረክቧል። ቢቢሲ፤ ማዳም ተብለው የሚጠሩት ሴቶች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ሌላ ቦታ እንደሄዱ ያምናል።
ፖሊስ ቢቢሲ የቀረጻቸውን ሴቶች እና ሴት ልጆችን ማግኘት አልቻልኩም ብሏል። እስካሁን ድረስም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው የለም።
ኬንያ ውስጥ የወንጀል ተጠያቂነት እምብዛም አይደሉም። ፖሊስ በተሳካ ሁኔታ ክስ እንዲመሰርት የህጻናት ምስክርነት ያስፈልገዋል። ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ህፃናት ደግሞ ብዙውን ጊዜ ምስክርነት ለመስጠት እጅጉን ይፈራሉ።
ቢቢሲ በከተማው ጎዳናዎች በምሽት የቀረጸው ምስል ራሷን ኛምቡራ ብላ የምትጠራ አንዲት ሴትን ያሳያል። በቪድዮው ላይ፤ "አሁንም ልጆች ናቸው፤ ጣፋጭ እየሰጡ እነሱን ማታለል ቀላል ነው" በማለት እየሳቀች ስትናገር ትታያለች።
"ማኢ ማሂዩ ውስጥ የወሲብ ንግድ ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ ነው። በመሰረቱ የሚያቀጣጥሉት የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ናቸው። እኛ የምንጠቀመው በዚህ መንገድ ነው። በማኢ ማሂዩ ውስጥ የተለመደ ትላለች። ለስድስት ወራት "የሰራች" የ13 ዓመት ልጅ እንዳለችም አክላለች።
ኛምቡራ፤ "እድሜያቸው ያልደረሰ ህፃናትን ማግባባት በጣም አደገኛ ነገር ነው። እንዲሁ በግልጽ ወደ ከተማ ማምጣት አይቻልም። በድብቅ የማወጣቸው ምሽት ላይ ብቻ ነው" ስትል ትደመጣለች።
አዋቂ ሰው በፈቃደኝነት የሚያከናውነው የወሲብ ንግድ ተግባር በኬንያ ብሄራዊ ህግ ውስጥ በግልጽ ወንጀል ሆኖ አልተደነገገም። ነገር ግን በብዙ የከተማ አስተዳደሮች ደንቦች የተከለከለ ነው። የናኩሩ ካውንቲ አካል በሆነው በማይ ማሂዩ ውስጥ ድርጊቱ አልተከለከለም።
በሀገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት፤ ከወሲብ ንግድ በሚገኝ ገቢ መተዳደር ህገ ወጥ ተግባር ነው። ይህ የህጉ ድንጋጌ የወሲብ ንግድ ተዳዳሪ በመሆንም ሆነ በሶስተኛ አካልነት ተግባሩን በማመቻቸት ወይም ከወሲብ ንግድ በማትረፍ የሚገኙ ገቢዎችንም ያጠቃልላል።
ከ18 ዓመት በታች የሆናቸውን ልጆች ማዘዋወር ወይም መሸጥ ከ10 ዓመት እስከ እድሜ ልክ ያስቀጣል።
ኛምቡራ፤ ደንበኞቹ ኮንዶም ይጠቀሙ እንደሆነ ስትጠየቅ፤ ብዙውን ጊዜ መከላከያ መጠቀማቸውን እንደምታረጋግጥ አንዳንዶች ግን እንደማይጠቀሙ ተናግራለች።
"አንዳንድ ልጆች የበለጠ ገቢ ማግኘት ይፈልጋሉ [ስለዚህ አይጠቀሙም]። አንዳንዶቹ [እንዳይጠቀሙ] ይገደዳሉ" ብላለች።
በሌላ ጊዜ ደግሞ የሽፋን መርማሪዎቹን፤ ሶስት ሶፋ ላይ እና አንዲት ወንበር ላይ የተቀመጠች ሴቶች ወደሚገኙበት ቤት ይዛቸው ሄዳለች።
ኛምቡራ ክፍሉን ለቅቃ ስትወጣ መርማሪዎቹ ታዳጊዎቹን ለብቻቸው የማነጋገር እድል አግኝተዋል። ልጆቹ በየቀኑ ለወሲባዊ ጥቃት እንደሚጋለጡ ገልጸዋል።
