የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሥመራ የሚያደርገው በረራ ለምን እንደታገደ አልተገለጸልኝም አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሥመራ የሚያደርጋቸው በረራዎች በኤርትራ መንግሥት ለምን አንደታገዱ ምክንያቶቹ እንዳልተገለጸለት አስታወቀ።
አየር መንገዱ ወደ አሥመራ ያደርጋቸው የነበሩ በረራዎች ከመስከረም 20 ጀምሮ በሙሉ እንደሚቋረጡ የሚገልጽ ደብዳቤ ከኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከሦስት ቀናት በፊት ሐምሌ 14/ 2016 ዓ.ም እንደደረሰውም ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
ሆኖም የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ለማገድ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዳልተገለጸ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ማብራሪያ መጠየቁን በመግለጫው ጠቁሞ ማንኛውንም ችግር በወዳጅነት እና በአፋጣኝ ለመፍታት ቁርጠኛ ነኝ ብሏል።
ነገር ግን የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተጠቅመው ከኤርትራ እና ወደ ኤርትራ ለሚያቀኑ መንገደኞች ባወጣው ማሳሰቢያ ላይ ለበረራው መቋረጥ ምክንያቶችን አስፍሯል።
የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዋና ከተማዋ አሥመራ የሚያደርገው በረራዎች ከመስከረም አጋማሽ በኋላ እንዲቋረጡ መወሰኑን ለሕዝብ ይፋ ያደረገው ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም. ነው።
በኤርትራ የትራንስፖርት እና ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስቴር የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዛሬ በታተመው በመንግሥታዊው “ሓዳስ ኤርትራ” ጋዜጣ ላይ ባወጣው ማስታወቂያ ላይ ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ መታገዱን የገለጸው።
ባለሥልጣኑ በጋዜጣው ላይ ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት ከመስከረም 20/2017 ዓ.ም. በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርጋቸው በረራዎችን በሙሉ ማገዱን አስታውቋል።
የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣኑ በጋዜጣ ላይ ባወጣው መግለጫ አየር መንገዱ እንዲታገድ የተወሰነው "ያልተገባ የንግድ ተግባራት" በመከተሉ ነው ሲል ኩባንያውን ወቅሷል።
የኤርትራ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ከደረሰባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ በአየር መንገዱ ተጓዦች ላይ “የተደራጀ እና ስልታዊ የሻንጣ ስርቆት" ይፈጸማል የሚለው ይገኝበታል።
ከዚህ በተጨማሪም ተደጋጋሚ የበረራዎች እና የሻንጣዎች መዘግየት እንደሚያጋጥም ጠቅሶ፤ አየር መንገዱ ለተጓዦች ካሳ ሳይሰጥ ቆይቷል ብሏል።
የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ለእግዱ እንደ ምክንያት ያቀረባቸው ጉዳዮች ለኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለመጠቀሱ የተባለ ነገር የለም።
የኤርትራ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አየር መንገዱን ለማገድ ከወሰነበት ምክንያቶች ሌላኛው የበረራ ቲኬቶች ዋጋ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ ነው ብሏል።
“ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች እንዲቀረፉ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጡ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎች ውጤት ማስገኘት ባለመቻላቸው ከመስከረም 20/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኤርትራ የሚደረጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች እንዲታገዱ ተደርገዋል” ብሏል።
የኤርትራ መንግሥት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓዦች ባወጣው መልዕክት ከመስከረም 20 በኋላ በአየር መንገዱ በረራ ለማድረግ ያቀዱ መንገደኞች ቀድመው ማስተካከያ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
የኤርትራ መንግሥት አየር መንገዱን ከመስረም 20 በኋላ አግጃለሁ ቢልም አየር መንገዱ ግን አሁንም በድረ-ገጹ እና በቲኬት መሸጫ ቢሮዎቹ ከመስከረም 21 በኋላ ለሚደረጉ በረራዎች የአየር ቲኬቶችን እየሸጠ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ወደ አሥመራ በሳምንት አምስት በረራዎችን ያደርጋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ የሳዑዲ አረቢያ፣ የቱርክ እና የግብፅ አየር መንገዶች ወደ አሥመራ መደበኛ በረራዎችን አሏቸው።
በቅርቡ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በጣልያን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የጣልያን አየር መንገድ ወደ ኤርትራ በረራ እንዲጀምር ስምምነት መደረሱ ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Hadas
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ያካሄዱት ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት ካበቃ በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የአውሮፕላን ጉዞ ሐምሌ/ 112010 ዓ.ም. መጀመሩ ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ጦርነትም ሆነ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ቆይታው የነበሩት አሥመራ እና አዲስ አበባ ግንኙነታቸውን ማደሳቸውን ተከትሎ ነበር በረራ የጀመረው።
በወቅቱ የሁለቱ አገራት መሪዎች “የአሥመራ ዲክላሬሽን” የተሰኘ ስምምነት ተፈራርመው ከአየር በረራ በተጨማሪ ተቋርጠው የነበሩት የየብስ ትራንስፖርት፣ የንግድ እና የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ዕድል ፈጥሮ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱን አገራት የሚያዋስኑ የድንበር በሮች በሙሉ ተዘግተው የሚገኙ ሲሆን የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው።
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ታድሶ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሰሜን ኢትዮጵያ የእርሰ በርስ ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ መልሶ መሻከሩ ይገለጻል።
በሰሜኑ ጦርነት የኤርትራ መንግሥት ከፌደራሉ መንግሥት ጎን ተሰልፎ የትግራይ ኃይሎችን ሲወጋ መቆየቱ ይታወሳል።












