ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩናይትድ ኪንግደም ከመቶ ዓመት በፊት የተጻፈው ደብዳቤ ወደ ተላከበት ደረሰ
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1916 ተላከ አንድ ደብዳቤ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ዘግይቶ ወደ ተላከበት ስፍራ ደረሰ።
የንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ምስል ያረፈበት ባለ አንድ ፓወንድ ቴምብር የተለጠፈበት ፖስታ ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ቆይቶ ክሪስታል ፓላስ ሐምሌት መንገድ ላይ ከሚገኘው የግሌን ፊንሌይ መኖሪያ ሕንጻ ደርሷል።
“ደብዳቤው ከአንድ መቶ ዓመት በላይ እንዴት ሊዘገይ እንደቻለ መደነቅ እና ግራ መገባት ተሰምቶናል” ሲል ደብዳቤውን የተቀበለው ግሌን በሁኔታው የተሰማውን ተናግሯል።
የአገሪቱ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ሮያል ሜይል ስለጉዳዩ በሰጠው ምላሽ “ይህ ደብዳቤ ምን እንዳጋጠመው እርግጠኛ አይደለንም” ብሏል።
ደብዳቤው ባለፈው ዓመት ያረፉት የንግሥት ኤልዛቤት አባት ንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ በዙፋን ላይ በነበሩበት እና የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በተካሄደበት ጊዜ ነበር የተላከው።
በአገሪቱ የፖስታ አገልግሎት ደንብ መሠረት አንድ ሰው በስሙ ያልተላከን ደብዳቤ መክፈት ወንጀል ቢሆንም፣ ከመቶ ዓመት በላይ የዘገየው ደብዳቤ በቤቱ አድራሻ የመጣለት ግሌን ግን ከፍቶ መልዕክቱን ለማንበብ ጓጉቷል።
የ27 ዓመቱ የቴአትር ዳይሬክተር ግሌን እንደሚለው “ይህንን በማድረጌ ወንጀል የምፈጽም ከሆነ፣ ማድረግ የምችለው ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ነው።”
ደብዳቤው በዘመኑ በተለያዩ መስኮች ታዋቂ የነበሩ ሰዎች የተጻጻፉት መሆኑን፣ በየሦስት ወሩ የሚታተመው የአካባቢውን ታሪክ የሚዘግበው መጽሔት አርታኢ ኖርዉድ ኦክስፎርድ ተናግሯል።
ጨምሮም “ደብዳቤው በ1800ዎቹ ከፍ ባለ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙ ሰዎች ተወዳጅ የነበረው የዚህን አካባቢ ነዋሪዎች እና ታሪክን ባልተለመደ ሁኔታ ለማወቅ የሚረዳ ነው” ብሏል።
ደብዳቤው የደረሰው ግሌን መልዕክቱን የላኩት ወይም የተቀባይ ቤተሰቦች የሚገኙ ከሆነ፣ ይህ የቤተሰባቸው አስደናቂ የታሪክ ክፍል ስለሆነ ሊጠይቁት እንደሚችሉ ግልጽ አድርጓል።
ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ቆይቶ ወደ ተላከበት አድራሻ የደረሰው ደብዳቤን በሚመለከት ዜናው መጀመሪያ ላይ የተዘገበው በ‘ሳውዝ ለንደን ፕሬስ’ ላይ ረቡዕ ዕለት ነበር።
ሮያል ሜይል የተሰኘው የፖስታ አገለግሎት ድርጅት ቃል አቀባይ “ይህን የመሳሰሉ ሁኔታዎች በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት ሲሆን፣ የአሁኑ ግን እንዴት ሊሆን እንደቻለ እርግጠኛ አይደለንም።
“እኛም በ1916 በተላከው በዚህ ደብዳቤ አሁን መድረስ ታሪክ ዙሪያ በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን ጥያቄ እንገነዘባለን፣ ቢሆንም ግን ምክንያቱ ምን እንደሆነ የምንሰጠው ተጨማሪ መረጃ የለንም” ብሏል።