ትራምፕ በአትላንታ ከታሰሩ በኋላ በፖሊስ የተነሱት ታሪካዊ ፎቶ ተለቀቀ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በፖሊስ የተነሱት ፎቶ
የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በፖሊስ የተነሱት ፎቶ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የ2020 የጆርጂያ ግዛት ምርጫ ውጤት ለመቀልበስ አሲረዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ተከትሎ በጆርጂያ፣ አትላንታ ከታሰሩ በኋላ በፖሊስ የተነሱት ፎቶ ይፋ ተደረገ።

ትራምፕ አትላንታ በሚገኘው እስር ቤት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በ200 ሺህ ዶላር የገንዘብ ዋስ ተለቀዋል።

ከእስር ከወጡ በኋላም ውሳኔውን “ኢ-ፍትሃዊ” ብለውታል።

ትራምፕ በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን በፖሊስ ፎቶ ሲነሱ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ትራምፕ በኋላ ላይም በቀድሞ ስሙ ትዊተር በአሁኑ ኤክስ በሚባለው የማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ከአውሮፓውያኑ ጥር 2021 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ጽሑፍ አጋርተዋል።

ባጋሩት መልዕክትም በፖሊስ የተነሱትን ፎቶ፣ የድረ ገጻቸውን አድራሻ እና “የምርጫ ጣልቃ ገብነት! በፍጹም እጅ አንሰጥም” የሚል ጽሑፍ አስፍረዋል።

የቀድሞ ፕሬዝደንቱ የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው ሲሉ ተከራክረዋል። ትራምፕ በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዲሞክራት የሆኑትን ፕሬዚደንት ጆ ባይደንን ለመገዳደር የሪፐብሊካኖችን ውድድር እየመሩ በመሆኑ የተከፈተባቸው ክስ እንደሆነም አስረድተዋል።

በወንጀል የተከሰሱት የመጀመሪያው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ሐሙስ ዕለት ከሰዓት በግል ጄታቸው ከኒውጀርሲ የደርሶ መልስ ጉዞ ያደረጉ ሲሆን፣ ወደ ፉልተን ካውንቲ እስር ቤት የተወሰዱትም በዚህ ዓመት የፍርድ ቤት ችሎቶች ለመገኘት ከሆነው በተለየ መልኩ በከፍተኛ አጀብ ነበር።

በእስር ቤቱ ውስጥም ለ20 ደቂቃ ያህል ቆይተዋል። በርካታ ደጋፊዎቻቸውም ደጅ ላይ ተሰብስበው ሲጠባበቁ ነበር ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በእስር ቤቱ ድረ ገጽ ላይ የወጣው መረጃም ትራምፕ ቀለማቸው ነጭ፣ ጾታቸው ወንድ ፣ ክብደታቸው 97 ኪሎ ግራም ፣ ጸጉራቸው ወርቃማ እና ዐይኖቻቸው ሰማያዊ ቀለም እንዳላቸው ገልጿል።

በእስር ቤት ፒኦ1135809 የሚል የእስረኛ መለያ ቁጥርም ተሰጥቷቸው ነበር።

ትራምፕ በገንዘብ ዋስ ከእስር ተለቀው ወደ ቤታቸው ከማቅናታቸው በፊትም አየር ማረፊያ ለነበሩ ጋዜጠኞች የምርጫ ውጤትን የመቃወም መብት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ብዙ ጊዜ የ2020 ምርጫ ስለመጭበርበሩ የሚናገሩት ትራምፕ “ምንም የሰራሁት ስህተት የለም። ምርጫው የተጭበረበረ፣ የተሰረቀ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህንን ለማለት ሙሉ መብት አለኝ፤ ሊኖረኝም ይገባል” ብለዋል።

“እንደምታውቁት ሒላሪ ክሊንተን ወይም የቀድሞዋ እጩ የጆርጂያ ገዥ ስቴሲይ አብርሃምስ ወይም ሌሎች ብዙ ሰዎች ላለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ነገር ሲያደርጉ እንደነበር እየተመለከታችሁ ነው" ብለዋል ትራምፕ ለጋዜጠኞች በተናገሩበት ወቅት።

ትራምፕ ከሌሎች 18 ተከሳሾች ጋር ክስ የቀረበባቸው ባለፈው ሳምንት ነበር።

ትራምፕና ሌሎቹ ተከሳሾች እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 የተካሄደውን ምርጫ ባይደን በጆርጂያ ውጤት እንዲያጡ እና ሌላ ውጤት እንዲመጣ አሲረዋል በሚል ነበር ክስ የቀረበባቸው።

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ብራድ ራፍንስፕሬገር ከተባሉ የጆርጂያው ሪፐብሊካን ባለስልጣን ጋር ባደረጉት የስልክ ልውውጥ በደምጽ ቆጠራ ወቅት 11 ሺህ 780 ድምጾችን እንዲፈልጉ ሲጠይቋቸው ተሰምቷል።

በሥልጣን ላይ ያለ ወይም የነበረ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሦስት የወንጀል ክስ ሲቀርብበት ትራምፕ የመጀመሪያው ናቸው።

እሳቸው ግን ምንም ጥፋት የለብኝም ብለው የሚከራከሩ ሲሆን ክሶቹም ፖለቲካዊ ፍላጎት የተጫናቸው ናቸው ይላሉ።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሪፐብሊካኖችን እየመሩ ሲሆን በ2024 ለሚደረገውና ባይደን ለሚሳተፉበት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ።