ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰው ልጅ ከአንድ ሰው ጋር ብቻ መጣመር የጀመረው መቼ ነው?
ውሃ አጣጫቸውን የሚፈልጉ፣ የፍቅር ጓደኛ ለማግኘት የሚባዝኑ ሁሉ ዓይናቸውም ልባቸውም ብዙ ያማትራል።
በሠለጠነው ዓለም ይህንን እናቀላለን ያሉ መተግበሪያዎች ማለቂያ የሌላቸውን አማራጮችን ያቀርባሉ።
በዘመናዊ ዓለም የሕይወቴ ሕይወት የሚሉትን ማግኛ ዘዴዎች እና መልኮች በፍጥነት እየተለወጡ ነው።
በርግጥ ሰዎች ተፈጥሯቸው አንድ ሰው ከአንድ ሰው ጋር ብቻ ተጣምሮ ለመኖር ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚያስፈልጋቸው ጊዜ አሁን ይመስላል።
በለንደን የምትኖረው ሮማንያናዊቷ አሊና ከበርካታ ሰዎች ጋር፣ ሁሉም እያወቁ እና እየፈቀዱ፣ ጥብቅ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ከቆየች በኋላ መጠየቅ ጀመረች።።
"በቅርቡ ከበርካታ ሰዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት ያለው ሰው አገኘሁ፤ ሁልጊዜም እንደዛ ነበር ሕይወቱን የሚመራው" ትላለች።
"ለምንድን ነው በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ አንድ ሰው ለአንድ ብቻ የሆነው? አልኩ።ማወቅ ፈልጌ ነበር"
የዝግመተ ለውጥ መንገዳችንን የምንረዳበት አንዱ መንገድ የቅርብ ዘመዶቻችንን እና የሥነ ተዋልዶ ስልቶቻቸውን በማጥናት ነው።
"በጎሪላዎች ዘንድ አንድ ወንድ የበርካታ ሴቶች ባል ነው" ይላሉ በእንግሊዝ በሚገኘው የብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ የዝግመተ ለውጥ አጥኚ የሆኑት ዶ/ር ኪት ኦፒ፤ "ስለዚህ በቡድኑ ውስጥ ያሉት ልጆች ሁሉም የሚወለዱት ከአንድ ወንድ ግን ከተለያዩ እናቶች ነው።"
ነገር ግን ይህ ውጤታማ የሥነ ተዋልዶ ስልት አይደለም ሲሉ ዶክተር ኦፒ ያብራራሉ።
ይህም ወደ ከፍተኛ የጨቅላ ሕጻናት ግድያ ይመራል።
አክለውም "የጨቅላ ሕፃናት ግድያ በጣም አሳዛኝ የጎሪላ ሕይወት ገጽታ ነው" ብለዋል።
"አንድ ወንድ ጎሪላ ከእርሱ ጋር ቅርበት ያልፈጠሩ ጨቅላ ጎሪላዎችን ሲገድል እናትየው ቶሎ ለድርሰ ጥቂ እንድትዘጋጅ ያደርጋታል። ምናልባት ልንኮርጀው የማንፈልገው የዝግመተ ለውጥ ስልት ሊሆን ይችላል።"
ከሌሎች የዝንጀሮዎች ዝርያ መካከል እንደ ቺምፓንዚ እና ቦኖቦስ ያሉት ሴቶቹ የተለየ የዝግመተ ለውጥ ዘዴ አዳብረዋል።
ሴቶቹ ከበርካታ ወንዶች ጋር ተራክቦ በመፈጸም አባትነትን ግራ በማጋባት በልጆቻቸው ላይ ጉዳት የመድረስ ዕድሉን ይቀንሳሉ።
