ከእነዚህ 7 ‘ውድ’ ተጨዋቾች ዝውውራቸውን የሚያጠናቅቁ ይኖሩ ይሆን?

ፎፋና፣ ሮናልዶ እና ኦባሚያንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፎፋና፣ ሮናልዶ እና ኦባሚያንግ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ ዝነኛ ሊጎች የወድድር ዘመናቸውን መጀመራቸውን ተከትሎ ክለቦች በየትኛው የሜዳ ክፍል ራሳቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው እየለዩ ነው።

ቢቢሲ ስፖርት ወደ ሌሎች ክለቦች ሊዘዋወሩ የሚችሉ “ውድ” ያላቸውን 7 ተጫዋቾችና ያሏቸውን አማራጮች ተመልክቷል።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ (ማንቸስተር ዩናይትድ)

ክርስቲያኖ ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ክርስቲያኖ ሮናልዶ

ሮናልዶ ክለቡን መልቀቅ መፈለጉ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ተጫዋቹ ከአንዴም ሁለቴ ልቀቁኝ ሲል ተናግሯል።

ሮናልዶ ክለቡን የሚለቀው በቻምፒየንስ ሊግ መጫወት ስለምፈልግ ነው ይበል እንጂ በቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ የሆነ አንድም ቡድን በሮናልዶ ላይ ፍላጎት አላሳየም።

የ37 ዓመቱ ተጫዋች የሚጠይቀው ከፍተኛ ክፍያ ለክለቦች የሚቀመስ አልሆነም። የውድድር ዓመቱን አሳፋሪ በተባሉ ሽንፈቶች ለጀመረው ዩናይትድ ሮናልዶ በመልበሻ ክፍል ውስጥ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጣሪ ነው የሚል ሪፖርት ዘ አትሌቲክ ይዞ ወጥቷል።

አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ሮናልዶ አይሸጥም ይበሉ እንጂ ክለቡ ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 10/2014 ዓ.ም. በሮናልዶ ላይ የነበረውን አቋም በመቀየር ክለቡን እንዲለቅ እንደሚፈቅድ ተገልጿል።

ይህን ተከትሎ የሮናልዶ ወኪል ተጫዋቹን ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ ለማዘዋወር ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል።

ፍራንኪ ዲ ዮንግ (ባርሴሎና)

ፍራንኪ ዲ ዮንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፍራንኪ ዲ ዮንግ

ባለፉት ወራት የዲ ዮንግ ስም ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።

ዩናይትድ ለዲ ዮንግ 56 ሚሊዮን ፓዎንድ ለመክፈል ከባርሴሎና ጋር ከተስማማ በርካታ ሳምንታት ቢያልፉም የዝውውር ስምምነቱ ግን ፈቀቅ አላለም።

የኔዘርላንዱ አማካይ ኑ ካምፕን የመልቀቅ ፍላጎት ባይኖረውም ባርሴሎና ግን ከገባበት የፋይናንስ ቀውስ እፎይታ ለማግኘት ዲ ዮንግን ሊሸጥ ይችላል።

ይህ የዝውውር ስምምነት ተፈጻሚ እንዳይሆን ማነቆ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ ዲ ዮንግ በባርሴሎና ሳይከፍለው የቆየው ገንዘብ አንዱ መሆኑ ሪፖርት ተደርጓል።

አሁን ላይ ደግሞ ቼልሲ ዲ ዮንግን ለመወሰድ ጥረት ጀምሯል።

ፒዬር-ኢሜሪክ ኦባሚያንግ (ባርሴሎና)

ፒዬር-ኢሜሪክ ኦባሚያንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፒዬር-ኢሜሪክ ኦባሚያንግ

ቼልሲ በዚህ የዝውውር መስኮት ከ150 ሚሊዮን ፓዎንድ በላይ ወጪ በማድረግ በርካታ ተጫዋቾችን ሰብስቧል።

ክለቡን በቅርቡ የተረከቡት አሜሪካዊው ባለሃብት አሁንም በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ለንደን ከማምጣት የቦዘኑ አይመስልም።

ሮበርት ሎዋንዶውስኪ ወደ ባርሳ ማምራቱን ተከትሎ ኦባሚያንግ ወደ ቼልሲ ሊዘዋወር ይችላል።

ቼልሲ ለቀድሞ የአርሰናል አምበል ኦባ እስከ 25 ሚሊዮን ፓዎንድ ሊጠየቅ ይችላል።

ሜምፊስ ዴፓይ (ባርሴሎና)

ሜምፊስ ዴፓይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሜምፊስ ዴፓይ

ባርሳን ሊሰናበት የሚችለው ሌላኛው ተጫዋች ሜምፊስ ዴፓይ ነው።

ባርሴሎና ራፊንሃን ከሊድስ ዩናይትድ ካዘዋወረ በኋላ፤ ዴፓይ በነጻ ዝውውር ወዳሻው ክለብ መሄድ እንደሚችል ክለቡ አሳውቆታል።

የ28 ዓመቱ ሆላንዳዊ የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ የክንፍ ተጫዋች ወደ ጣሊያኑ ጁቬንቱስ ሊያመራ ይችላል።

ዌስሊ ፎፋና (ሌስተር ሲቲ)

ዌስሊ ፎፋና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዌስሊ ፎፋና

አሁንም ቼልሲ ነው። ቼልሲ የሌስተሩን ተከላካይ በውድ ዋጋ ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ ለመውስደ የሚያመነታ አይመስልም።

የመሃል ተከላካዩን ኩሊባሊን ከናፖሊ እንዲሁም የቀኝ ክንፍ ተመላላሹን ማርከ ኩከሪያልን ከብራይተን ያዘዋወሩት ሰማያዎዎቹ ለሌላ ተከላካይ ከፍተኛ ገንዘብ ለመክፈል ዝግጁ ይመስላሉ።

ቼልሲ ለ21 ዓመቱ ፈረንሲያዊ 80 ሚሊዮን ፓዎንድ ሊያወጣ ይችላል የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

አንቶኒ ጎርደን (ኤቨርተን)

አንቶኒ ጎርደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አንቶኒ ጎርደን

ኤቨርተን የፊት መስመር አጥቂያቸውን ሪቻርልሰንን በቶተነሃም ተነጥቀዋል።

ደካማ አቋም እያሳየ ባለው ኤቨርተን ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው አንቶኒ ጎርደንም ወደ ቼልሲ ሊያመራ ይችላል።

ቼልሲ ለአንቶኒ ጎርደን ያቀረበው የ40 እና የ45 ሚሊዮን ፓዎንድ የዝውውር ጥያቄዎች በኤቨርተን ውድቅ ተደርጎበታል።

ቼልሲ ግን ዳግም ተጫዋቹን ለመውሰድ ሌላ ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

አርማንዶ ብሮጃ (ቼልሲ)

አርማንዶ ብሮጃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አርማንዶ ብሮጃ

ባለፈው ዓመት በውሰት በቆየበት ሳውዛምፕተን 9 ጎሎችን በማስቆጠር ጥሩ ግዜን ያሳለፈው አጥቂው ብሮጃ የብዙ ክለቦችን ትኩረት ስቧል።

አልባናዊው አጥቂ ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ ከተመለሰ በኋላ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የመካተት እድልን አላገኘም። ይህም ወደ ሌላ ክለብ እንዲያማትር ሊያደርገው ይችላል የሚሉ ግምቶች አሉ።

ዌስት ሃም፣ ኤቨርተን እና ኒው ካስትል የ20 ዓመቱን አጥቂ የመውሰድ ጽኑ ፍላጎት ካላቸው ክለቦች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።