ሩዋንዳ ስደተኞችን ከዩኬ ለመቀበል የገባችው ስምምነት ቢሰረዝም ገንዘቡን አልመልስም አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩዋንዳ የዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለመቀበል የገባችው ስምምነት መሰረዝ ተከትሎ የተቀበለችውን 310 ሚሊዮን ዶላር መመለስ እንደማይጠበቅባት አስታወቀች።
ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅድ የነበረው ወግ አጥባቂው የዩኬ ፓርቲ መሸነፉን ተከትሎ አሸናፊው ሌበር ፓርቲ ሰርዞታል።
አዲሱ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሌበር ፓርቲ ሊቀ መንበር ኬይር ስታርመር ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅድ “ሞቶ የተቀበረ” መሆኑን በሳምንቱ መጨረሻ አስታውቀዋል።
በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ይመራ የነበረው የወግ አጥባቂው መንግሥት ስደተኞችን ለመላክ ዕቅዱን ይፋ ካደረገበት ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ለሩዋንዳ 310 ሚሊዮን ዶላር ከፍሏል።
እቅዱ በገጠመው ህጋዊ ውዝግቦች የተነሳ ያልተተገበረ ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደምም ሰኞ ዕለት ከስምምነቱ የተወሰነ ገንዘብ ሊመለስ እንደሚችል ተስፋ ማድረጓን ገልጻ ነበር።
በማግስቱ የሩዋንዳ መንግሥት ቃለ አቀባይ በሃገሪቱ የመንግሥት ቴሌቪዥን ቀርበው እንደተናገሩት “ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ገንዘቡን መመለስ የስምምነቱ አካል አልነበረም” ብለዋል።
አሌይን ሙኩራሊንዳ ስምምነቱ ገንዘቡ ተመላሽ እንዲሆን አይደነግግም እንዲሁም ዩናይትድ ኪንግደም ከሩዋንዳ ጋር በጥልቀት ስትነጋገር የነበረው በአጋርነት መንፈስ ነው ብለዋል።
እቅዱ ሳይተገበር ከቆየ ከ21 ወራት በኋላ፣ ጥር ወር ላይ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አገሪቱ የማይላኩ ከሆነ የተወሰነው ገንዘብ ሊመለስ እንደሚችል ጠቁመው ነበር።
ነገር ግን በኋላ የሩዋንዳ መንግሥት ለስምምነቱ የተከፈለውን የዩናይትድ ኪንግደምን ገንዘብ የመመለስ “ግዴታ” እንደሌለበት ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት በዩናይትድ ኪንግደም በነበረው ምርጫ ለአስራ አራት ዓመታት በበበላይነት የገዛውን ወግ አጥባቂውን በአብላጫ ድምጽ የረታው የሌበር ፓርቲ መንግሥት መሪ የሩዋንዳውን ዕቅድ ውድ “ማጭበርበሪያ” ሲሉ አጣጥለው ነው የሰረዙት።
መንግሥታቸው ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት አዲስ የድንበር ደህንነት ኮማንድ በማቋቋም ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
አዲሱ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ረቂቅ ህጉ ለባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ተቃውሞዎች በተለያዩ አካላት ቀርበውበት ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ፍርድ ቤት እቅዱን ህገወጥ በማለት የፈረጀው ሲሆን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በበኩላቸው ጭካኔ የተሞላበት ሲሉ ተችተውታል።
በወግ አጥባቂው ፓርቲ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አባላት እቅዱ የህግ ተግዳሮቶች እንዳይገጥመው በማለት በተሻለ ሁኔታ የሚከላከለው ማሻሻያዎችን እንዲደረግ ጠይቀው ነበር።
የቀድውሞው የዩኬ አስተዳደር ይህ እቅድ ስደተኞች በትናንሽ ጀልባዎች አቋርጠው ወደ ዩኬ እንዳይገቡ ለማድረግ ያለመ ነው ብሎ ነበር።
በህገወጥ መንገድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ገብተዋል የተባሉ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ተልከው ጥያቄያቸው ከዚያ የሚታይበትን እቅድ ከሩዋንዳ የደህንንት ስጋት ጋር በተገናኘ በፍርድ ቤቶች መታገዱ ይታወሳል።












