የታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ‘ቦርጫም’ ፖሊሶች ወደ ሥልጠና እንዲገቡ አዘዙ

የፎቶው ባለመብት, TANZANIA STATE HOUSE
የታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን ‘ቦርጫም’ የሆኑ የፖሊስ አባላት ክብደታቸውን እንዲቀንሱ ዳግም ሥልጠና እንዲገቡ አዘዙ።
ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት በኢሚግሬሽን ዘርፍ የአገሪቱ ፖሊስ አባላት ምረቃ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
ሳሚያ ሐሰን በፖሊስ አባላት ምረቃ ላይ በነበረው የሰልፍ ትርዒት ላይ ከተመለከቷቸው የፖሊስ አባላት መካከል ቦርጫም የሆኑ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
“የሰልፍ ትርዒቱን ስመለከት ነበር። ትርዒቱን ሲመሩ ከነበሩት መካከል ነባር፣ ብዙ ልምድ ያላቸው ፖሊሶች አሉ፤ ከእነርሱ መካከልም ቦርጫም የሆኑ አሉበት” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቷ የፖሊስ አባላቱ ቀልጠፍ ብለው የሚጣልባቸውን ግዴታ በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ ክብደታቸውን መቀነስ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።
“ቦርጫቸውን ለማጥፋት እና ኃላፊነታቸውን በቅልጥፍና ለመወጣት ወደዚህ (ወደ ሥልጠና ማዕከሉ) መመለስ አለባቸው” ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሐሰን አዘዋል።
በበርካታ አገራት ውስጥ ያሉ የፖሊስ መኮንኖች እንደ ታንዛኒያ ሁሉ ቦርጫምና ከፍተኛ ክብተደት እንዳላቸው ይነገራል።
ይህንንም አንዳንዶች ከሙስና ጋር ሲያያይዙት፣ ሌሎች ደግሞ ፖሊሶቹ የሚጠበቅባቸውን ተገቢውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን ያነሳሉ።
በዚህም ሳቢያ በሥራቸው ምክንያት ለሚያጋጥማቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ብቁ አይደሉም በማለት ይተቻሉ።
ፕሬዝዳንት ሳሚያ ይህን አስተያየት የሰጡት በቅርቡ የአገሪቱን የፖሊስ ዋና አዛዥን ከሥልጣን አንስተው የአገሪቱ መልዕክተኛ በማድረግ ወደ ዚምባብዌ ከላኩ በኋላ ነው።
የአገር ወስጥ መገናኛ ብዙኃን ሳሚያ ሐሰን የፖሊስ አዛዥ የነበሩትን ሲሞን ሲሮ ከአንድ ወር በፊት ከሥራ ያሰናበቱት በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው ነው ሲሉ ዘግበዋል።
ሳሚያ ሐሰን ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በፊት የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ሞትን ተከትሎ ሥልጣን መረከባቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቷ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ተጽእኖ ፈጣሪ መሪ መሆን የቻሉ ሲሆን፤ እውቁ ታይም መጽሔትም በዚህ የፈረንጆች ዓመት 100 ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ አካቷቸዋል።












