የሩሲያ የኒውክሌር ኃላፊ በሞስኮ መገደል የፈጠረው ረብሻ

የሩሲያ ጄነራሎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ሩሲያ የኒውክሌር ኃላፊዋን ሌተናንት ጄኔራል ኢጎር ኪሮሎቭን በዩክሬን ግድያ አጥታለች።

የኒውክሌር፣ ባዮሎጂካል እና ኬሚካል መከላከያ ኃላፊው የተገደሉት በመሬቷ ነው።

ለሶስት ዓመታት ያህል ከዩክሬን ጋር ጦርነት ላይ ብትሆንም በሩሲያ ህይወት በተለመደው መልኩ እንደቀጠለ ነው።

ባቡር የሚጠብቁ ሰዎች በሞስኮ ጎዳናዎች ሰብሰብ ብለው በየዕለቱ ይታያሉ። የምሽት ክበቦችም፣ ሬስቶራንቶች፣ ካፌዎች አልተዘጉም። አገራቸው በጦርነት እየተፋለመች የማይመስል ሁኔታ አለው።

ድንገት ግን ጦርነቱን የሚያስታውስ ክስተት ብቅ ይላል። በተለመደው ህይወት ጣልቃ ገብተው ይረብሻሉ።

ይህ ክስተት የሞስኮን የአየር መከላከያ ጥሶ የገባ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ሊሆን ይችላል።

ወይም በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ማለዳ እንደተፈጠረው የበለጠ አስገራሚ እንደሆነው የአንድ ከፍተኛ የሩሲያ ጄነራል ከመኖሪያ ህንጻቸው ሲወጡ የታለመው ግድያ።

ሌተናል ጄነራል ኢጎር ኪሮሎቭ እና ረዳታቸው አሊያ ፖሊካርፖብ ብስክሌት መሳይ በሆነው (የኤሌክስትሪክ ስኩተር ውስጥ በተደበቀ ቦምብ መገደላቸው ጦርነቱን ያስታወሰ ሆኗል። በተለይም ግድያው ሲፈጸም በቅርብ ለነበሩት ሩሲያውያን።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ዜና ላይ ማንበብ አንድ ነገር ነው፤ በጣም ሩቅ እንደሆኑ ሊሰማ ይችላል። ነገር ግን በቅርብ ርቀት ይህ ሲከሰት ፍጹም የተለየ እና የሚያስፈራ ነው" ስትል ጄኔራሉን ከገደለው ፍንዳታ አጠገብ በሚገኝ ህንጻ አቅራቢያ የምትኖረው ሊዛ

"እስካሁን ድስ [ጦርነቱ] በጣም ሩቅ እንደሆነ ይሰማን ነበር። አሁን አንድ ሰው ሞቷል። መዘዙ ላይሰማችሁ አይችልም" ትላለች።

"ጭንቀቴን መቆጣር አልቻልኩም። የምሰማው ድምጽ ሁሉ ይረብሸኛል። ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይስ ግንባታ እየተከናወነ፤ ሁሉ ነገር ግራ ያጋባል" ትላለች ሊዛ።

በዩክሬን ውስጥ እየተደረገው ያለው የሩሲያ ጦርነት ለብዙዎች ሩቅ ነው። ለበርካታ ሩሲያውያን ይህ ጦርነት በየቴሌቪዥን መስኮቶቻቸው ወይም በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ላይ ብቻ የሚከታተሉት ነው። በብዙ መንገዶች ለሩሲያውያን ምናባዊ የሆነ ጦርነት ነው ፤ምንም እንኳን የበርካታ ሰዎችን ህይወት ቢቀጥፍም እና ጉዳት ቢያደርስም።

ነገር ግን የሩሲያው ጄነራል በመሬቷ ሞስኮ ውስጥ መገደል በእርግጠኝነት የማንቂያ ደወል ነው። ጦርነቱ ቅርብ እና ቤት እያንኳኳ ስለመሆኑ ማሳያ።

ለሩሲያ ባለስልጣናትስ? የማንቂያ ደወል ይሆን?

ምናልባት ላይሆን ይችላል። የሩሲያ ባለስልጣናት በዩክሬን ላይ የሚያደርጉትን ጦርነት ይገታሉ ማለት ዘበት ነው። ሩሲያ ጦርነቱን በበለጠ ልታጠናክር እንደምትችል ማሳያዎች አሉ።

የጄነራሉን ግድያ ተከትሎ የሩሲያ የመንግሥት ቴሌቪዥን የፖለቲካ ውይይቶች አቅራቢ ዩክሬንን ጥፋተኛ በማድረግ "በዚህ ጥቃት ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በራሳቸው ላይ የሞት ፍርድ ፈርመዋል" ብሏል።

የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በበኩላቸው "መርማሪዎች ገዳዮቹን በሩሲያ ውስጥ ፈልገው ማግኘት አለባቸው" ብለዋል። አክለውም "በኪዬቭ ያሉ ተባባሪዎቻቸውን ለማጥፋት ሁሉንም ነገር ማድረግ አለብን" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሆኖም ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስለ ጄኔራሉ እና ረዳታቸው ግድያ እስካሁን በይፋ የተሰጠ አስተያየት የለም።

ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሩሲያ ከደህንነት ስጋቶች ጋር ከተጋፈጠች "ምላሽ ትሰጣለች" ሲሉ በተደጋጋሚ ተሰምተዋል።

በዚህም መመርኮዝ የበቀል እርምጃ ይወስዳሉ የሚለው አሳማኝ ነው።

በዚህ ሳምንት ሐሙስ ፕሬዚዳንት ፑቲን የአውሮፓውያኑን ዓመት መገባደጃ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ።

ይህ ዝግጅት በሁሉም ዋና ዋና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ ይተላለፋል።

በዚህ መግለጫቸው ላይ ስለ ኒውክሌር ኃላፊው ግድያ ይናገሩ ይሆን?

በሶሪያ ላይ ዝምታቸውን ይሰብሩ ይሆን? በመካከለኛው ምስራቅ የሩሲያ አጋር የሆነችው ሶሪያ መሪ በሻር አል አሳድ ከስልጣን መገርሰስን አስምመልክቶ ፑቲን እስካሁን በይፋ የተናገሩት ነገር የለም።

ወደ ሶስተኛ ዓመት እየተጠጋ ያለውን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ " ብለው የሚጠሩትን የዩክሬን ጦርነት እየሄደ ያለበትን አቅጣጫ የሚሉት ጉዳይ ይኖራል።