ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ጦር ለሶማሊያ ወታደሮች ሰጠ የተባለው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?
በሶማሊያ ጌዶ ክልል የሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ወታደሮች በቅርቡ ከያዙት የድንበር ከተማ፣ በለድ ሀዋ በሦስት ቀን ውስጥ ለቅቀው እንዲወጡ ለአገር ሽማግሌዎች መናገራቸው ተገለፀ።
በለድ ሀዋ ቁልፍ የሶማሊያ የድንበር ከተማ ስትሆን ኢትዮጵያን እና ኬንያን የምታዋስን እና የኢትዮጵያ ሠራዊት የሚገኝባት ነች።
ባለፉት ሳምንታት የሶማሊያ የከፊል ራስ ገዝ ክልል ጁባላንድ ታጣቂዎች እና የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ወታደሮች በአካባቢው ውጊያ አካሂደው፣ የሶማሊያ መንግሥት ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም. ከተማዋን በቁጥጥሩ ስር አውሏል።
ከፍተኛ የኢትዮጵያ ወታደራዊ መኮንኖች ከሶማሊያ የጎሳ መሪዎች ጋር በዶሎ ከተማ መነጋገራቸውን እና የሶማሊያ ፌደራል መንግሥቱ ወታደሮች ከበለድ ሀዋ በሦስት ቀን ውስጥ ለቅቀው እንዲወጡ ማዘዛቸውን የአገር ሽማግሌዎች ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።
በሶማሊያ የፌደራል መንግሥት የጌዶ አስተዳዳሪ የሆኑት አብዱላሂ አብዲ ጃማ (ሺምቢር) በዶሎ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት በበለድ ሀዋ የሚገኘውን የሶማሊያ መንግሥት ኃይል በሦስት ቀናት ውስጥ ለቅቆ እንዲወጣ በአገር ሽማግሌዎች እንደተነገራቸው ገልፀዋል።
የጌዶ አስተዳዳሪ አብዱላሂ አብዲ ጃማ (ሺምቢር) ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በጥምረት የሚሠራ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ሠራዊት በኩል ተላለፈ በተባለው ትዕዛዝ ምክንያት ከበለድ ሀዋ የሚወጣ የፌደራል ጦር የለም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
አሁን ተፈጠረ የተባለው ሁኔታ ያጋጠመው ሻክሮ የነበረው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት እየተሻሻለ ኢትዮጵያ አዲስ አምባሳደር በሾመችበት ወቅት ነው።
በአካባቢው ተሰማርቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር አዛዦች የዶሎ ሽማግሌዎችን ሰብስበው የሶማሊያ ጦር በተጨማሪ በለድዌን ለቅቆ እንዲወጡ የሦስት ቀን ጊዜ እንደሰጧቸው ተናግረዋል።
ከቀናት በፊት በአብዲሪሺድ ጃናን የሚመራው የፌደራል መንግሥት ጦር ከጁባላንድ ጦር ጋር ለቀናት የዘለቀ ውጊያ ካካሄደ በኋላ የበለድዌ ከተማ አስተዳደርን ተረክቧል።
"ይህ እውነት ነው። ባለሥልጣናት ትናንት [ማክሰኞ ሐምሌ 29 2017 ዓ.ም.] የዶሎው የአገር ሽማግሌዎችን ሰብስበው ስለ ጉዳዩ አነጋግረዋቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች [የሶማሊያ ጦር] ቦታውን ለቅቆ እንዲወጣ የሦስት ቀናት ቀነ ገደብ ሰጥተዋል። ልቀቁ የሚሉት ቦታ የሶማሌ መሬት ነው" ብለዋል አስተዳዳሪው።
ቢቢሲ በአገር ሽማግሌዎቹ እና በኢትዮጵያ ሠራዊት አዛዦች መካከል ተደረገ ስለተባለው ስብሰባ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
የጌዶ አስተዳዳሪ የሆኑት አብዱላሂ አብዲ ጃማ ውይይቱ መደረጉን አስረግጠው ሲናገሩ "ሽማግሌዎቹ አሉ፤ የከተማዋ ሰዎች ናቸው። የምናውቃቸው ሰዎች ናቸው" ብለዋል።
አክለውም የኢትዮጵያ ወታደራዊ መኮንኖች ከአገር ሽማግሌዎቹ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት፣ "ግብፆች እየመጡ እንደሆነ፣ እንዲሁም ሌሎች ወታደሮችም እየመጡ እንደሆነ እናውቃለን፤ እንዲሁም አብዱራሺድ ጃነንን [በአካባቢው የሚገኘውን የሶማሊያ መንግሥት ጦር የሚመራው] በስም ጠቅሰው ነው የተናገሩት" ብሏል።
ከኢትዮጵያ ወታደራዊ አዛዦች ጋር የተገናኙት የአገር ሽማግሌዎች የተሰጠውን የሦስት ቀናት ገደብ በተመለከተ በመካከላቸው መከፋፈል ተፈጥሮ እንደነበር የጌዶ አስተዳዳሪ ይናገራሉ።
