ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ ውስጥ ተሰርቃ ከ50 ዓመታት በኋላ ጠፍታ የነበረች ልጅ ከወላጆቿ ጋር ተገናኘች
በህጻንነቷ ተሰርቀው ከ50 ዓመታት በላይ ከቤተሰቧ ተለያይታ የቆየችው አሜሪካዊት ሴት በዘረ መል (ዲኤንኤ) ምርመራ አማካይነት ከትክክለኛ ወላጆቿ ጋር ተገናኘች።
የ53 ዓመቷ ሜሊሳ ሃይስሚዝ፣ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1971 ሁለት ዓመት ሊሞላት ሁለት ወር ሲቃረት ነበር በሞግሪቷ ተሰርቃ የተወሰደችው።
በቴክሳስ ግዛት ውስጥ ከምትገኘው ፎርት ዎርዝ ከተማ ከ50 ዓመታት በፊት በጨቅላነቷ ከቤተሰቧ የተነጠለችው ሜሊሳ በአዛውነትነት እድሜዋ ነው ከቤተሰቦቿ ጋር የተገናኘችው።
ሜሊሳ ከተሰረቀች በኋላ ቤተሰቦቿ ለዓመታት ልጃቸውን በእጃቸው ለማስገባት ጥረት ቢያደርጉም ውጤት ሳያገኙ አምስት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል።
አሁን ግን የቤተሰብ ግንድን ለመለየት ለሚያግዘው ድረ ገጽ የተላከ የዘረ መል ናሙና የሚመሳሰለው ዘረ መል በመገኘቱ አዛውንቷ ሜሊሳ ቤተሰቧን አግኝታለች።
ለረጅም ጊዜ “ሜላኒ” በሚል ስም ስትጠራ የቆየችው ሜሊሳ ሃይስሚዝ አሁን ስሟን ለመቀየር አቅዳለች።
ይህ ለዘመናት ሳይፈታ የቆየው የቤተሰብ ምስጢር የጀመረው በነሐሴ ወር 1971 (እአአ) ነበር። በዚህም በወቅቱ እናት አልታ አፓቴንኮ በአንድ የአካባቢው ጋዜጣ ላይ ማስታወቂያ አስወጥታ ለልጇ ሞግዚት ቀጠረች።
ህጻኗን ጠልፋ ተሰውራለች የተባለችው ሞግዚቷም ከእናት ጋር ልጇን በእራሷ ቤት ውስጥ ለመንከባከብ ቃል ገብታ ተስማምተው ነበር።
ነገር ግን ሞግዚቷ ከህጻኗ ጋር በመሰወሯ ለአምስት አስርት ዓመታት የዘለቀ ፍለጋ በቤተሰቧ፣ በፖሊስ እና በፌደራል ባለሥልጣናት ሲደረግ ቆይቷል።
ተስፋ ያልቆረጠው ቤተሰብ ፍለጋውን ከ50 ዓመታት በላይ የቀጠለ ሲሆን፣ ባለፈው መስከረም ወርም ሜሊሳ ደቡብ ካሮላይና ውስጥ እንደምትገኝ ባገኙት ፍንጭ ክትትል ሲያደርጉ ነበር።
ዓመታት እየተፈራረቁ ፍለጋውም በቀጠለበት ጊዜ ስሟ ወደ ሜላኒ ዋልደን የተቀየረው ሜሊሳ ሃይስሚዝ እሷን ለማግኘት እየፈለጋት ያለ ቤተሰብ እንዳላት ፈጽሞ አታውቅም ነበር።
ቤተሰቧ ያሉ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም ልጁን ሲፈልግ ቆይቷል። በአንድ ወቅት በፌስቡክ በኩል ሜሊሳን ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ወደ ልጃቸው ዘንድ ቢያደርስም፣ እሷ ግን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚደረግ ማጭበርበር ነው ብላ አስባ ነበር።
በመጨረሻም በዘረ መል ምርመራ አማካይነት የተጠፋፉ ቤተሰቦችን የሚያገናኘው “23ኤንድሚ” የተባለው ድረገጽ የግማሽ ክፍለ ዘመኑን ምስጢር ፈትቶታል።
የዘር ግንድን በማጥናት ሙያ ላይ በተሰማሩ አማተር ባለሙያዎች ድጋፍ ውጤቱን በመረዳት የሜሊሳ ልጆች ከቀሪው ቤተሰባቸው ጋር ለመገናኘት ችለዋል።
ቤተሰቡም በፖሊስ ወይም በሌላ መንገድ ሳይሆን ከሜሌሳ ጋር “ባላቸው ዘረ መል ምክንያት” ጥርት ባለ ሁኔታ ልጃቸው መሆኗን ማረጋገጣቸውን በፌስቡክ ገጽ ላይ አስፍረዋል።
በዚህም መሠረት ሜሌሳ ሃይስሚዝ እና ቤተሰቧ ከ50 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተዋል። ቤተሰቡ ጨምሮም የበለጠ ማረጋገጫ ለማግኘት ተጨማሪ “ይፋዊ እና ሕጋዊ የዘረ መል ምርመራ” አድርጎ ውጤቱን እየተጠባባቀ ነው ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው በኩል ገልጸዋል።
ሜሊሳ ሃይስሚዝ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ እንደተናገሩት ውጤቱ “በዓለም ላይ ካሉ አስደሳች ስሜትን ከሚፈጥሩ ነገሮች ሁሉ የላቀ ነው” ብለዋል።
የሜሌሳ ትክክለኛ እናት አፓቴንኮ ልጃቸውን ከ50 ዓመታት በኋላ ሲያገኙ፣ ቤተሰባቸው ከዘመናት በኋላ መገናኘቱን “ለማመን አልቻልኩም” ብለዋል።
“ልጄን በሕይወት እያለሁ መልሼ አያታለሁ ብዬም አላሰብኩም ነበር” ሲሉ አክለዋል።
ከዚሁ ክስተት ጋር በተያያዘ ልጅቷን ጠልፋ ስለወሰደቻት ሞግዚት ግን ምንም የተባለ ነገር የለም። ሜሌሳ እንዳለችው ሰርቃ ያሳደገቻት ሴት ከምታሳያት አያያዝ እና ሁኔታ አንጻር እንቷ አለመሆኗን እያወቀች እንደነበር ገልጻለች።
ፖሊስ የህጻኗን የጠለፋ ጉዳይ የመከታተል በሕግ የተሰጠው የጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ ረጅም ጊዜ ቢሆነውም፣ ምን እንደተከሰተ ለማወቅ ያሉ መረጃዎችን በማገጣጠም ምርመራውን እንደሚቀጥል የፎርት ዎርዝ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እናዳለ ከ50 ዓመታት በላይ የጠፋች ልጁን ያገኘው ቤተሰብ ለመተዋወቅና ትስስሩን ለማጠናከር ጥረት እያደረገ ነው።
የሜሊሳ እህቶች ለዋሽንግተን ፖስት እንደተናገሩት ስሟን ለመቀየር፣ አባቷ እና ቤተሰቧ እንዲታደሙ እንዲሁም አስፈላጊው ሥነ ሥርዓት በወላጆቿ እንዲፈጸም የሠርግ ሥነ ሥርዓቷን ከባለቤቷ ጋር በድጋሚ ለማድረግ አቅዳለች።