ኡራጓዊው የሊቨርፑል አጥቂ ዳርዊን ኑኔዝ ከኮሎምቢያ ደጋፊዎች ጋር ተደባደበ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለብ ሊቨርፑል አጥቂ የሆነው ዳርዊን ኑኔዝ ረቡዕ አገሩ ኡራጓይ በተሸነፈችበት ምሽት ከደጋፊዎች ጋር ተደባደበ።
በኮፓ አሜሪካ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ኡራጓይ በኮሎምቢያ ከተሸነፈች በኋላ ነው ኑኔዝ ከኮሎምቢያ ደጋፊዎች ጋር ተደባድቧል።
አል ፓይ የተሰኘው የኡራጋይ ድረ-ገፅ እንደዘገበው ብጥብጥ የተነሳው የኡራጓይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ቤተሰቦች እና ጓደኞች የተቀመጡበት አካባቢ ነው።
ኑኔዝ የተከሰተውን ሁኔታ በተለመከተ እስካሁን ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠም።
የቴሌቪዥን ካሜራዎች እና ደጋፊዎች ኑኔዝ ወደ ስታደየሙ ወንበሮችን እየዘለለ ወደ ደጋፊዎች ሲሄድ ቀርፀው አስቀምጠዋል።
ኡራጓይ እና ኮሎምቢያ በግማሽ ፍፃሜው በአሜሪካዋ ኖርዝ ካሮላይና በሚገኘው ባንክ ኦፍ አሜሪካ ስታድየም ነው ረቡዕ ምሽት የተጫወቱት።
ሌሎች የኡራጓይ ተጫዋቾችም ከደጋፊዎች ጋር ቡጢ ገጥመው እንደነበር ዘገባዎች አስነብበዋል።
የኡራጓይ አምበል ሆዜ ማሪያ ሂሜኔዝ በሰጠው አስተያየት ተጫዋቾቹ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠበቅ ነው ግርግሩ ውስጥ የገቡት ያለ ሲሆን፣ ሁኔታው “ከቁጥጥር ውጭ የሆነ” ነው ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አምበሉ አክሎ “በሥፍራው ምንም ዓይነት ፖሊስ ስላልነበረ ቤተሰቦቻችንን ለመጠበቅ ተገደናል። ይህ ምናልባትን የሁለት ወይስ ሦስት ሰዎች ጥፋት ይሆናል። ከአቅማቸው በላይ አልኮል ጠጥተው የፈጠሩት ግርግር ነው” ብሏል።
ግርግሩ ከረገበ በኋላ ኑኔዝ ሕፃን ልጁን ታቅፎ ሜዳ ውስጥ ታይቷል።
የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኮንሜቦል የተፈጠረውን ግርግር “ፍፁም አውግዣለሁ” ያለ ሲሆን፣ ምርመራ እንደሚከፍትም አሳውቋል።
“ሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ ምንም ዓይነት ትግዕስት ማጣት እና ግጭት ሊኖር አይገባም” ብሏል ማሕበሩ።
የኮፓ አሜሪካ ፍፃሜ በሚቀጥለው ሰኞ የሚካሄድ ሲሆን፣ የመጨረሻዎቹ አራት ቡድኖች ውስጥ የገባችው ኡራጓይ በኮሎምቢያ 1-0 ተሸንፋ ለዋንጫ ሳትደርስ ቀርታለች። የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚያበስረው ፊሽካ ከተነፋ በኋላ ነው ግርግሩ የተነሳው።
በደጋፊዎች መቀመጫ አካባቢ ግርግር ከመነሳቱ በፊት ሜዳው ውስጥ የኡራጓይ እና ኮሎምቢያ ተጫዋቾች እንዲሁም የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ተጋጭተው ነበር።
የኡራጓይን የፊት መስመር እየመራ ወደሜዳ የገባው ኑኔዝ አራት ለጎል የሚሆኑ አጋጣሚዎችን ቢያገኝም አንዱንም ወደ ግብ መቀየር አልቻለም።
ሊቨርፑል ዳርዊን ኑኔዝን በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2022 ነው ከፖርቹጋሉ ክለብ ቤንፊካ በ64 ሚሊዮን ፓውንድ የገዛው። ኑኔዝ ለሊቨርፑል በ65 ጨዋታዎች 20 ጎሎች አስቆጥሯል።
ቢቢሲ የኑኔዝ ወኪሎችን አስተያየት ቢጠይቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
ኮሎምቢያ በኮፓ አሜሪካ ፍፃሜ ሰኞ ከአርጀንቲና ትጋጠማለች።












