ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለ17 አመታት በሲኤንኤን ያገለገለው ዋና አቅራቢ ዶን ሌመን ከሥራ ተባረረ
ለ17 አመታት በሲኤንኤን ያገለገለው ዋና አቅራቢ ዶን ሌመን ከሥራ መባረሩን ተከትሎ ቁጣውን ገለጸ።
ሲኤንኤን ጋዜጠኛውን ያባረረው በሥነ ምግባር ጉድለትና ጾተኝነት በተሞላው ንግግር ውንጀላ መሆኑም ተገልጿል።
ዶን ሌመን ስለ መባረሩ የተነገረውም በወኪሉ አማካኝነት እንደሆነ በትዊተር ገጹ “በጣም አስደንጋጭ ነው” ሲል አስፍሯል።
ሲኤንኤን በበኩሉ የማለዳ ዝግጅቱን ከሚያቀርበው ዶን ሌመን ጋር መለያየቱን ገልጾ፣ ለጋዜጠኛው “መልካም እንዲገጥመው እንመኛለን” ብሏል።
ጋዜጠኛው የ51 ዓመቷ ሪፐብሊካን ኒኪ ሃሌይ ‘በፍሬያማ’ ወቅቷ ላይ አይደለችም የሚል አስተያየቱ ነው ሲኤንኤንን እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሰው።
ከዶን ሌመን መባረር በተጨማሪም በአሜሪካ ሚዲያ ስመ ጥር የተባለው ተከር ካርልሰን ከፎክስ ኒውስ ጋር መለያየቱ ተገልጿል።
ዶን ሌመን ለረጅም ጊዜ በሲኤንኤን ‘ዚስ ሞርኒንግ’ በተሰኘው ፕሮግራም በአዘጋጅነትና በአቅራቢነት አገልግሏል።
ሆኖም በቅርቡ የወደፊቱ የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንት እጩ ይሆናሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት አምባሳደር እና የደቡብ ካሮላይና አስተዳዳሪ ላይ የሰጠው አስተያየት ከፍተኛ ውግዘትን እንዲያስተናግድ ምክንያት ሆኗል።
ሃሌይ “በፍሬያማዋ ወቅት ላይ አይደለችም” የሚለው የጋዜጠኛው አስተያየትም ጾተኛ ነው ተወግዟል።
"አንዲት ሴት በፍሬያማዋ ወቅት ላይ ነው ተብላ የምትቆጠረው በ20ዎቹ፣ በ30ዎቹ እንዲሁም ምናልባትም በ40ዎቹ ዕድሜዋ ላይ ነው” የሚልም አስተያየት ሰጥቷል።
ይህንንም በሚናገርበት ወቅት ከሴት የሥራ ባልደረቦቹና አቅራቢዎቹ ፖፒ ሃሎው እና ኬትላን ኮሊንስ ተቃውሞ ቢያቀርቡም “እውነቴን ነው የምናገረው፣ ከጉግል ማጣራት ትችላላችሁ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ጋዜጠኛው አስተያየቱን ከሰጠ በኋላም “የማይገባ እና ተዛማጅነት” የሌለው አስተያየት በመስጠቱ ይቅርታ ጠይቋል። በተጨማሪም የዜና ክፍሉን ይቅርታ ጠይቆ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት “አስገዳጅ ስልጠናም” ለመውሰድ ተስማምቶ ነበር።
ነገር ግን አስተያየቱ መጠነ ሰፊ ትችቶችን አስተናግዷል። ከነዚህም መካከል የ60 ዓመቷ ተዋናይት ሚሼል ዮህ በኦስካር የፊልም ሽልማት ላይ በቀረበችበት ወቅት “ሴቶች ማንም ሰው ጊዜያችሁ አልፏባችኋል እንዲላችሁ አትፍቀዱ” ብላለች።