ከጓደኞቹ ጋር ሲጠጣ ያመሸው ጃፓናዊ በጣለው ምሥጢራዊ ሰነድ ምክንያት መንግሥት ይቅርታ ጠየቀ

በጃፓን የገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ የሚሠራ አንድ ሠራተኛ ከጓደኞቹ ጋር 'አንድ-ሁለት' ለማለት መሸታ ቤት በወጣበት ምሽት አንድ ወሳኝ ሰነድ ከእጁ በመጥፋቱ መሥሪያ ቤቱ ይቅርታ ጠየቀ።

ስሙ በውል ያልተገለጸው ይህ የጃፓን ገንዘብ ሚኒስቴር ሠራተኛ የጣለው ምሥጢራዊ ሰነድ የ187 ተጠርጣሪ የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎች የግል ዶሴን የያዘ ነው።

በዮኮሃማ ከተማ ነዋሪ የሆነው ይህ ግለሰብ ይህንን መንግሥታዊ ሰነድ በመጣል ጉድ የሆነው ዘጠኝ ጠርሙስ ቢራ ከጠጣ በኋላ ነው ተብሏል።

ግለሰቡ ወደ ቤቱ ከመግባቱ በፊት በመሸታ ቤት ከጓደኞቹ ጋር የቆየው ለአምስት ሰዓት ነበር።

የመሥሪያ ቤቱ ወሳኝ የሚባለውን ዶሴ መጣሉን ያወቀውም በባቡር ተሳፍሮ ሱሚዳ በተባለች ሌላ ከተማ ወደ ሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በሚያደርሰው ባቡር ተሳፍሮ ከወረደ በኋላ ነው።

የሰነዱን መጥፋት ተከትሎ የጃፓን የገንዘብ ሚኒስቴር በሁኔታው "በጽኑ ማዘኑን" ገልጿል።

የጃፓን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህ ክስተት "ያለንን የሕዝብ አመኔታ የሚያሳጣ ነው" በማለት በሠራተኛው ምክንያት ሀፍረት እንደተሰማው አመልክቷል።

ይህ ሠራተኛ የጣለው ቦርሳ 187 ተጠርጣሪ የአደኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን ስም እና አድራሻ ብቻ ሳይሆን የተቀባዮቹንም ዝርዝር የያዘ ምሥጢራዊ ሰነድን በውስጡ ይዞ ነበር።

ግለሰቡ ከዚህ ሰነድ ሌላ መሥሪያ ቤቱ ለሥራ የሰጠውን ላፕቶፕ እና ውስጡ የነበሩ ወሳኝ መረጃዎችም አብረው ጠፍተውበታል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ዙሪያ ከጃፓን የገንዘብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተጨማሪ መረጃ ለማካተት ያደረገው ጥረት ዛሬ ማክሰኞ በጃፓን የሕዝን በዓልቀን ስለሆነ መሥሪያ ቤቶች ዝግ በመሆናቸው አልተሳካም።

በጃፓን ለበርካታ ዓመታት አልኮል እየቀማመሱ የቢዝነስ እና ሌሎች ጠንከር ያሉ ጉዳዮችን ማውጋት የተለመደ ነው።

ይህም ሰዎች እየጠጡ ሲያወጉ ዘና ስለሚሉ የተሻለ ቢዝነስ ለመደራደር እና ለመግባባት ይመቻል በሚል እሳቤ የሚደረግ ነው።