አንዲት ሴት ልጅ፤ "አንዳንዴ ከብዙ ሰዎች ጋር ወሲብ ትፈጽሚያለሽ። ደንበኞቹ ለማሰብ የሚከብድ ነገር እንድታደርጊ ያስገድዱሻል" በማለት ተናግራለች።
በኬንያ የወሲብ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲሰሩ የሚገደዱ ሴቶች ምን ያህል እንደሆኑ የሚያሳዩ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች የሉም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኬንያ የሰብአዊ መብቶች ልምምዶችን በተመለከተ በ2012 ያወጣው ሪፖርት ይህ ቁጥር እስከ 30,000 እንደሚገመት ጠቅሷል።
ሪፖርቱ ቁጥሩን የጠቀሰው፤ ከኬንያ መንግሥት እና አሁን በስራ ላይ ከሌለ 'ኢራዲኬት ቻይልድ ፕሮስቲትዩሽን ኢን ኬንያ' የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት (NGO) ባገኘው መረጃ ላይ ተመስርቶ ነው።
ሌሎች ጥናቶች ደግሞ በተለይም በቱሪስት ሪዞርቶቻቸው በሚታወቁት የሀገሪቱ የባህር ዳርቻዎች ላይ በማተኮር የተወሰነ አካበቢን የሚሸፍን ዳሰሳ አድርገዋል።
'ግሎባል ፈንድ ቱ ኢንድ ሞደርን ስሌቨሪ' የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም በ2022 ባወጣው ሪፖርት በኪሊፊ እና ክዋሌ ካውንቲዎች ውስጥ ቢያንስ 2,500 ህጻናት ተገድደው የወሲብ ንግድ ውስጥ እንደተሰማሩ ደርሶበታል።
ሁለተኛዋ ራሷን የደበቀች መርማሪ፤ ራሷን ቼፕቱ በማለት የምትጠራ ሴትን እምነት ማግኘት የቻለች ሲሆን ግለሰቧም ከእርሷ ጋርም በርካታ ጊዜ ተገናኝታለች።
እንደ ግለሰቧ አገላለጽ፤ እድሜያቸው ያልደረሰ ታዳጊ ልጆችን መሸጥ "ለኑሮ የሚሆን ገቢ እና ምቾች ማግኘት" ነው። "ይህ አይነቱ ንግድ ህገወጥ ስለሆነ የምታከናውኚው በጣም በሚስጥር ነው" ብላለች።
"አንድ ሰው ሴት ልጅ እንደሚፈልግ ከተናገረ ለእኔ እንዲከፍሉኝ እጠይቃቸዋለሁ። ለዚህ ሲሉ ሁል ጊዜም የሚመለሱ ቋሚ ደንበኞቻች አሉን" ስትልም ተናግራለች።
ቼፕቱ፤ በስሯ ያሉትን አራት ሴት ልጆች ለማሳየት መርማሪዋን ወደ አንድ ክለብ ወስዳታለች።
ከሴት ልጆቹ ውስጥ ትንሿ እዚህ ተግባር ውስጥ ስትገባ 13 ዓመቷ እንደነበረች ተናግራለች። ሌሎቹ ደግሞ 15 እንደነበሩ ገልጸዋል።
ቼፕቱ እንደምትናገረው እነዚህ ሴቶች ከሚያመጡት ከእያንዳንዱ ሶስት ሺህ የኬንያ ሽልንግ ውስጥ 2,500 ው ገቢ የሚሆነው ለእሷ ነው።
ሌላ ጊዜ በከተማው ውስጥ በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ በተገናኙ ጊዜ ቺፕቱ፤ ሁለት እድሜያቸው ያልደረሰ ሴት ልጆችን ከመርማሪዋ ጋር ጥላቸው ወጥታ ነበር።
ከልጆቹ አንዷ በአንድ ቀን ውስጥ በአማካይ ከአምስት ወንዶች ጋር ወሲብ እንደምትፈጽም ተናግራለች።
ያለ ኮንዶም ወሲብ እንዲፈጸም ፈቃደኛ ካልሆነች ምን እንደሚፈጠር ለቀረበላት ጥያቄ በሰጠችው ምላሽ፤ ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌለ ገልጻለች።
"[ያለ ኮንዶም ወሲብ] መፈጸም አለብኝ። ያለበለዚያ እባረራለሁ፤ የምሄድበት ቦታም የለኝም። ወላጅ አልባ ነኝ" ስትል አስረድታለች።
