ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሲሪል ራማፎሳ በድጋሚ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ
በገዢው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ወሳኝ የተባለውን የአንድነት መንግሥት ለመመሥረት ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ በድጋሚ ሲሪል ራማ ፎሳን ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ።
አዲሱ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የአንድነት መንግሥት ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሁኔታ የራማፎሳን ኤኤንሲ፣ መሃል-ቀኝ ዘመሙን ዲሞክራቲክ አሊያንስን እና ሌሎች ትንንሽ ፓርቲዎችን ያቀፈ ነው።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ከተመረጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር ፓርቲዎች በጋራ መንግሥት መመሥረታቸውን አድንቀው፣ መራጮች ከመሪዎቻቸው “ለአገሪቱ ዜጎች በሙሉ መልካም ነገር በጋራ እንዲሠሩ እንደሚጠብቁ” ተናግረዋል።
ከሳምንት በፊት በተካሄደው ምርጫ ኤኤንሲ በአገሪቱ ፓርላማ ለ30 ዓመታት የነበረውን የበላይነት በማጣቱ መንግሥት ለመመሥረት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የአንድነት መንግሥት ለመመሥረት ንግግር ሲያደርግ ቆይቷል።
ኤኤንሲ በምርጫው ከፓርላማው መቀመጫዎች 40 በመቶውን ብቻ በማግኘቱ በተናጠል መንግሥት ለመመሥረት ባለመቻሉ፣ ሁለተኛውን 22 በመቶ ከፍተኛ መቀመጫ ካገኘው ዴሞክራቲክ አሊያንስ ጋር ለመጣመር ከስምምነት ላይ ደርሷል።
በተመሠረተው አዲስ መንግሥት ውስጥ ኤኤንሲ የራማፎሳን የፕሬዝዳንትነት መንበር ያስጠበቀ ሲሆን፣ በቀጣይነት በጥምር መንግሥቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ፓርቲዎች በአገሪቱ ካቢኔ ውስጥ የተለያዩ የሥልጣን ቦታዎችን ይጋራሉ።
የአፓርታይድ ሥርዓት ማብቃቱን ተከትሎ ባለፉት 30 ዓመታት በተካሄዱ ዴምክራሲያዊ ምርጫዎች በሙሉ ኤኤንሲ ከግማሽ በላይ መቀመጫ በማግኘት የበላይነት ይዞ ያለችግር መንግሥት ሲመሠርት ቆይቶ ነበር።
ነገር ግን ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ሠፊ የሙስና፣ የሥራ አጥነት እና የወንጀል ክስተቶች ምክንያት በሕዝቡ ውስጥ በተፈጠረ ቁጣ ምክንያት ፓርቲው የነበረው ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።
ከኤኤንሲ ጋር መንግሥት ለመመሥረት ጥምረት የፈጠረው ፓርቲ ዲሞክራቲክ አሊያንስ ላለፉት ዓመታት በተቀናቃኝነት የቆየ ከመሆኑ አንጻር ትብብራቸው ታይቶ የማይታወቅ ነው።
የዲሞክራቲክ ፓርቲ በአፓርታይድ የዘር መድልዎ ሥርዓት ዘመን ጥቂት ነጮች የገነቡትን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ የሚሠራ ነው ተብሎ የሚተች ቢሆንም ፓርቲው ግን ይህንን ያስተባብላል።
የተቃዋሚው ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ ፓመርሪ ጁሊየስ ማሌማ ባደረጉት ንግግር ሕዝቡ በምርጫ የሰጠውን ውጤት ቢያከብሩም በኤኤንሲ እና በዲሞክራቲክ አሊያንስ መካከል የተፈጠረውን ጥምረት “ነጮችን በአገሪቱ ኢኮኖሚ እና የምርት ዘርፍ ላይ ያላቸውን የበላይነት የሚያጠናክር ነው” በሚል ተቃውመውታል።