መርማሪ ኮሚሽኑ የጥቃት አካባቢዎችን ለመጎብኘት ያልተገደበ ፈቃድ እንደሚጠብቅ ገለጸ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ያቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መርማሪ ኮሚሽን፤ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተፈጽመውባቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን ባልተገደበ ሁኔታ መጎብኘት የሚያስችለው ፈቃድ ለማግኘት እንደሚጠብቅ አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ የኮሚሽኑ አባላት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መሄዳቸውን ተከትሎ ተመድ ባወጣው መግለጫ፣ አባላቱ የመብቶች ጥሰት ተፈጽመውባቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን ለመጎብኘት “አፋጣኝ እና ያልተገደበ ፈቃድ” እንደሚያገኙ ይጠብቃሉ።

“የምርመራ ኮሚሽን አባላቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ፣ የዐይን እማኞችን ምስክርነት ለመቀበል ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን ለመጎብኘት ያልተገደበ ፈቃድ እንደሚያገኙ ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል ተመድ ትላንት ሐምሌ 26/2014 ዓ.ም. ያወጣው መግለጫ።

ይህ ኮሚሸን ለመጀመሪያ ጊዜ ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሪፖርት ያቀረበው ሰኔ መጨረሻ ላይ ነበር።

መርማሪዎቹ በኦሮሚያ ክልል ተገድለዋል የተባሉትን 200 ሰዎች ጉዳይ በተመለከተ ምርመራ እንደሚያደርጉ በተመድ መግለጫ ተገልጿል።

የኮሚሽኑ ሦስት ባለሙያዎች ኬንያዊቷ የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ፣ አሜሪካዊው ስቲቨን ራንተር እና ሲሪ ላንካዊቷ ራሲካ ከሐምሌ 18/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከሌሎችም አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ይህ ኮሚሽን በዋነኛነት በሰሜኑ የኢትዮጰያ ጦርነት ወቅት፣ በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ጥሰቶችን እንዲሁም ዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕግ ጥሰቶችን “በጥልቀት እና በገለልተኛነት” እንደሚመረምር ተመድ ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን እና የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር ቡድን አባላትን የሰየመው በመጋቢት ነበር።

በወቀቱ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርማሪ እንዲቋቋም የተላለፈውን ውሳኔ እንደማትቀበለውና ከኮሚሽኑ ጋር እንደማትተባበርም መግለጿ አይዘነጋም።

ኋላ ላይ ግን መርማሪ ኮሚሽኑ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ሐምሌ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ እንደተሰጠው ይታወሳል።

አዲስ አበባ የነበረውን የአምስት ቀን ቆይታ በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በተሰጠው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ መጀመሪያ ላይ የኮሚሽኑን መቋቋም ነቅፋ እንደነበር አስታውሶ፣ “ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን ሲወጣ የመንግሥትን መሠረታዊ አቋም ባገናዘበ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥርዓትን በተከተለ” መንገድ ከሆነ ግን ከኮሚሽኑ ጋር የመተባበርን ጉዳይ “መልሶ የማጤን ዕድል” እንደሚኖር ጠቁሟል።

የኮሚሽኑ ምርመራ “የብሔራዊ ሕግ ሥርዓቱ ደጋፊና ማሟያ” ሆኖ መታየት እንዳለበት የጠቆመው መግለጫው፣ ምርመራው “የአሟይነት መርሕን ባከበረ መንገድ” እንዲሄድና “ተገቢነት ከሌላቸው የፖለቲካ ፍላጎቶች” ነጻ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሻ አክሏል።

ከዚህ ቀደም የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጥምረት ያደረጉትን ምርመራ “በማይደግም እና መንግሥት ተጠያቂነትን ለማስፈን እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን በማያስተጓጉል” መንገድ ምርመራው መካሄድ እንዳለበትም መንግሥት አቋሙን ገልጿል።

ተመድ ምን አለ?

የተባበሩት መንግሥታት በትናንትናው መግለጫው፤ መርማሪ ኮሚሽን ጥቃት የተፈጸመባቸው አካባቢዎችን ለመጎብኘት ያልተገደበ ፈቃድ እንደሚጠብቅ ገልጿል።

ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ መንግሥትን ፍትሕ በመደገፍ፣ ተጠያቂነትን በማስፈን እንዲሁም በእርቅ ዙሪያ ምክረ ሐሳብ እንደሚሰጥም በተመድ መግለጫ ተጠቁሟል።

የምርመራ ኮሚሸን አባላቱ ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሸን አባላት ጋር ተገናኝተው ውይይት እንዳደረጉም ተገልጿል።

ኮሚሽኑ በአምስት ቀናት የኢትዮጵያ ቆይታው ከኢሰመኮ፣ ከሲቪል ማኅበሮች፣ ከዲፕሎማቶች እና ከተመድ የኢትዮጵያ ወኪሎች ጋር ስለ አገሪቱ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ መወያየቱንም አክሏል።

የምርመራ ኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ ከዚህ ቀደም በጄኔቫ ባደረጉት ንግግር፣ “በመላው ዓለም ግጭት የተበራከተበት ወቅት ላይ ብንሆንም ዓለም በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን መዘንጋት የለበትም” ማለታቸው ይታወሳል።

“እየተስፋፋ ባለው ግጭት በጥላቻ ንግግር እየተባባሰ ሲሆን፣ ይህም ለብሔር ተኮር ጥቃትና ለጾታዊ ጥቃት መንገድ ከፍቷል። ከዚህ በከፋ ሁኔታም፣ በተለይ ሴቶችና ሕጻናት ላይ ያነጣጠረ ንጹሀን ዜጎችን የሚቀጥፍ ጥቃት እንደሚፈጸም ጠቋሚ ምልክቶች አሉ” ሲሉም ተደምጠዋል።