ፕሬዚዳንት ሩቶ የፋይናንስ ሕጉን ውድቅ ቢያደርጉም ኬንያውያን ተቃውሟቸውን ቀጥለዋል

በርካታ ሕይወትን ከቀጠፈ በኋላ የተለያዩ ግብር ጭማሪዎችን ለመጣል ያለመው የኬንያ የፋይናንስ ረቂቅ ሕግን ፕሬዚዳንት ሩቶ ውድቅ ቢያደርጉትም ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው።

በአገሪቱ በተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ፓርላማው ያጸደቀው ረቂቅ ሕግ ላይ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ “የሕዝቡን ድምጽ ሰምቻለሁ” ብለው ነበር።

የበርካታ ሰዎች ሕይወት ከተቀጠፈ፣ አካላዊ ጉዳቶች እንዲሁም ወጣቶች ፓርላማውን ተቆጣጥረው የተወሰነው ክፍሉ ከተቃጠለ በኋላ ነው ፕሬዚዳንቱ በፋይናንስ ሕጉ ላይ ውሳኔያቸውን ያሳወቁት።

ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ ተደራራቢ ግብር እንዲሁም ከሰሞኑ በተነሳው ተቃውሞ ሰልፈኞች በፖሊስ መገደላቸው ከፍተኛ ቁጣ የፈጠረው የኬንያውያን የተቃውሞ መልኩን ቀይሮ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን እንዲወርዱ እየጠየቁ ነው።

መንግሥት በእነዚህ የቀረጥ ጭማሪዎች 2.7 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ እና አገሪቷ ያለባትን የዕዳ ጫና ለማቃለል ይውላል ሲል እየተሟገተ ቆይቷል።

ፕሬዚዳንት ሩቶ የፋይናንስ ሕጉን ውድቅ በማድረጋቸው አገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ማግኘት እንደሚጠበቅባት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

የሕዝቡን ድምጽ በመስማት ሕጉን ውድቅ ማድረጋቸውን ተናግረው የነበሩት ሩቶ እሁድ ዕለት ሰኔ 23/ 2016 ዓ.ም. ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ውሳኔው አገሪቷን ወደ ኋላ ለሁለት ዓመታት የሚመልስ ነው ብለውታል።

መንግሥት “አገሪቱን ለመምራት አንድ ትሪሊየን ሽልንግ (7.6 ቢሊዮን ፓውንድ) መበደር አለበት ማለት ነው” ብለዋል።

ይህም ኬንያ ካቀደችው 67 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል።

ፕሬዚዳንቱ የራሳቸውን ቢሮ ጨምሮ በፍትህ አካላት፣ በክልል መንግሥታት በአጠቃላይ በመንግሥት አስተዳደሮች ላይ የወጪ ቅነሳ ይደረጋል ብለዋል።

በፋይናንስ ሕጉ በሚጣሉ ተጨማሪ ግብሮች 350 ቢሊዮን ሽልንግ ለማሰባሰብ እና አገሪቱም 600 ቢሊዮን ሽልንግ ለመበደር አስባ ነበር።

ፕሬዚዳንቱ ኬንያ በአሁኑ ጊዜ ያለባትን 80 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብሔራዊ ዕዳን ለመቀነስ የተለያዩ ግብሮችን መጣል አንዱ እርምጃ እንደነበር ገልጸው፤ አገሪቱ ከምትሰበስበው 60 በመቶው የሚሆነውን ዕዳ ለመክፈል ታውለዋለች ብለዋል።

“ኬንያን ከተዘፈቀችበት ዕዳ ለማውጣት በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራሁ ነው። እንደ አገር የፋይናንስ ረቂቁን አንቀበልም ማለት ለእኛ ቃለል ነው። ጥሩ እሺ! የፋይናንስ ረቂቁን ውድቅ አደረግኩ ግን መዘዙ የከፋ ነው የሚሆነው” ሲሉ ሩቶ እሁድ ምሽት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ሩቶ የዚህ ረቂቅ ውድቅ መሆን በጊዜያዊ ኮንትራት ያሉ 46 ሺህ የመለስተኛ 2ኛ ደረጃ መምህራን ቅጥር እንዲሁም የጤና አጠባበቅ አቅርቦትን እንደሚጎዳ ተናግረዋል።

