ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሴፕ ብላተርና ሚሼል ፕላቲኒ በማጭበርበር ተከሰው ችሎት ፊት ሊቆሙ ነው
በአንድ ወቅት የዓለም እግር ኳስ አሿሪ የነበሩት ሴፕ ብላተር እና ሚሼል ፕላቲኒ ችሎት ፊት ሊቆሙ ነው።
የስዊዘርላንድ ከሳሾች የቀድሞው የፊፋ ፕሬዝደንት ብላተር ለቀድሞው የአውሮፓ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፕላቲኒ የሰጧቸው 1.6 ሚሊዮን ዩሮ ሕገ ወጥ ነው ይላሉ።
ብላተርም ሆነ ፕላቲኒ ክሱን ያጣጥላሉ።
ገንዘቡ ፈረንሳዊው ፕላቲኒ ፊፋን ላማከረበት የተከፈለ ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።
ሁለቱ በአንድ ወቅት ኃያላን የነበሩ ግለሰቦች ከፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ ከእግር ኳስ ታግደዋል።
ባለፈው ዓመት ደግሞ በይፋ መከሰሳቸውን የሚያሳይ ደብዳቤ ደርሷቸዋል።
ሚሼል ፕላቲኒ
የ66 ዓመቱ ፈረንሳዊ ፕላቲኒ ሦስት ጊዜ የባሎን ደኦር ሽልማትን ማንሳት የቻለ ድንቅ ተጫዋች ነበር።
ከፈረንሳይ ጋር የ1984ቱን የአውሮፓ ቻምፒዮንሺፕን ከጁቬንቱስ ጋር ደግሞ በ1985 የአውሮፓ ዋንጫን አንስቷል።
ፕላቲኒ ለተወሰነ ጊዜ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን ካሠለጠነ በኋላ በሌሎች የእግር ኳስ አስተዳደር ቦታዎች ሠርቷል።
ሚሼል ፕላቲኒ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ኃላፊ ሆኖ የተመረጠው በ2007 ነበር።
በፈረንጆቹ 2015 ብላተር በሙስና ተጠርጥረው የሥራ መልቀቂያ ሲያስገቡ ፕላቲኒ ሊተካቸው እንደሚችል ተገምቶ ነበር።
ነገር ግን የፕላቲኒን መዝገብ የመረመረው የፊፋ የሥነ ምግባር ኮሚቴ ፕላቲኒም እጁ አለበት ሲል ከሰሰ።
በዚህ ምክንያት ለስምንት ዓመት ከእግር ኳስ እንዲርቅ ታገደ። የኋላኋላ እገዳው ወደ አራት ዓመት እንዲወርድ ተወሰነ።
ፕላቲኒ ጉዳዩን ለእግር ኳስ የግልግል ዳኞች [ካስ] ቢያቀርብም ውድቅ ሆኖበታል።
ሴፕ ብላተር
የ86 ዓመቱ ስዊዝ የቢዝነስ ሰው ጆሴፍ ብላተር ፊፋን የተቀላቀሉት በፈረንጆቹ 1975 ነው።
የፊፋ ፕሬዝደንት ሆነው የተሾሙት ደግሞ በ1998።
ብላተር በተለያየ ጊዜ ብዙ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ፊፋን ለ17 ዓመታት አስተዳድረዋል።
በሙስና፣ በገንዘብ አያያዝ፣ ጉቦ በመቀበልና የምርጫ ድምፅ በማዛባት ወንጀል ለበርካታ ዓመታት ሲከሰሱ ቆይተዋል።
ብላተር በ2015 ለ8 ዓመታት ከእግር ኳስ እንዲታገዱ ተወስኖባቸዋል። ዘለግ ብሎ ግን እገዳው ወደ 6 ወርዶላቸዋል።
በ2021 ደግሞ ሌላ የ6 ዓመት እግድ ተጥሎባቸዋል።
ክሳቸው ምንድነው?
የስዊዝ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለስድስት ዓመታት ምርመራ ካደረገ በኋላ ብላተርን በማጭበርበርና በሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች ከሷቸዋል።
ፕላቲኒም እንደሁም በማጭበርበርና “ፎርጅድ” በማሠራት እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ መዝገቦች ተከሷል።
ፕላቲኒ በ2011 ከሴፕ ብላተር 2 ሚሊዮን የስዊዝ ፍራንክ አሊያም 1.5 ሚሊዮን ዩሮ ተቀብሏል ተብሎ ክስ ቀርቦበታል።
ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ፕላቲኒ ለማማከር ሥራው በዓመት 300 ሺህ የስዊዝ ፍራንክ እንዲከፈለው ስምምነት ቢኖርም ተጨማሪ 2 ሚሊዮን ተቀብሏል።
ሁለቱ ግለሰቦች ገንዘቡ ለማማከር ሥራ እንዲከፈል የቃል ስምምነት በመድረሳቸው የተከፈለ ነው።
ብላተር ክፍያው ሕጋዊ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።
የሁለቱ ሰዎች ክስ ስዊዝ ውስጥ በፈረንጆቹ ሰኔ 22 ጀምሮ ሐምሌ 8 ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ አምስት ዓመት እስር አሊያም የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።