ለዶናልድ ትራምፕ መርዝ በፖስታ የላከችው ሴት የ22 ዓመት እስር ተፈረደባት

ፓስካል ፌሪየር

የፎቶው ባለመብት, HIDALGO COUNTY SHERIFF'S OFFICE

ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት እሳቸውን ጨምሮ ለሌሎችን በመርዝ ለመግደል ራይሲን የተባለ መርዝ ያለባቸው ደብዳቤዎችን የላከችው ካናዳዊት ግለሰብ አሜሪካ ውስጥ በ22 ዓመት እስራት ተቀጣች።

የ56 ዓመቷ ፓስካል ፌሪየር በባዮሎጂካል የጦር መሳሪያ ክስ ጥፋተኛ ነኝ ብላ ለፍርድ ቤት አምናለች።

ለትራምፕ የተላከው ገዳይ ደብዳቤ በመስከረም 2020 (እአአ) ዋይት ሐውስ ከመድረሱ በፊት ሊደረስበት ችሏል።

ዕቅዷ ባለመሳካቱ እና “ትራምፕን ማስቆም ባለመቻ” እንዳዘነች ፌሪየር ለፍርድ ቤቱ ባደረገችው ረዘም ያለ ንግግር፣ እራሷን እንደ አክቲቪስት እንጂ እንደ አሸባሪ እንደማታይ ተናግራለች።

ፌሪየር አክላም “ዓላማዬን ለማሳካት ሠላማዊ መንገዶችን መጠቀም እፈልጋለሁ” ብላለች።

ኤፍቢአይ የጣት አሻራዎቿን ለትራምፕ በተላከው ደገብዳቤ ላይ አግኝቷል። በደብዳቤው ትራምፕ ከፕሬዝዳታዊ ምርጫ ውድድር ውጪ እንዲሆኑም አሳስባ ነበር ተብሏል።

በደብዳቤው ላይ “‘አስቀያሚው አምባገነን’ የሚል አዲስ ስም አገኝቼልሃለሁ” ብላለች።

ዳኛ ዳድኒ ፍሪድሪሽ፣ ፌሪየርን የ262 ወራት እስር ፈርደውባታል። ፍርዷን ካጠናቀቀች በኋላ ከአሜሪካ የምትባረር ሲሆን፣ የዕድሜ ልክ ክትትልም ይጠብቃታል።

ድርጊቷን በተመለከተ ዳኛው ፍሪድሪሽ ድርጊቷ “ሞት የሚያስከትል” እና “አንቺን፣ ሕብረተሰቡን እና ተጠቂዎችን ጎጂ ነው” ብለዋል።

ፌሪየር በተመሳሳይ ለስምንት የቴክሳስ ሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት ተመሳሳይ ደብዳቤዎችን መላኳን አምናለች።

እአአ በ2019 በሕገ-ወጥ መንገድ መሳሪያ በመያዝ እና ያለ ሕጋዊ ፍቃድ መኪና በማሽከርከር ለ10 ሳምንታት ያህል ታስራ ነበር። እንደ አሜሪካ ፍትህ መሥሪያ ቤት ገለጻ ከሆነ፣ በወቅቱ ለመታሰሯ ባለሥልጣናትን ተጠያቂ አድርጋለች።

የፈረንሳይ እና የካናዳ ጥምር ዜነት ያላት ፌሪየር ድንበር ልትሻገር ስትሞከር ነበር በቁጥጥር ስር የዋለችው። በወቅቱም ሽጉጥ፣ ቢላ እና ጥይቶችን ይዛ ነበር።

ኪዩቤክ በሚገኘው ቤቷ ውስጥ ራይሲን የተባለውን መርዝ ከካስተር ፍሬ ማዘጋጀቷ እና ደብዳቤው ያለበት ፖስታ ውስጥ መጨመሯን አምናለች።

ለራይሲን መርዝ ማርከሻ የሚታወቅ መድኃኒት የለም። እንደ አሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ከሆነ ራይሲን እንደ መጠኑ ዓይነት ከ36 እስከ 72 ሰዓታት ውስጥ ተጋላጩን ሰው ለሞት ሊዳርግ ይችላል።

እአአ በ 2014 ነዋሪነቱን በሚሲሲፒ ያደረገ ግለሰብ ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና ለሌሎች ባለሥልጣናት ራይሲን ያለባቸው ደብዳቤዎችን በመላኩ የ25 ዓመታት እስራት ተፈርዶበታል።