ኢድ አል-አደሃ: በሃይማኖት ውስጥ እንስሳት ለምን ለመሥዋዕትነት ይቀርባሉ?

በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የእርድ በዓል ተብሎ የሚታወቀው የኢድ አል-አደሃ በዓል ነብዩ ኢብራሂም ወንድ ልጃቸውን መሠዕዋት ለማድረግ ፍቃደኛ መሆናቸውን ለማሰብ ይከበራል።

ነብዩ ኢብራሂም በአላህ ትዕዛዝ ልጃቸው እስማኤልን መሠዋዕት ለማድረግ ተዘጋጅተው ነበር። ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለመሥዋዕትነት ሲያዘጋጁ አላህ አስቁሟቸው በልጃቸው ፈንታ በግ መሠዕዋት እንዳደረጉ ይታመናል።

በመላው ዓለም የሚገኘው ሕዝበ ሙስሊሙ የተለያዩ እንስሳትን መሠዕዋት እያደረገ በዓሉን ያከብራል።

እንስሳትን መሠዕዋት በማድረግ ዙሪያ በሌሎች ሃይማኖቶችን እንዴት ይታያል? በክርስትና፣ በሂንዱ እና በአይሁድ እምነቶች እንስሳትን መሠዕዋት ማድረግን በተመለከተ እንዴት ይታያል?

አይሁድ

እንስሳትን መሠዋዕት ከማድረግ ጋር በተያያዘ የአይሁድ እና የክርስትና ሃይማኖቶች ከእስልምና ታሪክ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።

የአይሁድ የሃይማኖት መሪ የሆኑት ጌሪ ሶመርስ በአይሁድ የእምነት ጽሑፎች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት እና ቦታዎች የተለያዩ የእንስሳት መሠዕዋትነቶች ተጠቅሰው ይገኛሉ ይላሉ።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ መሠዕዋትነት ይፈጸምባቸው የነበሩ ስፍራዎች ባለመኖራቸው የእምነቱ ተከታዮች መሰል ተግባራትን አይፈጽሙም። "አሁን እነዛን መሠዋዕትነት በጸሎት ብቻ ነው የምናስባቸው" ይላሉ።

በአሜሪካን ጂዊሽ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ራባይ ብራድሊ ሻቪት (ዶ/ር) የእስሳት መሠዕዋትነት የሚፈጸምባቸው የሃይማኖት ስፍራዎችን ሮማውያን በማውደማቸው አሁን ላይ የእንስሳት መሠዋዕትነት አይፈቀድም ይላሉ።

"ሮማውያን ሁለተኛውን የሃይማኖት ሰፍራ በማውደማቸው የእንስሳት መሠዕዋትነት በአሃይዱ እምነት አይፈቀደም። ብዙዎች ሙሉ በሙሉ እንደተከለከለ አድርገው ያስባሉ ሌሎች ደግሞ መሲህ ከመጣ በኋላ ሰርዓቱ ዳግም ይጀመራል ብለው ያምናሉ" ይላሉ።

ብራድሊ በንግግራቸው በወደመው የአይሁድ የሃይማኖት ስፍራ ብለው የሚገልጹት በአሁኑ ወቅት በእየሩሳሌም ከተማ አል-አቅሳ መስጅድ የሚገኝበት ስፍራ የነበረን ቦታ ነው።

አይሁዳውያን ይህ የሃይማኖት ቦታ ተመልሶ ተገንብቶ እንስሳትን መሠዕዋት የማድረግ ተግባራቸውን መልሰው መቀጠልን ይመኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ምንም እንኳ አብዛኛው አይሁድ እንስሳትን መሠዕዋት በማድረግ ተግባር ባይሳተፍም በእየሩሳሌም ያሉ እና ሳማሪታንስ የተባሉ አይሁዶች አሁንም ድረስ ሃይማኖታዊ ተግባሩን አስቀጥለዋል።

ለመሠዋዕትነት የሚቀርቡት እንስሳት እንደ በግ፣ ላም፣ ፍየል ወይም ጎሽ ያሉ በእምነቱ ተቀባይነት ያላቸው "ኮሸር" የሆኑ እንስሳት መሆን አለባቸው።

ክርስትና

እንስሳትን በመሠዕዋትነት በማቅረብ ረገድ ክርስትና ስር መሰረቱ ከአይሁድ ጋር ይያያዛል። የአይሁዶች ሃይማኖታዊ ጽሑፍ እንዲሁ ከብሉይ ኪዳን ጋር ተመሳሳይነት አለው።

በኢንዶኔዢያ ዳካ ከተማ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ፕኦሻንቶ ቲ ሬቤኢሮ (ዶ/ር) በብሉይ ኪዳን ዘሌዋውያን 17 ላይ እንስሳት እንዴት መሠስዕዋት መሆን እንዳለባቸው በዝርዝር ይገልጻል ይላሉ።

አንዳንድ ግዜ እንስሳት ለመሠዕዋትነት የሚቀርቡት ከፈጣሪ ይቅርታን ለማግኘት በማሰብ ነው ይላሉ እኚህ አገልጋይ።

ይሁን እንጂ የእየሱስ ክርስቶስ ሞት እንደ የመጨረሻው መሠዋዕትነት ተደርጎ ስለሚታሰብ ይህ ልማድ በሃይማኖቱ አይተገበርም።

እየሱስ በክርስትና እንደ ‘የእግዚአብሔር በግ’ ይቆጠራል።

የሂንዱ እምነት

ምንም እንኳን በሂንዱ እምነት ውስጥ በእንስሳት መሠዕዋትነት ዙሪያ የተለያዩ አለመግባባቶች ቢኖሩም፤ በተወሰኑ ሂንዱዎች ዘንድ ተግባራዊ ይደረጋል።

ለምሳሌ፣ በብዙ የሕንድ ወይም ባንግላዴሽ አካባቢዎች በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንስሳት መሠዕዋት የማድረግ ተግባር በሰፊው ይከናወናል።

እንስሳት መሠዋዕት ማድረግ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1500 እና 500 መካከል የተለመደ ተግባር እንደሆነ ይታመናል። እንስሳው ለፈጣሪ ተብሎ መሠዕዋት ከሆነ በኋላ ስጋው ለሃይማኖቱ ተከታዮች በግብዣ መልክ ይቀርብ ነበር።

ይሁን እንጂ በዘመናዊ ሕንድ የእንስሳትን መሠዕዋትነትን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች አሉ።

የሃይማኖቱ መሪዎች እንደሚሉት ሰዎች በሃይማኖት ሰበብ እንስሳትን መሠዕዋት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ለግላዊ ፍላጎት እንጂ ሃይማኖታዊ ፍይዳ ኖሮት አይደለም ይላሉ።

እንደ ስሪ ላንካ እና ኔፓል ያሉ አገራት በሂንዱ እምነት እንስሳትን መሠዕዋት ማድረግን ከልክለዋል። ይሁን እንጂ ይህ ትዕዛዝ ሁሌም የሚከበር አይደለም።