ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማራላጎ፡ ሥልጣን ፈላጊዎች የሚያንዣብቡበት ቅንጡው የዶናልድ ትራምፕ ጎልፍ መጫወቻ እና መዝናኛ
ፍሎሪዳ የሚገኘው ቅንጡው የዶናልድ ትራምፕ መዝናኛ እና መኖሪያ ድጋሚ ነቃ ነቃ ብሏል።
ማራላጎ የተሰኘው ትራምፕ ጎልፍ የሚጫወቱበት ሰፊ ግቢ አዲሱን አስተዳደራቸውን የሚያዋቅሩበት እንደሚሆንም ይገመታል።
በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እስከሚመጣው ጥር ድረስ ሥልጣን ላይ ይቆያሉ። ነገር ግን በሚመጡት ሳምንታት መገናኛ ብዙኃን ትኩረት የሚሰጡት ለዋይት ሐውስ ሳይሆን ለማራላጎ ይሆናል።
ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር ኤፍቢአይ (የአሜሪካ ፌዴራል ምርመራ ቢሮ) ወደ ማራላጎ አቅንቶ ምሥጢራዊ የሚባሉ ስለኒውክሌር መሣሪያ እና ስለላ የተሰናዱ መዛግብትን ከመጸዳጃ ቤት ፈልፍሎ ያወጣው።
ይህ ሰፊ የመዝናኛ እና የመኖሪያ ግቢ በሮቦት ውሾች እና በታጠቁ ጥበቃዎች ቀን ከሌት ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግለታል።
የኢነርጂ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት የሰሜን ዳኮታው ሀገረ-ገዥ ዳግ በርገም በምርጫው ቀን እዚህ ነበሩ። የቀድሞው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ኃላፊ ካሽ ፓቴልም እዚህ ነበር ያመሹት።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ሀብታሙ ሰው ኢላን መስክ ከዶናልድ ትራምፕ አጠገብ ተቀምጦ የምርጫውን ውጤት ሲጠባበቅ ታይቷል። የትራምፕ ቤተሰብ ተሰባስቦ በምርጫው ምሽት እራት የበላው ማራላጎ ነው።
ግቢው የሌለው ነገር የለም። ኢላን መስክ ከልጁ ጋር እዚህ ግቢ ውስጥ ሲንሸራሸር ታይቷል። ለጥቂቶች ብቻ የሚከፈተው ክለብ ውስጥም ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ሲመክር ፎቶግራፍ ተነስቷል።
ወደ ማራላጎ ለመግባት ግብዣ ያላገኙ ደግሞ ወጣ ብለው ዌስት ፓልም ቢች ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባሉ ሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች ሰፍረዋል። አብዛኞቹ በተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አዲሱ አስተዳደር ሥር ሥልጣን ለማግኘት የሻቱ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
በክትባት የማይምኑት እና የጆን ኤፍ ኬኔዲ ዘመድ የሆኑት ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር ማራላጎ አቅራቢያ ከሚገኘው ዘ ቤን ሆቴል ውስጥ ነበሩ።
ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር በአንድ ወቅት በግላቸው የአሜሪካ ፕሬዝንደንት ለመሆን ሲወዳደሩ ነበር። ነገር ግን አሁን የጤና ሚኒስትርነት ቦታ ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ጭምጭምታዎች መሰማት ጀምረዋል።
ከዲሞክራትነት ወደ ሪፐብሊካን ፓርቲ የመጡት የኮንግረስ አባሏ ቱልሲ ጋባርድ እና ሮበርት ከምርጫው በፊት በጋራ ለትራምፕ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር።
ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር “የተለያየ ርዕዮተ ዓለም ያላቸው ሰዎች አሉ። በሽግግር መንግሥቱ ሥር የተለያዩ ራዕዮች ያሏቸው ሰዎች ሊካተቱ ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሌላኛዋ በአወዛጋቢ ንግግራቸው የሚታወቁት ሪፐብሊካኗ ማርጆሪ ቴይለር ግሪንም እዚሁ ዘ ቤን ሆቴል ናቸው። የኮንግረስ አባሏ በቅርቡ በሰሜን ካሮላይና ለተከሰተው ጎርፍ የባይደን አስተዳደርን መውቀሳቸው አይዘነጋም። ማርጆሪም እንዲሁ በትራምፕ ካቢኔ ውስጥ ለመካተት አልመዋል የሚሉ ብዙዎች ናቸው።
እዚያው ማራላጎ አቅራቢያ ያለው ሌላኛው ሆቴል ደግሞ ዘ ብሬከርስ ነው። ይህ የጣሊያን የአብርሆት ዘመን ሕንፃዎችን ዲዛይን ይዞ የተገነባው ሆቴል ደረቱን ለውቅያኖሱ ሰጥቶ የቆመ ነው።