ሰዎችም የጀመሩት ተመሳሳይ በሆነ ሥርዓት ነው፤ ብዙ ወንድ ከብዙ ሴት የትዳር አጋሮች ጋር።
ከሁለት ሚሊዮን ዓመታት በፊት ግን ነገሮች ተለውጠዋል።
"ምክንያቱም የአየር ንብረት ለውጥ ነበር" ይላሉ ዶክተር ኦፒ።
"ቅድመ አያቶቻችን ይኖሩበት በነበረው ከሰሃራ በስተደቡብ ያለው የአፍሪካ ክፍል እየደረቀ ሰፊው ክፍል በረሃማ ሆነ። የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ራሳቸውን ከአዳኞች ለመጠበቅ በቡድን በቡድን መሆን ነበረባቸው። እነዚህን ትላልቅ ውስብስብ ቡድኖች ለመቋቋም አንጎል ትልቅ ሆነ እና በዚህም የተነሳ የጡት ማጥባት ጊዜ እየተራዘመ መጣ።"
ነገር ግን በትልልቅ ቡድኖች ውስጥ በጣም ብዙ ወንዶች ስለነበሩ፣ አባትነትን ለማምታታት አስቸጋሪ ሆነ።
"እንዲሁም ሴቶች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከእነዚህ ወንዶች የአንዱን እርዳታ ይፈልጋሉ። ስለዚህ አንድ ወንድን ብቻ ወደ ማግባት ተቀየሩ።"
'አንድ ሰው ለአንድ ነው፤ ትርፉ መዘዝ አለው'
እንደ ዶ/ር ኦፒ ገለጻ ከሆነ ይህ ለውጥ አስፈላጊ የሆነው ከአንድ ሰው ተጣምሮ መኖር "የተሻለ" ስለሆነ ሳይሆን ብቸኛው አዋጭ መንገድ በመሆኑ ነው።
ትልቅ አእምሮ ያላቸው፣ ቀስ እያሉ የሚያድጉ የሰው ልጆችን ማሳደግ እናት ብቻዋን ማድረግ ከምትችለው በላይ ትልቅ የወላጆች መዋዕለ ንዋይን ይጠይቃል።
ምንም እንኳን ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ቀስ በቀስ በአንድ ወደ መወሰን የተለወጡ ቢሆንም፣ ለአንድ አጋር ታማኝ ሆነው ለመቆየት ግን ይቸገራሉ።
ዶክተር ኦፒ "ከአንድ አጋር ጋር በሕይወታቸው ሙሉ ተቆራኝተው የሚዘልቁ ዝርያዎች አሉ፤ እና አይወሰልቱም ነገር ግን በጣም ጥቂት ናቸው" ብለዋል።
"የእኛ የቅርብ ዘመዶቻችን ሆነው በአንድ ተወስነው የሚኖሩት ጊቦኖች ናቸው።ጊቦኖች ከሌሎች ጥንዶች ተለይተው ወደ ጫካው የሚገቡትን ለመቆጣጠር ትንሽዬ የፖሊስ ዓይነት ክትትል ለማድረግ ለወንዶችም ለሴቶችም ለሁለቱም ቀላል ይሆንላቸዋል።"
"ነገር ግን እንደ ሰው ባለ ብዙ ወንድ፣ ብዙ ሴት ባለበት ውስጥ ሲኖር ግን፣ ጓደኛህ እያታለለች እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለመቆጣጠር የበለጠ ከባድ ነው።
'አንድ ሰው ለአንድ ነው፤ ትርፉ መዘዝ አለው' የሚለው በዚህ አተያይ ከተፈጥሯዊነቱ ይልቅ የመዳን ስልት ነው።
የጥንዶች ፍቅር
በፍቅር ስንወድቅ ወይም ታማኝ ለመሆን ስንታገል በአእምሯችን ውስጥ ምን ይፈጠራል?
