ትራምፕ “ሕዝቡ ያውቀኛል” ሲሉ በፓርቲያቸው የምርጫ ክርክር ላይ እንደማይሳተፉ አሳወቁ

45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, ICON SPORTSWIRE VIA GETTY IMAGES

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲያቸው በሚያዘጋጀው የዕጩ ፕሬዝዳንቶች ክርክር ላይ እንደማይገኙ አሳውቀዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት እንደሚሉት ከምርጫው በፊት የተሰበሰቡ ድምፆች እሳቸው “በታላቅ” ብልጫ የፓርቲ ተፎካካሪዎቻቸውን እንደሚቀድሙ ያሳያሉ።

“ሕዝቡ ማን እንደሆንኩ ያውቃል። ምን ዓይነት ስኬታማ ፕሬዝዳንት እንደነበርኩም አይጠፋውም” ሲሉ የ77 ዓመቱ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ላይ ፅፈዋል።

የመጀመሪያው የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ክርክር ከሁለት ቀናት በኋላ በመጪው ረቡዕ ነሐሴ 23/2023 (እአአ) ይካሄዳል።

ሁለተኛው ደግሞ በሚቀጥለው ቀን እንደሚካሄድ ሲጠበቅ በሚቀጥሉት ወራት ደግሞ ቢያንስ ሁለት ክርክሮች ይጠበቃሉ።

ማን የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆኖ ይወዳደር የሚለውን ለመለየት ድምፅ አሰጣጥ በአዮዋ ግዛት ጥር 15/2024 (እአአ) ይከናወናል።

ማን ይወክል የሚለውን ውሳኔ ለማቅለል ግን ከዚያ በፊት በርከት ያሉ ክርክሮች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል።

በቅርብ ጊዜያት የተሰበሰቡ ድምፆች በርካታ የወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው ዶናልድ ትራምፕ ተፎካካሪዎቻቸውን እየመሩ እንደሆነ ያሳያሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትሩዝ ሶሻል የተሰኘው እና የራሳቸው ንበረት በሆነው ማኅበራዊ ሚድያቸው ላይ እሑድ ዕለት ሃሳባቸውን የገለጹት ትራምፕ “ሲቢኤስ [የአሜሪካ ሚድያ] ያወጣው አዲስ የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ እንደሚያሳየው እኔ ፉክክሩን “በታላቅ” ቁጥር እየመራሁ ነው” ብለዋል።

አክለውም ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት የፍሎሪዳው አገረ ገዢ ሮን ዴሳንቲስ እንኳ ወደኋላ ቀርተዋል ሲሉ ሸንቆጥ አድርገዋል።

“ሕዝቡ ማን እንደሆንኩ ያውቃል። ምን ዓይነት ስኬታማ ፕሬዝዳንት እንደነበርኩም አይጠፋውም። የኢነርጂ ነፃነት አምጥቻለሁ፣ ጠንካራ ድንበር እና ወታደር መሥርቻለሁ፣ ትልቁን ቀረጥ ተግባራዊ አድርጊያለሁ፣ የኑሮ ውድነት አጥፍቼ አሜሪካንን በታሪክ ጠንካራ ምጣኔ ሃብት ያላት አገር አድርጊያለሁ ሌላም ብዙ ብዙ።”

ይሄን ያሉት ትራምፕ “ስለዚህ በክርክሩ አልሳተፍም” ሲሉ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል።

ትራምፕ በቅርብ ጊዜያት በፓርቲያቸው የምረጡኝ ክርክር ላይ እንደማይሳተፉ በተደጋጋሚ ሲጠቁሙ ነበር።

ለዚህ ደግሞ እንደ አንድ ምክንያት የሚያቀርቡት የተለያዩ ድርጅቶች ከሕዝብ በሚሰብስቧቸው የሕዝብ አስተያየት መመዘኛዎች እሳቸው መሪ ሆነው መገኘታቸው ነው።

አልፎም ክርክር ሲካሄድ የሚመረጡ አዳራሾች እና አከራካሪዎች እሳቸው ላይ “ጠንካራ ሆኖ መታየት” እንደሚሹ ይናገራሉ።

ሌሎች የሪፐብሊካን ዕጩ ተፎካካሪዎች ስለትራምፕ ውሳኔ እስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም።

45ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አራት ጊዜ በወንጀል ተጠርጥረው በይፋ ተከሰዋል።

በአውሮፓውያኑ 2024 ድጋሚ ወደ ዋይት ሐውስ ለመግባት ከመፎካከራቸው በፊት፣ ችሎት ፊት እንዲቀርቡ ይደረጋሉ።

ትራምፕ የቀረቡባቸውን ክሶች ፖለቲካዊ “አደን” ሲሉ ይገልጧቸዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በሕጉ መሠረት ዘብጥያ ሊወርዱ ይችላሉ።

ነገር ግን በርካታ ተንታኞች አንድ የቀድሞ ፕሬዝዳንትን ለእሥር መዳረግ የራሱ የሆነ ውስብስብ ሂደቶች ስላሉት የማይታሰብ ነው ይላሉ።