የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ የያዘበት ኤይር ኮንጎ በይፋ ሥራ ጀመረ

ኤር ኮንጎ በሁለት ቦይንግ 737 አውሮፕላኖችን በመጠቀም ነው አገልግሎቱን የጀመረው

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines/Facebook

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር በሽርክና አዲሱን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ አየር መንገድ ኤይር ኮንጎን በይፋ አስጀመሩ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤይር ኮንጎ 49 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፣ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት ደግሞ የ51 በመቶ ድርሻ መያዙን አየር መንገዱ ታህሳስ 8/ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አትቷል።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ አንቶይን ቲሽከዲ ኤይር ኮንጎ የሚል ስያሜ የተሰጠውን አዲሱን ብሔራዊ አየር መንገድ ን ዲጂሊ በተሰኘው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው አስጀምረዋል።

ኤር ኮንጎ ሁለት ቦይንግ 737 አውሮፕላኖችን በመጠቀም በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ሰባት አውሮፕላን ማረፊያዎች በረራ በማድረግ ነው አገልግሎቱን የጀመረው።

አውሮፕላኖቹ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋነኛ ከተሞች ሉቡምባሺ፣ ጎማ፣ ኪሳጋኒ፣ ኮልዌዚ፣ ካሌሚ እና ምቡጂላይ እንደሚበሩ ተገልጿል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ መስክ "ታሪካዊ" ሲሉ በማስጀመሪያ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው መናገራቸው በተቋሙ መግለጫ ተጠቅሷል።

በመካከለኛው አፍሪካ ያለውንም የአየር ትራንስፖርት እንደሚያሳድግ አክለዋል።

"ኤይር ኮንጎን ለመመስረት ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ያለን አጋርነት የቴክኒክ እና የአስተዳደር ልምዶች ለማስተላለፍ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የኮንጎ አቪዬሽን ባለሙያዎችን ለማሰልጠን፣ የሰለጠነ የአስተዳደር ባህልን ለማዳበር እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአቪዬሽን ዘርፉን ለማሳደግ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል" ሲሉ አቶ መስፍን ተናግረዋል።

ለኤይር ኮንጎ ስኬት ወሳኝ የሆኑ ቁልፍ ጉዳዮችን በመዘርዘር የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የሥራ ነጻነትን አስፈላጊነት በማጉላት የውጭ ጣልቃገብነት የአየር መንገዱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

"ኤይር ኮንጎ ከውጪ ጣልቃ ገብነት በጸዳ መልኩ ራሱን የቻለ ተቋም ሆኖ መንቀሳቀስ አለበት" ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየርመንገድ ሰራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines

"የአየር መንገዱ አስተዳደር ሃብቶችን የማሰባሰብ እና ወቅታዊ ውሳኔዎችን በቦርዱ መሪነት እና በዓለም አቀፍ ደንቦች መሠረት ሊተገብር ይገባል። ይህ መርህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስኬት መሰረት ነው። ማንኛውም አይነት ጣልቃ ገብነት ካለ ኤር ኮንጎ ላይሳካለት ይችላል" ሲሉ አክለዋል።

የአገሪቱ መንግሥት እና ባለድርሻ አካላት ዕቅዱ እውን እንዲሆን ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

የአገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀው፤ የኤይር ኮንጎን የትራፊክ መብት ለማስከበር በሌሎች አገራት ንቁ ሚና እንዲጫወት አሳስበዋል።

ኤይር ኮንጎ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተከራያቸው ሁለት ቦይንግ 737-800 አውሮፕላኖች ሥራ ጀምሯል።

ሁለቱም አውሮፕላኖች ኬንሻሳ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸው ታውቋል።

ይህ ጥምረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ራዕይ 2035 አንዱ አካል መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህም ቀደም በቶጎ አስካይ አየር መንገድ፣ በማላዊ የማላዊ አየር መንገድ እና በዛምቢያ የዛምቢያ አየር መንገድን በጋራ ማቋቋሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ለማቋቋም የያዘውን ራዕይ እንደሚገፋበትም በመግለጫው አስታውቀዋል።