ከግብርና እስከ ማንቸስተር ሲቲ - የብራዚላዊው ሳቪንሆ ታሪክ

ሳቪንሆ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጂሮና አሠልጣኝ የሆኑት ሚቼል እንዲሁ በቀላሉ የሚረቱ አሊያም የሚታለሉ ሰው አይደሉም።

ነገር ግን ያለፈው የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት በነበረው የክረምት ወቅት ሳቪንሆን ተመልክተው ወዲያው ወደ ስፖርቲንግ ዳይሬክተሩ ኪኬ ቻርሴል ስልክ መቱ።

“በሚቀጥለው ዓመት እስከ 8 ባለው ደረጃ እናጠናቅቃለን” ሲሉ ለካርሴል ነገሯቸው። ዳይሬክተሩ ግን ምላሻቸው “አንተ ሰው ጤናማ አይደለህም መሰለኝ” የሚል ነው።

ሚቼል ግን ቃላቸውን አላጠፉም። ጂሮና ባለፈው ዓመት በስፔን ላ ሊጋ አስፈሪ ከሚባሉትን ባርሴሎናን ጭምር ከፈተኑ ክለቦች አንዱ ሆኖ ተገኘ።

ጂሮና የላ ሊጋውን ዋንጫ ለማንሳት እስከ መጨረሻው ተፋልሟል። በስተመጨረሻም ከሪያል ማድሪድ እና ከባርሴሎና ቀጥሎ ሦስተኛ ሆኖ አጠናቀቀ። በሚቀጥለው ዓመት በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ሲጫወት እንመለከተዋለን።

ይህ ጂሮና በ93 ዓመት ታሪኩ ያሳካው ትልቁ ድሉ ነው። ለዚህ ደግሞ የክንፍ ሥፍራ ተጫዋቹ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል።

ሳቪንሆ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የፒኤስቪ አይንድሆቨን ተጠባባቂ ከመሆን ተነስቶ በስፔን ጎልቶ ከመታየቱ ባሻገር ብራዚልን ወክሎ በዌልምብሌ ስታድየም መጫወት ችሏል።

“ይሄን ማለቴ ድፍረት ሊሆን ይችላል፤ ግን አንድ ለአንድ ከተከላካዮች ጋር ተፋጦ በማሸነፍ ከቪኒሲየስ ጁኒየር ቀጥሎ ምርጡ ተጫዋች ነው ብዬ ነው የማስበው” ይላሉ ሚቼል።

“ጁድ ቤሊንግሀም በሁሉም ዘንድ ይታወቃል ብለን ካሰብን፤ እሱ [ሳቪንሆ] በላ ሊጋው በጣም አስደናቂ ብቃት ያሳየን ነው ማለት እንችላለን።”

ማንቸስተር ሲቲ ሳቪንሆን በክረምቱ የዝውውር መስኮት የገዛው የመጀመሪያ ተጫዋች መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። ሳቪንሆነ ከክለቡ ትሮየስ በውሰት ነበር ወደ ጂሮና ያቀናው።

ባለፈው የውድድር ዘመን ለጂሮና 11 ግቦችን አስቆጥሮ 10 ለግብ የሚሆኑ ኳሶች ያመቻቸው የ20 ዓመቱ ሳቪንሆ በማንቸስተር ሲቲ ማሊያ መልካም ብቃት ያሳያል ተብሎ ይታመናል።

“እግር ኳስ የመጫወት ተሰጥኦ ታድዬ ነው የተወለድኩት” በማለት በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል።

የሲቲው አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ የዚህን ወጣት የክንፍ መስመር ተጫዋች ችሎታ ለመጠቀም እንደጓጉ አያጠራጥርም።

“ይህ ልጅ እግር ኳስ ተጫዋች ይሆናል”