በአሜሪካ ውስጥ የሚገኘው በኤሞሪ ዩኒቨርሲቲ የኒውሮሳይንስ ፒኤችዲ ተማሪ የሆነችው ሳራ ብሉመንታል፣ ትንንሽ እና ፀጉራማ ፍጥረታትን ከሰዎች ጋር በሚመሳሰል ረገድ ለረዥም ጊዜ ጥንድ ሆነው በመኖር የሚታወቁትን ፕራሪ ቮልስን አጥንታለች።
ከሁሉም ጋር የፍቅር ግንኙነት እና ወሲባዊ ተራክቦ ከሚፈጽሙት ቮል የሚባሉት ዘመዶቻቸው በተለየ፣ፕራሪ ቮልስ በአንጎላቸው ውስጥ ከፍተኛ የኦክሲቶሲን ተቀባይ አላቸው።
ኦክሲቶሲን ብዙውን ጊዜ "የመተቃቀፍ ሆርሞን" ተብሎ ይጠራል። በአካል ንክኪ እና በግንኙነት ወቅት በአንጎል ውስጥ የሚለቀቅ ኒውሮኬሚካል ነው።
"በፕራሪ ቮልስ ውስጥ ያለውን የኦክሲቶሲን ምልክት በሙከራ እንዳይሰራ ብናደርገው ጠንካራ ትስስር መፍጠር አይችሉም፤በአጋሮቻቸው አካባቢ የሚያሳልፉት ጊዜ ያነሰ ይሆናል" ብላለች ብሉመንታል።
ሰዎች ተመሳሳይ የኦክሲቶሲን ስርዓቶች አሏቸው፣ ይህም አእምሯችን ጥምረትን እንደ በጎ ተግባር ለመለማመድ የተገነባ መሆኑን ይጠቁማል።
ነገር ግን ሌላ ኬሚካል፣ዶፓሚን፣ ከታማኝነት ይልቅ አዲስ ነገር ለመፈለግ የምናሳየውን ለውጥ ሊያስረዳልን ይችላል።
በመጀመሪያዎቹ የመቀራረብ ደረጃዎች ዶፓሚን አንጎላችንን ይሞላዋል። ሁሉን ነገር ውብ በማድረግ እና ግልጽነትን በማደፋፈር ሚና አለው።
መቀራረቡ ካበቃ በኋላ ግን የዶፓሚን መንገዶች ይለወጣሉ።
ብዙ ባሎች ያሏቸው ሴቶች
ከአንድ ሰው ጋር ኪዳን የመግባት ዝግመተ ለውጥ ላይ ክርክር ያለ ቢሆንም፣ የሰው ልጅ ባህሎች ሁልጊዜም ሰፊ የጥምረት መልኮች አሉት።
በአሜሪካ ኢሊኖይ ቺካጎ ዩኒቨርሲቲ አንትሮፖሎጂስት የሆነችው ዶክተር ኬቲ ስታርክዌዘር በዓለም ዙሪያ ከኔፓል እና ቲቤት፣ ከእስያ እስከ አፍሪካ እንዲሁም የአሜሪካ ክፍሎች በርካታ ባሎች ያሏቸው ከ50 በላይ ሴቶችን ታሪክ ሰንዳለች።
በርግጥ ብዙ ባል ያላቸው ሴቶች ብዙ ሚስት ካላቸው ወንዶች በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም ስታርክዌዘር ግን አይቻልም ብለን እንዳንወስደው ታስጠነቅቃለች።
"ሴቶች ብዙ አጋሮች በማፍራት በኢኮኖሚ ሊጠቅሙ ይችላሉ። ዋና ባልሽ ቢሞት ወይም በጣም ለረዥም ጊዜ የማይኖርበት ሁኔታ ቢፈጠር፣ በአንዳንድ የሰሜን አሜሪካ በሚኖሩ ቡድኖች ውስጥ እንደታየው፣ የመጠባበቂያ እቅድ ማኖር ያስፈልጋል" ትላለች።
በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ በአንድ ሰው ተወስነው ያልተቀመጡ ሰዎች የዘረ መል ጥቅሙን መቋደስ ችለዋል ስትልም ታብራራለች።
ስታርክዌዘር "ሰዎች በብዛት በሚታመሙበት እና በበሽታ በሚሞቱባቸው አካባቢዎች፣ ከተለያዩ ሰዎች ብዙ ልጆች ያሉት ለራሱ መልካም እያደረገ ሊሆን ይችላል" በማለት ታስረዳለች።
"በአካባቢያቸው ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመጠኑ የተሻሉ ሊሆኑ ይችላሉ።"
ነገር ግን ከበርካታ ሰው ጋር ግንኙነት መመስረት ያለ ፈተና አይመጣም። ብዙ ግንኙነቶች ውስጥ በተመሳሳይ ወቅት መቆየት ጊዜን፣ጉልበትን፣ ስሜትን እና ንግግርን ይጠይቃል።
"ለወንድም ሆነ ሴት ብዙ ትዳሮችን በአንድ ጊዜ መመስረት እጅግ በጣም ከባድ ነው። በኢኮኖሚ፣በስሜት በሁሉ ነገር ከባድ ነው። እኔ እንደማስበው አንድ ሰው ማግባት ተመራጭ የጋብቻ ዓይነት ሆኖ የቀጠለው ለዚህ ነው" ስትል ስታርክዌዘር ትናገራለች።
በርካታ የፍቅር እና የወሲብ አጋር ያላቸው ምን ይላሉ?