የኬንያ የወሲብ ኢንዱስትሪ፤ ወንዶችም ሴቶችም ህጻናትን ለወሲብ ንግድ የሚያመቻቹበት ውስብስብ ዘርፍ ነው።
ማይ ማሂዩ ውስጥ ምን ያህል ልጆች የወሲብ ንግድ ውስጥ እንዲገቡ እንደተገደዱ በትክክል አይታወቅም። 50 ሺህ ነዋሪዎችን በያዘችው በዚች ትንሽ ከተማ ውስጥ ግን እነዚህን ልጆች ማግኘት ቀላል ነው።
'ቤቢ ገርል' ተብላ የምትታወቅ አንዲት የቀድሞ የወሲብ ንግድ ተዳዳሪ በአሁኑ ሰዓት ከወሲባዊ ጥቃት ለሚያመልጡ ሴት ልጆች ማይ ማሂዩ ውስጥ መጠለያ ታቀርባለች።
የ61 ዓመቷ 'ቤቢ ገርል'፤ በወሲብ ኢንዱስትሪው ውስጥ 40 ዓመታትን አሳልፋለች። ለመጀመሪያ ጊዜ ጎዳና ላይ የወጣችው በ20ዎቹ እድሜዋ መጀመሪያ ላይ ነው።
በወቅቱ በባለቤቷ ይደርስባት በነበረው የቤት ውስጥ ጥቃት ምክንያት የሶስት ዓመት ልጇን ይዛ ስትወጣ ነፍሰ ጡር ነበረች።
በከተማው ውስጥ በሚገኘው ቤቷ፤ በህጻንነታቸው ማይ ማሂዩ በሚገኙ 'ማዳሞች' የወሲብ ንግድ ውስጥ እንዲገቡ ተገድደው የነበሩ እና አሁን ያመለጡ አራት ሴቶችን ለቢቢሲ አስተዋውቃለች።
እያንዳንዳቸው ሴት ልጆች ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው፤ ችግር ያለበት ቤተሰብ ውስጥ እንደነበሩ ወይም በቤት ውስጥ ጥቃት ሲፈጸምባቸው እንደነበረ ተናግረዋል።
ሚሼል የተባለች ልጅ፤ በ12 ዓመቷ ወላጆቿን በኤች አይ ቪ አጥታ ወደ ጎዳና ለመውጣት እንደተገደደች ታስረዳለች። አንድ ግለሰብ መኖሪያ ቦታ እንደሰጣት፤ ኋላ ግን ወሲባዊ ጥቃት ይፈጽምባት እንደጀመረ ገልጻለች።
"ስለሚያስተምረኝ በአይነት እንድከፍለው ያደርግ ነበር። ገደቤ ላይ ደረስኩ ነገር ግን ማንም አልነበረኝም" ብላለች።
ከሁለት ዓመት በኋላ አንዲት ሴት አገኘቻት። ማይ ማሂዩ ከተማ ውስጥ 'ማዳም' የሆነችው ይህቺ ሴትም ወደ ወሲብ ንግድ እንድትገባ አስገደደቻት።
ናኩሩ፤ ከፍተኛ የኤች አይ ቪ ተጠቂዎች የሚገኙበት የኬንያ ካውንቲ ነው። ከአሜሪካው የእርዳታ ድርጅት ዩኤስ ኤይድ ድጋፍ የምታገኘው ቤቢ ገርል፤ ልቅ ወሲብ የሚያመጣውን አደጋ የማስተማር ተልዕኮ ላይ ነች።
በካራጊታ የማህበረሰብ ጤና ማዕከል ውስጥ በሚገኘው ቢሮዋ፤ ኮንዶም እና የምክር አግልግሎት ታቀርባለች።
ይሁን እንጂ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የዩኤስ ኤይድን የገንዘብ ድጋፍ እንዲቆም ማደረጋቸውን ተከትሎ፤ የእርዳታ ፕሮግራሞቿ ሊቆሙ ነው።
"ከመስከረም ወር ጀምሮ ስራ አጥ እንሆናለን" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። በእርሷ ላይ ጥገኛ የሆኑ ሴቶች እና ሴት ልጆች እጣ ፋንታ እንደሚያሳስባትም አክላለች።
"እነዚህ ልጆች ምን ያህል ተጋላጭ እንደሆኑ አይታችኋል። እንዴት በራሳቸው ሊጋፈጡት ይችላሉ? ገና በመዳን ላይ ናቸው" ስትል ስጋቷን ገልጻለች።
አሜሪካ መንግስት የእርዳታው መቋረጥ የሚኖረውን ተፅእኖ በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም። የዩኤስ ኤይድ ባለፈው ወር በይፋ ተዘግቷል።