ሳቪንሆ እንደ ሌሎች እግር ኳስ ተጫዋቾች ዓይነት ታሪክ ያለው ወጣት አይደለም።

በደቡብ ምሥራቅ ብራዚል ሳኦ ማቴውስ አያቶቹ ቤት ያደገው ሳቪንሆ በልጅነቱ ነው ፈረስ መጋለብ፣ ላሞችን ማለብ እና ጥቅል ጎመን እና ቲማቲም የመሳሰሉ አትክልቶችን መትከል የተማረው። አሁንም ቢሆን እረፍት ሲፈልግ ወደዚያ ነው የሚሄደው።

“ለመዝናናት ወደ ካንኩን ወይስ ወደ አያቶችህ መንደር መሄድ ትመርጣለህ ብላችሁ ብትጠይቁት፤ በእርግጠኝነት አያቶቹን ይመርጣል። ውስጡ የሚፈልገው እሱን ነው” ይላሉ የተጫዋቹ እናት ዶና ኒልማ።

ምንም እንኳ ሳቪንሆ ገበሬ አያቶቹ ጋር ያለው የየቀን ሕይወት ቢማርከውም እግር ኳስ ደግሞ ተሰጥኦው ነው። እናቱ ይህ ተገልጦላቸዋል። በተለይ ገና የአምስት ዓመት ሕፃን ሳለ አንድ አሠልጣኙ ይህን ብለዋል።

“ይሄ ልጅ ወደፊት ጎበዝ እግር ኳስ ተጫዋች ይሆናል” ሲሉ አሠልጣኙ ተንብየዋል።

ሳቪንሆ እግር ኳስ መጫወት የጀመረው በባሕር ዳርቻ አካባቢ ነው። ነገር ግን ወደ ሳር ሜዳ ባመራ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ነው ትላልቅ ቡድኖች ዐይናቸው የጣሉበት።

11 ዓመቱ ሳለ ከ17 ዓመት በታች በነበረው ጨዋታ ያሳየውን ድንቅ ብቃት የተመለከቱት አትሌቲኮ ሚኔሮ ባለግራ እግሩን ተዓምረኛ አስፈረሙት።

ሳቪንሆ ለብራዚል ሲጫወት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በብራዚል ሊግ በ16 ዓመቱ ለአትሌቲኮ የተጫወተው ሳቪንሆ በዕድሜ ትንሹ የሚለውን ማዕረግ ሲጎናፀፍ በ18 ዓመቱ ደግሞ በሊበርታዶስ የዋንጫ ፍፃሜ ግብ በማስቆጠር ይህን ታሪክ ደገመው።

ተጫዋቾች በፍጥነት እያደገ መምጣቱ የማንቸስተር ሲቲ መልማዮች ጊዜ ሳያጠፉ ተፎካክረው እንዲያስፈርሙት እና ከአርሰናል ዐይን እንዲያሸሹት አደረጋቸው።

ኳስን ይዞ በሰከንዶች ውስጥ አቅጣጫ በመቀያየር የሚጫወተው ሳቪንሆ በፈረንሳይ ሦስተኛው ደረጃ ለሚጫወተው ትሮየስ ተመዘገበ። ነገር ግን ምንም ጨዋታ ሳያደርግ ለፒኤስቪ አይንድሆቨን በውሰት ተሰጠ።

ቢሆንም በደረሰበት ጉዳት ምክንያት እንደፈለገው የጨዋታ ዕድሜ ያላገኘው ወጣቱ ተጫዋቹ በኔዘርላንድስ ሊግ [ኤሬዲቪዜ] መጉላት አልቻለም።

በ2023 ከ20 ዓመት የዓለም ዋንጫ የተመለከቱት ጂሮናዎች የመጣው ይምጣ ይህን ተጫዋች እናስፈርማለን ብለው ተነሱ። ምንም እንኳ ሳቪንሆ ብዙ ልምድ ባይኖረውም ሚቼል ግን የሚቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ወሰኑ።

ለካታሎኒያው ክለብ የፈረመው ሳቪንሆ አሠልጣኙ እና ክለቡን አላሳፈረም።

ሳቪንሆ በእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ በፔፕ ጉዋርዲዮላ ጥላ ሥር ቀላል የሚባል ጊዜ ይጠብቀዋል ማለት አይደለም። ነገር ግን እሱ የሚረታ አይመስልም።