ሙስናን ይከላከላሉ የተባሉት የዛምቢያ ፀረ ሙስና ባለሥልጣናት በሙስና ከኃላፊነታቸው ተባረሩ

ገንዘብ በፖስታ

የፎቶው ባለመብት, ISTOCK

ሙስናን እንዲከላከሉ የተሾሙት የዛምቢያ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የቦርድ አባላት እራሳቸው ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል በሚል በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ከኃላፊነታቸው ተባረሩ።

የመንግሥታዊው የፀረ ሙስና ተቋም የቦርድ አባላት ቢያስተባብሉም የሙስና ክስ መቀረቡን ተከትሎ ነው የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ሃኪንዴ ሂቺሌማ ለየት ያለ ውሳኔ በማሳለፍ ሁሉንም ከሥልጣን ያሰናበቱት።

የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ይፋ የሆነው የአገሪቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዋና ኃላፊ ቶማስ ሻማካምባ በፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸው ከተነገረ ከቀናት በኋላ ነው።

ባለሥልጣኑ በፈቃዳቸው ሥራቸውን ይልቀቁ ወይም በፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ከኃላፊነታቸው ይባረሩ በይፋ የታወቀ ነገር የለም።

ከሥልጣን የለቀቁት ኮሚሽነሩ እና የተቋሙ ዋና ዐቃቤ ሕግ ማርሻል ሙቼንዴ ጉቦ በመቀበል የተከሰሱ ሲሆን፣ ሁሉቱም ግን የቀረበባቸውን ክስ ሐሰት ሲሉ አስተባብለዋል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሂቺሌማ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ባለሥልጣናት በሙስና በተከሰሱ የቀድሞው አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ምርመራ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

አሁን በፀረ ሙስና ኃላፊዎች ላይ የቀረበው ክስም ከዛምቢያ የቀድሞ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል። በዚህም ምርመራ እየተደረገባቸው ላሉት የቀድሞ ፖለቲከኞች ምርመራቸው ተቋርጦ ምህረት እንዲያገኙ ለማስቻል ገንዘብ ተቀብለዋል ተብሏል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ጥቆማ የሰጠው ቀድሞ በፀረ ሙስና ኮሚሽን ውስጥ የቦርድ አባል የነበረው ኦብሪን ካባ የተባለ ግለሰብ እንደሆነ ተገልጿል።

ግለሰቡ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በጽሁፍ ይፋ እንዳደረገው “በወጡ ዘገባዎች መሠረት የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ በሙስና ከተዘፈቁ ሰዎች መካከል የተወሰኑት ከፍትህ እና ከተጠያቂነት ነጻ እንዲሆኑ የሚያስችል በሕግ ትርጉም አልባ የሆነ ስምምነት አድርጓል” በማለት ገልጾ ነበር።

ግለሰቡ ጨምሮም በቀደመው የአገሪቱ አስተዳደር ወቅት የነበረው “ከመከሰስ ነጻ የሚያደርገው ስምምነት” የአሁኑ አስተዳደር “ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኝነት የሌለው በሚያስመስል ሁኔታ” ጥቅም ላይ እየዋለ ነው በሚልም ተችቷል።

ኦብሪን ካባ ተበላሽቷል የሚለውን የአገሪቱን የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ለማስተካከል አራት የቦርድ አባላትን ማባረር ብቻ “በቂ አይደለም” በማለት ሙሉ ተቋሙ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ጠቁሟል።

የግለሰቡን ክስ ተከትሎ የተቋሙ ዋና ዐቃቤ ሕግ የነበሩት ሙቼንዴ የስም ማጥፋት ክስ መሥርተውበታል። የኮሚሽኑ ሌሎች አባላትም ተመሳሳይ ክስ በኦብሪን ካባ ላይ ሊመሠርቱ ይችላሉ እየተባለ ነው።

በፀረ ሙስና ኮሚሽኑ መሪዎች ላይ የቀረበውን ክስ ተከትሎ ከዛምቢያው ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በወጣው መግለጫ የተቋሙ የቦርድ አባላት መባረር አስፈለጊ የሆነው “ወሳኝ የሆነውን የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ኃላፊነት ለማደስ ነው” ብሏል።

የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ዋና ኃላፊ ቶማስ ሻማካምባ ከሥልጣን መልቀቃቸው ይፋ የተደረገውም ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት በወጣ መግለጫ ሲሆን፣ ይህም ባለሥልጣኑ በፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀው ሳይሆን ተባረው ነው የሚል ግምትን ፈጥሯል።