አርጀንቲና ለምን ጥቁር ተጫዋቾች የሏትም? - የሰሞኑ “ዘረኛ” ሕብረ ዜማ ያጫረው ጥያቄ

*ይህ ዘገባ የተፃፈው በደቡብ አሜሪካው የስፖርት ፀሐፊ ቲም ቪከሪ ነው

አርጀንቲና የኮፓ አሜሪካ ዋንጫን በማንሳት በእግር ኳስ ክብር ብታገኝም ተጫዋቾች ደስታቸውን ሲገልጹ ያሰሙት ዜማ ብዙዎችን አስቆጥቷል።

አማካዩ ኤንዞ ፈርናንዴዝ በማኅበራዊ ሚድያ ገፁ በለቀቀው ቪድዮ ምክንያት ከክለቡ ቼልሲ ቅጣት ይጠብቀዋል። የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአርጀንቲና አቻውን በፊፋ ችሎት እገትራለሁ ብሏል።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ በኮፓ አሜሪካ ፍፃሜ ኮሎምቢያን 1 - 0 በመርታት ዋንጫ ያነሱት የአርጀንቲና ተጫዋቾች ያሰሙትን ሕብረ ዜማ በተመለከተ ምርመራ እንደጀመረ ተሰምቷል።

ሕብረ ዜማው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ በተለይ ጥቁር እና የተዳቀለ ዘር ያላቸው የብሔራዊ ቡድኑ አባላትን የሚያንኳስስ ነው ተብሏል።

ይህ ዜማና ጭፈራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስከተለውን ውዝግብ ተከትሎ የአርጀንቲና መንግሥት አስተያየቱን ሰጥቷል።

በዣቪዬ ሚሌ የሚመራው ቀኝ ዘመም የአርጀንቲና መንግሥት በምዕራቡ ዓለም “ስሱ” ተብለው የሚጠሩ ጉዳዮችን በተለመከተ ምንም ዓይነት ርህራሔ የሚያሳይ አይመስልም።

ነገር ግን የስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው ሁሊዮ ጋሮ የብሔራዊ ቡድኑ አምበል ሊዮኔል ሜሲ እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ክላውዲዮ ታፒያ ይቅርታ እንዲይቁ መክረዋል። እሑድ ምሽት ተጫዋቾቹ አውቶብስ ውስጥ ያሰሙት ዜማ “ምስላችንን የሚያጠለሽ ነው” ብለዋል።

ይህን አስተያየት የሰጡት ጋሮ ረቡዕ ዕለት ከሥልጣናቸው ተባረዋል። ሌሎች ባለሥልጣናት ደግሞ ይቅርታ ልንጠይቅ አይገባም እያሉ ነው።

በተለይ በደቡብ አሜሪካ የአህጉር ጨዋታዎች ላይ የብራዚል ክለቦች ከአርጀንቲና ክለቦች ጋር ሲጫወቱ አርጀንቲናውያን ደጋፊዎች የዝንጅሮ ምልክት እንደሚያሳዩ የማይካድ ሐቅ ነው።

ደጋፊዎች ቃለ-መጠይቅ ሲደርግላቸው ያሳዩት ድርጊት በፍፁም ዘረኛ እንዳልሆነ በመናገር ያስተባብላሉ። የእግር ኳስ “ብሽሽቅ” ነው ሲሉ ይከራከራሉ። የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን አባላት ባሰሙት ዜማ ምክንያት ለተፈጠረው ግርግርም የተሰጠው ምክንያት ይህ ነው።

የአርጀንቲና ክለቦች መሰል ድርጊቶችን ለማስቀረት ያደረጉት ሙከራ በሙሉ ልብ የሆነ አይመስልም። ክለቦቹ ጉዳዩ “ዜኖፎቦያ” [የመጤዎች ጥላቻ] ነው ይላል። ነገር ግን ጉዳዩ ዘረኝነት ነው።

በጣም አሳዛኝ የሚያደርገው ነገር በአንዳንድ ክስተቶች ተጫዋቾች ሳይቀር ይህን ድርጊት ማንፀባረቃቸው ነው።

ከአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን አባላት ሊዮኔል ሜሲ እና ሁለተኛው ግብ ጠባቂ ፍራንኮ አርማኒ በቀር ሁሉም በአውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱ ናቸው።

እኒህ ተጫዋቾች ከተለያዩ አገራት የመጡ፤ የተለያዩ ባሕል ያላቸው፤ የተለያየ ዘርና ቀለም የተላበሱ ተጫዋቾች ባሏቸው ክለቦች ነው የሚጫወቱት።

ተጫዋቾቹ ወደ አውሮፓ ክለቦቻቸው ሲመለሱ ምናልባት ቅጣት ከቅጣት ባሻገር ከክለብ አጋሮቻቸው ጋር ቅሬታ የተላበሰ ገፅ ሊጠብቃቸው ይችላል።

ለምን አደረጉት?

