ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዴንማርኳን ጠቅላይ ሚኒስትር በቡጢ የተማታው ግለሰብ በአራት ወር እስር ተቀጣ
የዴንሟርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜት ፍሬድሪክሰንን በቡጢ የተማታው ግለሰብ በጥቃት ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኘ።
በመዲናዋ ኮፐንሃገን የሚገኝ ፍርድ ቤት ፖላንዳዊውን ግለሰብ በአራት ወር እስር እንዲቀጣ ብያኔ አስተላልፎበታል።
በተጨማሪም ተከሳሹ ከአገር እንዲባረር እንዲሁም ወደ ዴንማርክ ለአምስት ዓመታት እንዳይገባ የእግድ ውሳኔ ተጥሎበታል።
ስሙ ያልተጠቀሰው ይህ የ39 ዓመቱ ተከሳሽ በወቅቱ ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ ስለነበር ክስተቱን እንደማያስታውስ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከሁለት ወራት በፊት በከተማዋ ማዕከል በሚገኝ አደባባይ ላይ እየተራመዱ ባለበት ወቅት ነው አንድ ግለሰብ ትከሻቸውን በቡጢ የጎሸማቸው። በዚህም ጥቃት መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር ተዘግቧል።
ፖላንዳዊው በመንግሥት ሰራተኛ ላይ ላይ ጥቃት በመፈጸም በሚል ክስ እንዲሁም በማጭበርበር እና በህዝባዊ ቦታዎች ራስን ያላግባብ በማጋለጥ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
የእስር ወራቱንም ካጠናቀቀ በኋላ ከዴንማርክ የሚባረር ሲሆን ለፍርድ ሂደቱ የወጣውንም ወጪ መክፈል እንደሚኖርበት ተወስኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሜት በችሎቱ ሂደት ላይ በምስክርነት እንዲቀርቡ አልተጠየቁም።
ተከሳሹ የጥቃት ወንጀሉን አልፈጸምኩም ብሎ የተከራከረ ሲሆን በሌሎች ክሶች ግን ጥፋተኛነቱን አምኗል።
ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ ስለነበር ሁኔታውን እንደማያስታውስ እና ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጋር ፊት ለፊት በተገናኘበት ወቅት “መጥፎ ቀን” እንዳሳለፈ ተናግሯል።
የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ ሊካሄድ ሁለት ቀናት ሲቀሩት በተፈጸመባቸው ጥቃት ጠቅላይ ሚኒስትሯ አንገታቸው እና ትከሻቸው ላይ ቀለል ያለ ጉዳት ደርሶባቸው ነበር።
በወቅቱም ክስተቱ እንዳስደነገጣቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሯ በዚህም የተነሳ በምርጫው ቅስቀሳ ዘመቻ የመጨረሻ ዕለትም ሳይሳተፉ ቀርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ በዴንማርክ ጥምር መንግስት ውስጥ ትልቁ እና የግራ ዘመም ፖለቲካን የሚያራምደው የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ መሪ ናቸው።
የ46 ዓመቷ ሜት ፍሪድሪክሰን ወደ ስልጣን የመጡት በአውሮፓውያኑ 2019 ሲሆን ይህም በዴንማርክ ታሪክ ትንሿ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጓቸዋል።