“የሁለት ከዋክብት ጅማሬ”፡ ከሊዮኔል ሜሲ እና ላሚን ያማል ፎቶግራፍ ጀርባ ያለው ታሪክ ምንድን ነው?

ሜሲ እና ያማል ከ17 ዓመት ገደማ በፊት

የፎቶው ባለመብት, Joan Monfort/AP

የምስሉ መግለጫ, ሜሲ እና ያማል ከ17 ዓመት ገደማ በፊት

ከ17 ዓመታት ገደማ በፊት እአአ 2007 ላይ ሜሲ በካምፕ ኑ ተገኘ።

ወቅቱ የአርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ የእግር ኳስ ሕይወት ገና ደምቆ እየወጣ የነበረበት ጊዜ ነበር።

ሜሲ በክለቡ ባርሴሎና ስታዲየም የተገኘው ለእግር ኳስ ግጥሚያ አልነበረም።

ለበጎ አድራጎት ተግባር ገቢ ማሰባሰቢያነት የሚውል ቀን መቁጠሪያ ላይ ለሚወጣ ምሥል ከአንድ ጨቅላ ጋር ፎቶ ግራፍ ለመነሳት ነበር ሜሲ በዚያን ዕለት በካምፕ ኑ ስታዲየም የተገኘው።

በወቅቱ በኳሱ ደምቆ እየወጣ የነበረው ሜሲ፤ ላሚን ያማል የተባለውን ጨቅላ ገላ እያጠበ ፎቶግራፍ ተነሳ።

በዚያን ጊዜ ታዲያ ያጨቅላ ከ17 ዓመታት በኋላ አሁን በምርጥ የእግር ኳስ ችሎታው በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ይሆናል ብሎ የጠበቀ አልነበረም።

ላሚን ያማል ትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም. በተደረገ የአውሮፓ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ለአገሩ ስፔን ያስቆጠራት ግሩም ግብ ለአስርት ዓመታት መነጋገሪያ ሆና መቀጠሏ አይቀሬ ነው እየተባለ ነው።

ያማል ይህን ግብ ሲያስቆጥር 16 ዓመት ከ 362 ቀናት ላይ እያለ በመሆኑ በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ በዕድሜ ትንሹ ግብ አስቆጣሪ ሆኖም በታሪክ ተመዝግቧል።

ይህ የሜሲ እና የያማል የተረሳ ፎቶግራፍን የያማል አባት “የሁለት ከዋክብት ጅማሬ” ብሎ የኢንስታግራም ገጹ ላይ ከለጠፈ በኋላ ምሰሉ በይነ መረብን አጥለቅልቋል።

ፎቶ ግራፉን ያነሳው የአሶሺዬትድ ፕሬስ (ኤፒ) ፎቶግራፈር የሆነው ጆአን ሞንፎርት ነው።

ሞንፎርት አንደሚለው የላሚን ወላጆች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ያዘጋጀውን ከባርሴሎና ተጫዋች ጋር ፎቶግራፍ የመነሳት ዕጣን ካሸነፉ በኋላ ለፎቶ ልጃቸውን ይዘው ካምፕ ኑ መገኘታቸውን ያስታውሳል።

ሜሲ፣ የያማል ወላጅ እናት እና ያማል

የፎቶው ባለመብት, Joan Monfort/AP

የምስሉ መግለጫ, ሜሲ፣ የያማል ወላጅ እናት እና ያማል

ፎቶግራፈሩ ለኤፒ ሲናገር “የተሰጠኝ ኃላፊት ቀላል አልነበረም። ሜሲ በመጣም የሚያፍር ሰው ነው። ከመልበሻ ክፍል ወጥቶ ሲመጣ ገላ መታጠቢያ የፕላስቲክ ገንዳ ውስጥ ያለ ሕጻን ልጅ አገኘ። መጀመሪያ ላይ ልጁን እንዴት መያዝ እንዳለበት አንኳ ግራ ገብቶት ነበር” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳል።

ልክ እንደ ሜሲ ሁሉ ያማል ለባርሳ ገና በአምስት ዓመቱ መጫወት ጀመረ። ለባርሳ መጫወት ብቻ ሳይሆን ያማል በክለብ ደረጃ ጭምር በትንሽ ዕድሜው ብዙ ክብረ ወሰኖችን ይዟል።

ያማል ለክለቡ ባርሴሎና በትንሽ ዕድሜው ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች ነው። ከዚህ በተጨማሪ በትንሽ ዕድሜው በቻምፒየንስ ሊግ ግጥሚያ ተሰልፎ የተጫዋተ፣ በላ ሊጋ እና ኮፓ ዴላሬ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።

በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ለኤምኤልኤስ የሚጫወተው ሜሲ፤ የባርሳ እና እስካሁን የታየ የምንጊዜም ምርጡ ተጫዋች ተብሎ በበርካቶች ይወደሳል።

ከሞሮኳዊ አባቱ እና ከኢኳቶሪያል ጊኒያዊት እናት በስፔን የተወለደው ላሚን ያማል እንዲሁ በሜሲ ደረጃ የኳስ ጥበበኛ ይሆናል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ አለ።