እንደ ማንኛውም እግር ኳሰኛ ለአርጀንቲናውያን ተጫዋቾች አገራቸውን ወክለው መጫወት ትልቅ ክብር ነው። ለብሔራዊ ቡድናቸው ያላቸውን ክብር በመስዋዕትነት የሚገልጹበት አጋጣሚ ነው።

የአርጀንቲና ክለቦች ደጋፊዎች ስታድየም ውስጥ የሚያሰሙት የድጋፍ ሕብረ ዜማ ድንቅ ነው። ሕብረ ዜማዎቹ ጥዑም ናቸው።

ነገር ግን ከኮፓ አሜሪካ ድል በኋላ የተሰማው ዜማ ግጥም የሚረብሽ ነው። ይህ ዜማ በኳታር ዓለም ዋንጫ አርጀንቲና ፈረንሳይን በፍፁም ቅጣት ምት አሸንፋ ዋንጫ ባነሳች ወቅት የተወለደ ነው።

የአርጀንቲና ተጫዋቾች ጥቁር የክለብ አጋሮቻቸውን ብቻ አይደለም በዚህ ዜማ የተሳደቡት። የገዛ ታሪካቸውን ጭምር እንጂ።

እርግጥ ነው ጥቁር አርጀንቲናውያን እግር ኳስ ተጫዋች ማየት የተለመደ አይደለም። ነገር ግን ይህ ሁሌም የነበረ አይደለም።

ስፔን አርጀንቲናን ቅኝ በገዛችበት ወቅት በርካታ አፍሪካውያን በባርነት ወደ ብራዚል ሲመጡ ቁጥራቸው ብዙ የማይባል ደግሞ ወደ አርጀንቲና ተግዘዋል።

ቢሆንም ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት የአሁኗ የአርጀንቲና ዋና ከተማ ቦነስ አይረስ አንድ ሦስተኛ ነዋሪዎች ጥቁሮች ነበሩ።

ይህ ሕዝብ የት ገባ?

የአርጀንቲና ጥቁር ዜጎች የት ገቡ ለሚለው ጥያቄ በርካታ መላ ምቶች ይሰነዘራሉ። የቢጫ ወባ ወረርሽኝ እና የነፃነት ትግል የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው።

የማይካደው ታሪክ ግን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ እና በ20ኛው መባቻ አብዛኛው የአርጀንቲና ጥቁር ዜጋ ከአውሮፓ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ በመጡ ስደተኞች መዋጡ ነው።

በርካታ ስደተኞች ከጣሊያን ነው የመጡት። አርጀንቲናውያን የሚናገሩት ስፖኒሽ ቋንቋ ለጣሊያንኛ የቀረበ ነው።

ወጣም ወረደ የአፍሪካውያን ደም አርጀንቲናውያን ውስጥ አለ። ጠቆር ያለ ቀለም ያላቸው አርጀንቲናውያን ‘ኤል-ኒግሮ’ ተብለው ይጠራሉ። ነገር ግን ይህ ቅጥያ አጸያፊ ትርጉም ያዘለ አይደለም።

በቅኝ ግዛት ዘመን ደቡባዊ ጫፍ ላይ ያሉ አገራት ብዙም ነጭ ስደተኞች የሚጎበኟቸው አልነበሩም። በተቃራኒው አንዳንድ የደቡብ አሜሪካ አገራት መሪዎች ደግሞ ነጭ ስደተኞችን በማምጣት አገራቸውን “ለማዘመን” ሞክረዋል።

ለዚህ ነው በርካታ አርጀንቲናውያን ዘራቸው ሲመዘዝ ከአውሮፓ አገራት የሚሆነው። ይህም በወቅቱ የነበረውን የዘር አመለካከት የሚያሳይ ነው።

ይህ አንድ ዘር ከሌላው ይበልጣል የሚለው አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ተነቅሎ የጠፋ አይመስልም። ይህ አስተሳሰብ ነው በአርጀቲናውያን ተጫዋቾች ዘንድ የተንፀባረቀው።