አሊና ከአንድ ሰው ጋር መስርታው የነበረው ትዳር አልሰመረም።
አሁን ከበርካታ ሰዎች ጋር ባላት ግንኙነት ውስጥ ራሷን በውስብስብ ስሜቶች ውስጥ ታገኘዋለች።
ይህንንም ስታስረዳ "ቅናት በጣም ከባድ እና ጠንካራ ሊሆን ይችላል" ብላለች።
"በግሌ አብዛኛው ለእኔ ሃቀኛ እንዳልሆኑ ከመሰማት ይጀምራል፤ እና ልክ እነሱ ሃቀኛ መሆናቸውን ሳውቅ የቅናት ስሜቴን ያቀልልኛል።"
የፍቅር አጋሯ በዚህ ሃሳብ ይስማማል፤ አክሎም "ቅናት በእውነቱ ትልቁ ጉዳይ አይደለም ነው የምለው።ብዙ ጤናማ ግንኙነቶችን ለማስቀጠል የሚወስደው ጊዜ እና ጥረት ትንሽ ከባድ ሊሆን ይችላል ባይ ነኝ።"
ሆኖም ሁለቱም አዋጭ መሆኑ ላይ ጥያቄ የላቸውም። አሊና "አስቀድሞ የተቀመጡ ደንቦች የሉም" ትላለች።
"ያ ደግሞ በሁለቱ ግለሰቦች መካከል ግልጽ ውይይት እንዲኖር ያደርጋል፤ ካለበለዚያ ግን ሁሉ ነገር ያከትማል። ያ ነው ግንኙነታችንን የበለጠ ጠንካራ ያደረገው።"
ታድያ በተፈጥሯችን አንድ ሰው ለአንድ ሰው ብቻ ነበርን? መልሱ አዎን እና አይደለም የሚል ይመስላል።
በባህሎች እና በታሪክ ውስጥ፣ ሰዎች ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር የሚስማሙ የተለያዩ የግንኙነት መንገዶችን አዳብረዋል።
ለአንዳንዶች፣ ከበርካታ ሰዎች ጋር የፍቅር ወይም የወሲብ ግንኙነት መመስረት የስሜት ነፃነትን እና የኢኮኖሚ ተጣጣፊነትን ይሰጣል።
ለሌሎች ደግሞ አንድ ሰው ከአንድ ጋር ታምኖ ሲኖር ፍቅርን ለማግኘት፣ለማጣጣም የሚረዳው ቀላሉ መንገድ ነው።
ኬቲ ስታርክዌዘር "የሰው ልጆች በበርካታ ለውጦች ውስጥ አልፏል።ከዚያም መካከል አንዱ ግንኙነቶችን የሚመሰረትበት እና የሚጋባባትን መንገድን ይጨምራል" ትላለች።
"በፕላኔታችን ላይ በሁሉም ዓይነት አካባቢዎች ውስጥ እንኖራለን፤ ያም ባለን ተለዋዋጭነት እና ባህሪ ምክንያት የመጣ ነው።"