መንግሥት እንደታቀደው የሸንኮራ አገዳ፣ የወተት ፋብሪካዎች እና የኅብረት ሥራ ማኅበራት የተበደሩትን ዕዳ መክፈል ጨምሮ የቡና አምራቾችን መደገፍ እንደማይችል ተናግረዋል።

ሆኖም የፋይናንስ ረቂቅ አዋጁን በሚቃወሙ ወገኖች የተነሱትን ቢሯቸው የሚያወጣውን ወጪ መቀነስ እና ለቀዳማዊት እመቤት እና የምክትል ፕሬዝዳንቱ ባለቤት በጀቶችን መሰረዝ ያሉ ጉዳዮችን እያጤኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ ተጨማሪ ብድርን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ትችት የገጠመው ሲሆን፣ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ኦድሂምቦ ራሞጊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኬንያን “በከፋ የዕዳ አዘቅት ውስጥ ስለሚከታት የበለጠ መበደር ማስተዋል ያልታየበት ነው” ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያም ተመሳሳይ ውይይቶች ተደርገዋል።

ምንም እንኳን የፋይናንስ ሕጉ ውድቅ ቢደረግም በመንግሥት ላይ ያለው ቁጣ የተቀጣጠለ ሲሆን፣ በዚህ ሳምንም ተጨማሪ የተቃውሞ የአደባባይ ሰልፎች ተጀምረዋል።

መንግሥት የበለጠ ተጠያቂ እንዲሆን የሚጠይቁ እንዳሉ ሁሉ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ይልቀቁም እያሉ ነው።

መንግሥት ለሕዝቡ ችግር ግድየለሽነት አሳይቷል የሚሉት ተቃዋሚዎች ፖሊስም የሰጠው ምላሽ ጭካኔ የተሞላበት ነው ይላሉ።

በሰሞኑ ተቃውሞ ቢያንስ 23 ሰዎች መገደላቸውን የዶክተሮች ማኅበር የገለጸ ሲሆን፣ በርካቶችም መቁሰላቸው ተነግሯል።

ሆኖም እሁድ ዕለት ፕሬዚዳንቱ ፖሊስ “የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል” ብለዋል።

የፋይናንስ ረቂቁ በርካታ የአፍሪካ አገራትን በተለይም ድሃውን ሕዝብ በድህነት አዙሪት ውስጥ በመዘፈቅ የሚወቀሰው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ተግባራዊ እንዲደረግ የሰጠው ማሻሻያ ነው።

ረቂቅ ሕጉ የኬንያ የ2024̀/5 በጀት አካል ሲሆን መንግሥት ገቢውን ለመጨመር በተለያዩ ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ ቀረጥ እና ታሪፍ መጨመርን የያዘ ነበር።

ከእነዚህም መካከል በዳቦ ላይ 16 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) መጣልን ጨምሮ እንዲሁም በሞባይል ገንዘብ የማስተላለፊያ አገልግሎት ላይ ታሪፈ እና በመኪና ላይ 2.5 ቀረጥ ተካትተውበት ነበር።

ረቂቅ ሕጉ ለአካባቢ ጎጂ ናቸው ተብለው በሚታሰቡ እንደ ማሸጊያ፣ ፕላስቲክ እና ጎማ ያሉ ምርቶች ላይ ‘ኢኮ ታክስ’ እንዲጣል ሃሳብ አቅርቧል። በዚህም እንደ ህፃናት ዳይፐር፣ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያዎች፣ ኮምፒውተሮች እና ሞባይል ስልኮች ላይ ቀረጥ ይጥላል።