እዚህ ሆቴል ውስጥ ደግሞ ዩኤፍሲ የተሰኘው የቡጢ ውድድር ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳና ዋይት ይታያል። ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ባወጁበት ምሽት ንግግር ሲያደርጉ አጠገባቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ ዳና ዋይት ነበር። በዚያው ምሽት ንግግር ያሰማው ዳና ፖለቲካዊ ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት የለኝም ይላል።
ሌሎቹ እነዚህ ውድ ሆቴሎች ውስጥ ተቀምጠው ትራምፕን የሚጠባበቁ ግለሰቦች ግን ሥልጣን አይፈልጉም ማለት ከባድ ነው። አንድ የሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ አዋቂ የሽግግር መንግሥቱ “ለሁሉም ክፍት” የሆነ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
“ትራምፕ ሰዎች ለሥልጣን ሲታገሉ እና ለሳቸው ሲያሸረግዱ ማየት ደስ ይላቸዋል።”
ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ የመጡ ግለሰቦቸን ለነባር ቦታዎች ያጩ ይመስላሉ።
ልጃቸው ዶን ጁኒየር እንደሚለው አባቱ የሚፈልጓቸው ሰዎች “እኔ የተሻለ አውቃለሁ” የማይሉ መሆን አለባቸው። አክለው አባታቸው ወደፊት ችግር ሊያመጡባቸው የሚችሉ ሰዎችን እንደማይቀበሉ ለፎክስ ኒውስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ይናገራሉ።
ተመራጩ ፕሬዝደንት በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ከቀድሞው በተለየ መንገድ ማስተዳደር እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። በተለይ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የሠሩት ትልቅ ስኅተት “መጥፎ አሊያም የማይታመኑ ሰዎችን” መቅጠራቸው እንደሆነ ይገልፃሉ።
በአውሮፓውያኑ 2016 ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ሲመጡ ሥልጣን ሲሰጡ የነበረው ትራምፕ ታወር በተሰኘው ሕንፃቸው ውስጥ ወዳለ ቢሮ እየጠሩ ነበር። በወቅቱ መገናኛ ብዙኃን ካሜራቸውን ተክለው በወርቃማው አሳንሰር ወደ 26ኛው ፎቅ የሚወጡ ሰዎችን ሲከታተሉ እንደነበር ይታወሳል።
አሁን ትራምፕ ታማኝነት መመሪያቸው ያደረጉ ይመስላል። ከመጀመሪያው ጀምሮ ከሳቸው ጋር የነበሩ ሰዎችን ነው ሊሾሙ የሚችሉት የሚል እሳቤ አለ።
በዚህኛው ዙር መገናኛ ብዙኃን ፊታቸውን ወደ ማራላጎ አዙረዋል። በማራላጎ ዙሪያ ያሉ ሆቴሎች በካሜራ እና ፎቶ አንሺዎች ተጨናንቀዋል። የፀጥታ ሰዎች በየቦታው ሲዘዋወሩ ይታያሉ።
የመጀመሪያዋ የትራምፕ ተሿሚ የፍሎሪዳዋ የፖለቲካ አማካሪ ሱዚ ዋይልስ ናቸው። ሱዚ የዋይት ሐውስ ኃላፊ (ቺፍ ኦፍ ስታፍ) ሆነው ነው የተሾሙት።
ትራምፕ በፍሎሪዳ ግዛት ፓልም ቢች በተባለው ሥፍራ የሚገኘውን ማራላጎ የመዝናኛ እና የመኖሪያ ቅንጡ ቦታን የገዙት በ1980ዎቹ ነው። በወቅቱ የፍሎሪዳ ሰዎች በትራምፕ ድርጊት ብዙም ደስተኛ አልነበሩም።
አሁን ወደ ከተማዋ ለሚመጣ ሰው በግልፅ የሚታየው አንድ ነገር ቢኖር ሥፍራው የትራምፕ ግዛት መሆኑን ነው። እዚህ አሜሪካንን መልሶ ታላቅ ማድረግ (ማጋ፣ ሜክ አሜሪካ ግሬት ኧጌይን) የሚል መፈክር ያለበት ኮፍያ እና የዋና ልብስ መመልከት ብርቅ አይደለም።
በሚቀጥለው ሳምንት የአርጀንቲው ፕሬዝደንት ጃቪዬ ሚሌ ወደ ማራላጎ መጥተው ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና ኢላን መስክን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።
እንዲሁ በቀጣዩ ሳምንት ሲፓክ የተሰኘው የወግ አጥባቂ ፓርቲ ዓመታዊ ጉባዔ የሚካሄደው በማራላጎ ሲሆን፣ የመግቢያ ቲኬት ዋጋ 25 ሺህ ዶላር እንደሚሆን ይገመታል።
የፖለቲካ ተንታኞች ትራምፕ በሚመጣው የሥልጣን ዘመናቸው አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉት ዋይት ሐውስ ሳይሆን ማራላጎ ነው የሚል ግምት አላቸው።
58 ሺህ ስኬዌር ሜትር የሚሰፋው ማራላጎ በአሜሪካ ፖለቲካ ታሪክ ከዋይት ሐውስ ቀጥሎ እጅግ የገነነው ግቢ የመሆኑ ነገር የሚያጠራጥር አይደለም።