"ሽማግሌዎቹ ተከፋፈሉ፣ ብዙዎች ግብፃውያንን አላየንም አናውቃቸውም ብለው ነበር። ሰውየውም [አብዱራሺድ ጃነንን] ሆነ ወታደሮቹ የመንግሥት ኃይሎች ናቸው። በገዛ አገራቸው ነው ያሉት። ይውጡ የምትሉት እናንተ ናችሁ። እኛ ውጡ የምንልበት ምንም ምክንያት የለም" ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ተናግሯል።
አስተዳዳሪው አክለውም በአካባቢው የተከሰተውን ሁኔታ ለሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።
የጌዶ ክልል አስተዳዳሪ የሆኑት አብዱላሂ አብዲ ጃማ ከኢትዮጵያ ሠራዊት በኩል ለተሰጠው ትዕዛዝ "የእኛ ምላሽ በአገራችን ውስጥ ነን። ጣልቃ ገብነትን አንቀበልም" ማለታቸውን ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።
"ሰዎቹ [ወታደራዊ መኮንኖቹ] የኢትዮጵያ መንግሥትን እንደሚወክሉ አናውቅም። ግንባር ላይ ያሉ መኮንኖች ናቸው፣ በድንበር ላይ ያሉት መኮንኖች በተደጋጋሚ ትክክል ያልሆነ ነገር ይሠራሉ። ይህ እርምጃ የኢትዮጵያ መንግሥት መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ሃሳቡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የወታደራዊ መኮንኖቹ አንቀበለውም።"
በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት የተሾሙት የጌዶ አስተዳዳሪ እንዳሉት ከአገር ሽማግሌዎች ጋር የተገናኙት የኢትዮጵያ ሠራዊት መኮንኖች "የግብፅ እና የኤርትራ ወታደሮች ወደ ክልሉ እየመጡ ነው" ሲሉ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።
የጁባላንድ ምክትል ፕሬዝዳንት ሙሐሙድ ሰይድ አደን ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በክልሉ የሞቃዲሾ መንግሥት በዚህ ክልል ሊተገብረው የሚፈልገው ዓላማ አለ።... በመንግሥታት መካከል ያለው ልዩነት ወደ ክልላችን እንዳይዛወር ለማድረግ እየጣርን ነው። የኤርትራ እና የግብፅን ሃሳብ ወደ ግዛቱ ለማምጣት እየፈለጉ ይመስላል" ሲሉ የጌዶ አስተዳዳሪን ተችተዋል።
የጁባላንድ ምክትል ፕሬዝዳንት ሙሐመድ ሰይድ አደን የሰጡትን ሃሳብ አስመልክቶ የጌዶ አስተዳዳሪ ሲናገሩ "የግብፅ እና የኤርትራ ወታደሮች በሶማሊያ ውስጥ የት እንዳሉ አላውቅም፤ ነገር ግን በእርግጠኝነት በጌዶ ውስጥ የሉም። ይህን እያለ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፤ ይህ የውሸት ዜና ነው" ብለዋል።
አስተዳዳሪው በአሁኑ ወቅት በጌዶ ወረዳዎች እና ከተሞች ስላሉ አካላት ሲናገሩ በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት እና በጁላንድ መሪዎች መካከል ያለውን የሥልጣን ሽኩቻን አንስተዋል።
በዚህም የግዛቲቱ አስተዳዳሪ የሆኑት የአህመድ ማዶቤን አስተዳደር በመተቸት " ከዶሎ በስተቀር ሁሉም ከተሞች በእኛ ቁጥጥር ስር ናቸው" ሲሉ በአካባቢው የፌደራል መንግሥቱ ያለውን የበላይነት ገልጸዋል።
የሶማሊያ መንግሥት በበኩሉ በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት ትናንት ረቡዕ ባወጣው መግለጫ የጁባላንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ግጭት በመቀስቀስ ወንጅሏል።
"የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት በአህመድ ማዶቤ የሚመራው ቡድን በጌዶ ክልል ግጭት ለመቀስቀስ እንዲሁም የሠራቸውን ወንጀሎች ለመሸፈን ሐሰተኛ እና አሳሳች መረጃ ለማሠራጨት እየሞከረ መሆኑን ያውቃል" ሲል ሚኒስቴር ከስሷል።
በመግለጫው ላይ በስም የተጠቀሱት የፑንትላንድ ምክትል አስተዳዳሪ ሙሐሙድ ሰይድ አደን ከዚህ ቀደም በጌዶ ግዛት በተፈጸሙ በርካታ ወንጀሎች እጃቸው አለበት ብሏል።
የኢትዮጵያ ጦር በዶሎ ለሚገኙ የሶማሊያ የአገር ሽማግሌዎች ሰጠ ስለተባለው የሦስት ቀናት ማስጠንቀቂያን በተመለከተ ቢቢሲ ሶማሊኛ ከኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናት በጽሑፍ እና በስልክ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።